ር.ሊ.ጳ. ሊዮ ጨካኝ ልብ ካለን አምላካችንን 'አባት' ብለን መጥራት የለብንም ማለታቸው ተገለጸ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሐምሌ 20/2017 ዓ.ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምእመናን በእለቱ ከሉቃስ ወንጌል 11፡1-13 ላይ ተወስዶ በተነበበውና ኢየሱስ ለሐዋርያቱ "አባታችን ሆይ" የሚለውን ጸሎት ማስተማሩን በሚገልጸው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ ተንተርሰው ባደረጉት አስተንትኖ "አባታችን ሆይ" የሚለውን ጸሎት አስፈላጊነት በማሳሰብ ጌታ ሁል ጊዜም ከእኛ ጋር ነው፣ ነገር ግን በቸርነቱ መለወጥ ይኖርብናል ሲሉ አሳስበዋል
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ክቡራን እና ክቡራት የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በወቅቱ ያደረጉትን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፣ እንድተከታተሉን ከወዲሁ እንጋብዛለን።
የተወዳድችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ መልካም እለተ ሰንበት ይሁንላችሁ!
የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን "አባታችን ሆይ" የሚለውን ጸሎት ያስተማረበትን ሁኔታ ያቀርብልናል (ሉቃስ 11፡1-13)፣ ሁሉንም ክርስቲያኖች አንድ የሚያደርግ ጸሎት ነው። በዚህ ውስጥ፣ ጌታ እግዚአብሔርን “አባ”፣ “አባት” ብለን እንደ ሕጻናት ልጆች ሆነን እንድንጠራው ይጋብዘናል፣ “በቀላል [...]፣ በልጅነት መተማመን፣ [...] ትሕትና በተሞላበት ድፍረትና፣ በመወደድ እርግጠኝነት” (የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ ቁ. 2778) ልንጸልየው የሚገባን ጸሎት ነው።
የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በጣም በሚያምር አገላለጽ ስለዚህ ሁኔታ የገለጸ ሲሆን በዚህ ረገድ አባታችን ሆይ የሚለው ጸሎት “አብን ለእኛ በሚገልጽበት ቅጽበት፣ እኛንም ለራሳችን ይገልጻል" (ቁ. 2783) ይላል። እውነትም ነው፡ በሰማዩ አብ በመታመን አብዝተን በምንጸልይ ቁጥር እንደ ተወዳጅ ልጆች አድርገን ራሳችንን በገለጥን መጠን፣ የፍቅሩን ታላቅነት የበለጠ እናውቃለን (ሮሜ 8፡14-17)።
እንግዲህ የዛሬው ቅዱስ ወንጌል የእግዚአብሔርን የአባትነት ባህሪያት አንዳንድ ቀስቃሽ ምስሎችን ይገልፃል፡- ጓደኛው ያልጠበቀውን እንግዳ ለመቀበል በእኩለ ሌሊት ተነስቶ የረዳውን ሰው ያሳያል። ወይም ለልጆቹ መልካም ነገር ለመስጠት የሚጨነቅ ወላጅ ምን እንደሚመስል ያሳየናል።
በሩን ለማንኳኳት ዘግይተን ብንደርስም ምናልባት ከስሕተት፣ ካመለጡ አጋጣሚዎች ወይም ውድቀቶች በኋላ አምላክ ወደ እርሱ ስንመለስ ፊቱን እንደማይመልስ ያሳስበናል። እኛን ለመቀበል እንኳን በቤቱ የተኙትን ልጆቹን “መቀስቀስ” አለበት (ሉቃስ 11፡7)። በእርግጥም፣ በቤተክርስቲያኗ ታላቅ ቤተሰብ ውስጥ፣ አብ በሁሉም የፍቅር ምልክቶች ለመካፈል አያመነታም። ጌታ ወደ እርሱ ስንጸልይ ሁል ጊዜ ይሰማናል፣ እናም አንዳንድ ጊዜ እና ለመረዳት በሚያስቸግር መንገድ ከሆነ፣ እሱ ከአእምሮአችን በላይ በሆነ ጥበብ እና አሳቢነት ስለሚሰራ ነው። ስለዚህ፣ በእነዚህ ጊዜያትም ቢሆን፣ መጸለይን አናቋርጥም፣ እናም በመተማመን እንልይ፡ በእርሱ ውስጥ ሁል ጊዜ ብርሃን እና ብርታት እናገኛለን።
የጌታን ጸሎት መድገም ግን፣ የመለኮታዊ ልጅነት ጸጋን ከማክበር በተጨማሪ፣ ለዚህ ስጦታ ምላሽ ለመስጠት ያለንን ቁርጠኝነት እንገልፃለን፣ እርስ በርሳችን በክርስቶስ ወንድማማቾች ነን። ከቤተክርስቲያኗ አባቶች አንዱ ይህንን በማሰላሰል እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እግዚአብሔርን ‘አባታችን’ ብለን ስንጠራው እንደ ወንድ እና ሴት ልጆቹ የመሆን ግዴታችንን መዘንጋት የለብንም።” እናም ሌላው ደግሞ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከእንግዲህ ወዲህ ጨካኝና ሰብዓዊ ያልሆነ ልብ ያለን ሰው ከሆንን፣ በአእምሮዋችን ውስጥ ቸር የሆነው የሰማዩ አባታችሁ መልካምነት በውስጣችሁ የለም" (ቅዱስ ዮሐንስ ክሪሶስታም) በማለት ገልጿል። እንደ አባት ቆጥረነው ወደ እግዚአብሔር እንደ “አባት” አድርገን መጸለይ እና ከዚያም ጨካኝ እና ለሌሎች ግድ የለሽ መሆን አንችልም። ይልቁንም ራሳችንን በመልካምነቱ፣ በትዕግሥቱ፣ በምሕረቱ እንድንለወጥ፣ ፊቱን እንደ መስታወት እንድናንጸባርቅ መፍቀድ አስፈላጊ ነው።
ውድ ወንድሞች እና እህቶች፣ የዛሬው ሥርዓተ ቅዳሴ በጸሎትና ምጽዋት፣ እግዚአብሔር እንደሚወደን እኛም እንድንወድ እና እንድንዋደድ ይጋብዘናል፡ በመገኘት፣ በማስተዋል፣ በመተሳሰብ፣ ያለ ምንም ስሌት። ማርያም ለዚህ ጥሪ እንዴት ምላሽ እንደምንሰጥ፣ የአብን ፊት ጣፋጭነት እንድትገልጽ አማላጅነቷን እንማጸን።