MAP

በዋና ከተማ ዳካ የባንግላዲሽ ተዋጊ ጄት የተከሰከሰበት ሥፍራ በዋና ከተማ ዳካ የባንግላዲሽ ተዋጊ ጄት የተከሰከሰበት ሥፍራ  

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በባንግላዲሽ የተዋጊ አውሮፕላን አደጋ የተጎዱትን በጸሎታቸው አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የባንግላዲሽ ተዋጊ ጄት በአንድ ትምህርት ቤት ላይ ተከስክሶ ቢያንስ 31 ሰዎች የሞቱበትን አደጋ በማስታወስ፥ “ሟቾቹን በሙሉ ቻይ ለሆነው መሐሪ እግዚአብሔር አደራ እሰጣለሁ” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በባንግላዲሽ በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ በሞቱት ሰዎች ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

የባንግላዲሽ አየር ሃይል ተዋጊ ጄት በዋና ከተማዋ ዳካ በሚገኘው “ማይልስቶን” ትምህርት ቤት እና ኮሌጅ ላይ ተከስክሶ ቢያንስ ሰላሳ አንድ ሰዎችን መግደሉ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ማክሰኞ ሐምሌ 15/2017 ዓ. ም. በላኩት የቴሌግራም መልዕክት፥ ሟቾቹን በሙሉ ቻይ ለሆነው መሐሪ እግዚአብሔር አደራ እሰጣለሁ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በፈረሙት መልዕክት ላይ እንደገለጹት፥ “በሐዘን ላይ የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው እንዲጽናኑ የተጎዱትም ፈውስን እና መጽናናት እንዲያገኙ እጸልያለሁ” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የቴሌግራም መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ “ለመላው የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ እና በዚህ አደጋ ለተጎዱት በሙሉ የሰላም እና የጥንካሬ መለኮታዊ በረከቶችን ተመኝተውላቸዋል።

ተዋጊ ጄቱ ከባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ ጋር ተጋጭቶ የወደቀበት ሥፍራ
ተዋጊ ጄቱ ከባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ ጋር ተጋጭቶ የወደቀበት ሥፍራ   (ANSA)

የአደጋው ምክንያት እየተጣራ ይገኛል

በባንግላዲሽ መዲና ዳካ ውስጥ የተከሰተው ይህ የአውሮፕላን አደጋ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ከተከሰተኡት መካከል እጅግ አስከፊ መሆኑ ተነግሯል።

በባንግላዲሽ መዲና ዳካ ኡታራ በተባለ ሠፈር በሚገኝ ትምህርት ቤት እና ኮሌጅ ላይ የተከሰከሰው ኤፍ-7 ቢጂአይ የተሰኘ ተዋጊ ጄት የቻይና ስሪት እንደሆነ ታውቋል።

ከሟቾቹ መካከል ፓይለቱ እንደሚገኝ፣ ጉዳት ከደረሰባቸው 171 ሰዎች መካከል በርካታ ተማሪዎች መቁሰላቸውን፥ በርካቶችም በእሳት መቃጠላቸውን የባንግላዲሽ አየር ኃይል አስታውቋል።

አየር ኃይሉ በመግለጫው፥ በመዲናዋ ዳካ አቅራቢያ ኩርሚቶላ ከሚገኝ የባንግላዲሽ አየር ኃይል ሠፈር በአገሪቱ አቆጣጠር ከቀኑ ሰባት ሰዓት ከስድስት ደቂቃ ላይ የተነሳው ጄቱ በብልሽት ምክንያት ብዙም ሳይቆይ ወዲያውኑ በእሳት መያያዙን፣ 

ፓይለቱ ሰዎች በሚበዙባቸው አካባቢዎች እንዳይከሰከስ ቢሞክርም ሄዶ ከባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ ጋር ተጋጭቶ መውደቁን የአየር ኃይል መግለጫ አስታውቋል።

ጦር ጄቱን የቴክኒክ ብልሽት እንዳጋጠመው የገለጸው አየር ኃይሉ፥ የአገሪቱ ከፍተኛ የአየር ኃይል ኮሚቴ የብልሽቱን ምክንያት በማጣራት ላይ እንደሚገኝ አክሎ አስታውቋል።

 

23 Jul 2025, 17:03