MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በአረጋውያን ማዕከል የሚኖሩ ተረጂዎችን እና ገዳማውያትን ሲጎበኙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በአረጋውያን ማዕከል የሚኖሩ ተረጂዎችን እና ገዳማውያትን ሲጎበኙ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ በአረጋውያን ማዕከል የሚኖሩ ተረጂዎችን ለእምነታቸው ምስክርነት አመሰገኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ከሮም ወጣ ብሎ በሚገኝ በአልባኖ የቅድስት ማርታ አረጋውያን ማዕከል ውስጥ የሚኖሩ ተረጂዎችን እና ገዳማውያትን ጎብኝተዋል። ቅዱስነታቸው ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት የምስጋና፣ የተስፋ እና የአስተንትኖ ቃለ-ምዕዳንን አሰምተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ሰኞ ሐምሌ 14/2017 ዓ. ም. ማለዳ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ በሚገኝበት ካስቴል ጋንዶልፎ የተገነባውን የቅድስት ማርታ የአረጋውያን ማዕከልን ጎብኝተው፥ በማዕከሉ ውስጥ ለሚኖሩ ሴት ተረጂዎች እና ለተንከባካቢ ገዳማውያት የማጽናኛ እና የማበረታቻ ምክራቸውን ለግሠው መንፈሳዊ ቅርበታቸውንም ገልጸውላቸዋል።

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል በቴሌግራም በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አጭር የበጋ ዕረፍት ከሚያደርጉበት ማረፊያ ቤት ጋር በአንድ አካባቢ የሚገኘውን የአረጋውያን ማዕከል የሚያስተዳድሩ ገዳማውያት ለቅዱስነታቸው አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን በገዳማውያቱ የበላይ አለቃ በመመራት በጸሎት ቤት ውስጥ የጽሞና ጸሎት አድርሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመቀጠልም፥ በማዕከሉ ውስጥ ከሚኖሩት ዕድሜያቸው ከ80 እስከ 101 ዓመት ከሆናቸው ሃያ ሴት አረጋውያን  ጋር ሰላምታ ተለዋውጠዋል። በማዕከሉ ውስጥ የሚኖሩትን የሚንከባከቡ ገዳማውያትን አነጋግረው ታሪካቸውን ካዳመጡ በኋላ የማበረታቻ እና የፍቅር ምክራቸውን አካፍለዋል።

በአንዲት የማዕከሉ ወጣት ነርስ የአቀባበል ንግግር ከተደረገላቸው በኋላ በመዝሙር የተደገፈ የጋራ ጸሎት ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመቀጠል በዕለቱ በተዘመሩ መዝሙሮች እና እሑድ ዕለት በተነበበው የቅዱስ ወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ቃለ-ምዕዳናቸውን አሰምተዋል።

ኢየሱስ ክርስቶስን በቤታቸው ስለተቀበሉት ሁለት እህትማማቾች የሚናገረውን የቅዱስ ወንጌል ክፍል በመጥቀስ ቃለ-ምዕዳናቸውን ያሰሙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “በእያንዳንዳችን ውስጥ የቅድስት ማርታ እና የእመቤታችን ቅድስት ማርያም ክፍል አለን” ብለዋል። አክለውም “ይህ የሕይወት ደረጃ በውስጣችን ያለችውን ቅድስት ማርያምን የምንቀበልበት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እግር ሥር የምንቀመጥበት፣ ቃሉን የምናዳምጥበት እና የምንጸልይበት ጊዜ ነው” ብለዋል።

በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ አረጋውያን ያላቸውን ጠቀሜታ በማረጋገጥ የማዕከሉ ነዋሪዎች በኅብረት ላቀረቡት ጸሎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የጸሎት&Բ;አስፈላ͊ነት

“ጸሎት እጅግ አስፈላጊ እና ከምንገምተው በላይ ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በዕድሜ ወጣት ወይም አረጋውያን ብሆንም እንግዳችን ሆኖ ዘወትር ወደ እኛ የሚቀርብ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምስክሮቹ እንድንሆን ይጋብዘናል” ብለዋል።

የማዕከሉ አረጋውያን በእምነታቸው እንዲበረቱ እና እንዲተማመኑ በማበረታታት፥ ለቤተ ክርስቲያን እና ለዓለም በሙሉ የተስፋ ምልክቶች እንደሆኑ ገልጸውላቸዋል።

“በሕይወት ዘመናችሁ ብዙ አበርክታችኋል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ያለውን ለእግዚአብሔር የሚያቀርብ ቤተሰብ መሆንን በመቀጥል፥ የጸሎት እና የእምነት ምስክሮች እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከማዕከሉ ማኅበረሰብ ጋር አብረው “አባታችን ሆይ!” ጸሎት ካደረሱ በኋላ ተቋሙን በመጎብኘት እና ከሠራተኞቹ ጋር ሰላምታ ሲለዋወጡ ከቆዩ በኋላ ከጠዋቱ አምስት ሰዓት ተኩል በፊት ወደ መኖሪያቸው ተመልሰዋል።

 

22 Jul 2025, 16:51