ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14፥ “ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያነት መጠቀም አይገባም!” ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት (FAO) 44ኛ ጉባኤውን በሮም ከሰኔ 21-27/2017 ዓ. ም. ድረስ በማካሄድ ላይ ሲሆን፥ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመዋጋት የተቋቋመበትን 80ኛ ዓመትንም በማክበር ላይ ይገኛል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለጉባኤው ተሳታፊዎች በላኩት መልዕክት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮውን ለማዳመጥ የመጡትን ሰዎች በመመገብ ያደረገውን እንክብካቤ በማስታወስ፣ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና ግብርና ድርጅት ዓለም አቀፍ ረሃብን ለማስወገድ የሚደረገውን ጥረት ቤተ ክርስቲያን እንደምትደግፍ አስታውቀዋል።
“ኢየሱስ ክርስቶስ የፈጸመው እውነተኛ ተዓምር ረሃብን ማሸነፊያ ዋና መንገድ ነው” ብለው፥ ስግብግብነት ሳይሆን ነገር ግን ምንም ከሌላቸው ጋር መካፈል አስፈላጊ መሆኑን በማሳሰብ በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች የተትረፈረፈ እህል ቢኖርም ረሃብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በመቀጠሉ ብዙ ሰዎች ዛሬም በስቃይ ውስጥ ሆነው ፍላጎታቸው እንዲሟላላቸው እንደሚፈልጉ አስረድተዋል።
“ረሃብን እንደ ጦር መሣሪያነት መጠቀምን በጥልቅ ሐዘን እየተመለከትን እንገኛለን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ሲቪሉን ሕዝብ ማስራብ ጦርነትን ለማካሄድ በጣም ርካሹ መንገድ ነው” ብለዋል።
አብዛኞቹ ግጭቶች በአሁኑ ጊዜ በመደበኛ ጦር ሠራዊት ሳይሆን በታጠቁ ሲቪል ቡድኖች የሚካሄዱ መሆናቸውን ገልጸው፥ እንደ ሰብል ማቃጠል እና ሰብዓዊ ዕርዳታን መከልከል የመሳሰሉ ስልቶች ተከላካይ በሌላቸው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረባቸው ጠቁመዋል።
ግጭት ሲቀሰቀስ አርሶ አደሩ ምርቱን መሸጥ ባለመቻሉ የዋጋ ንረት እየጨመረ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ለረሃብ እና ለምግብ እጦት የሚዳርግ በመሆኑ፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወንጀለኞች እንዲጠየቁ የማድረግ እርምጃን እንዲወስድ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ አሳስበዋል።
“የፖለቲካ ቀውሶች፣ የትጥቅ ግጭቶች እና የኢኮኖሚ ውድቀቶች የምግብ ቀውሱን በማባባስ ረገድ ማዕከላዊ ሚናን ይጫወታሉ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ግጭቶች ሰብዓዊ እርዳታን ያደናቅፋሉ፣ የአካባቢውን የግብርና ምርት ያበላሻሉ፤ እንዲሁም የሰዎችን የምግብ አቅርቦት ብቻ ሳይሆን የተከበረ ሕይወት የመምራት መብትንም ይነጥቃሉ” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው አክለውም፥ ራስ ወዳድነት እና ግዴለሽነት ተወግደው የጋራ ውይይት እና መግባባት ሊኖር እንደሚገባ አሳስበው፥ “በዚህ መንገድ የሚመጣ ሰላም እና መረጋጋት ማኅበረሰቦች አስተማማኝ የግብርና ሥርዓቶችን እንዲገነቡ ያስችላቸዋል” ብለዋል።
በተመሳሳይም የአየር ንብረት ለውጥ እና የምግብ ሥርዓቶች በቅርበት የተሳሰሩ እንደሆኑ፥ ይህ ማለት የአንዱ መቃወስ ሌላውን በእጅጉ እንደሚነካ ታውቋል።
“በተፈጥሮ አደጋዎች እና በብዝሃ ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሚደርሰው ማኅበራዊ ኢ-ፍትሃዊነት መቀልበስ አለበት” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ይህም አካባቢን እና ሕዝቦችን ማዕከል ያደረገ ፍትሃዊ የሥነ-ምህዳር ሽግግር እንዲኖር ያስፈልጋል” ብለዋል።
ሁሉም ሰው የምግብ ዋስትና እና የተመጣጠነ ምግብ ዋስትና እንዲኖረው የዓለማችን ሃብቶች በሥራ ላይ መዋል ስላለባቸው፥ ሥነ-ምህዳሮችን በተቀናጀ የአየር ንብረት እርምጃ በአብሮነት መንፈስ እንዲጠበቁ ጠይቀዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የፋይናንሻል ሃብቶች እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወደ ጦር መሣሪያ ማምረቻነት እና ወደ ጦር መሣሪያ ንግድ እየተለወጡ መሆኑን በምሬት ተናግረው፥ አጠያያቂ አስተሳሰቦች ሲበራከቱ እና በሰዎች መካከል የእርስ በእርስ ግንኙነት እየቀዘቀዘ ሲሄድ ኅብረት መንምኖ ወንድማማችነት እና ማኅበራዊ ወዳጅነት ይጠፋል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ የሽንገላ ንግግሮችን ወደ ጎን በመተው ሁሉም ሰው ረሃብን ለማስወገድ በሚጥር ጠንካራ የፖለቲካ ፍላጎት እንዲሳተፍ እና የሰላም ገንቢ እንዲሆን ጋብዘው፥ ይህን የተከበረ ዓላማ ለማሳካት በሕዝቦች መካከል መግባባትን በማሳደግ እና በተለይም እጅግ የተጎዱትን፣ በረሃብ እና በጥማት የሚሰቃዩትን በተመለከተ ለሕዝቦች የጋራ ጥቅም አስተዋጽኦ ለማድረግ ቅድስት መንበር የማትታክት መሆኗን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ” ብለዋል።