ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ ፓስካል ሞት የሐዘን መግለጫ መልዕክት ላኩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የካፑቺን ፍራንችስካውያን ወንድሞች ማኅበር አባል የነበሩት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ፓስካል ድሪ፥ በላቲን አሜሪካ አገር አርጀንቲና መዲና በቦነስ አይረስ የተወለዱ ሲሆን፥ በ98 ዓመት ዕድሜያቸው ሰኔ 23/2017 ዓ. ም. አርፈዋል።
ነፍስሔ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ አባ ሉዊስ ፓስካል ድሪ፥ የአርጄንቲና ከተማ በሆነች ፔስኬራ ቅዱስ አንጄሎ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በማገልገል ላይ እያሉ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2023 ዓ. ም. የካርዲናልነት ማዕረግ መስጠታቸው ይታወሳል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፣ ረቡዕ ሰኔ 25/2017 ዓ. ም. የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ የሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የፈረሙበትን የሐዘን መግለጫ የቴሌግራም መልዕክታቸውን ለቦይነስ አይረስ ሊቀ ጳጳስ ለአቡነ ጆርጅ ኢግናስዮ ጋርሺያ ልከዋል።
ቅዱስነታቸው በካርዲናል ሉዊስ ፓስካል ድሪ ዕረፍት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸው፥ ለዘመዶቻቸው እና ለፍራንችስካውያን ካፑቺን ወንድሞችም መጽናናትን ተመኝተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሐዘን መግለጫ መልዕክታቸው ላይ፥ ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ፓስካል ድሪ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወደ ኋላ የማይሉ በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እጅግ የተከበሩ፣ በሕይወታቸው ለብዙ ዓመታት እግዚአብሔርን እና ቤተ ክርስቲያንን በማገልገል የሰዎችን ኑዛዜ የሚሰሙ መንፈሳዊ መሪ ነበሩ” በማለት ገልጸዋቸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሟቹ ካርዲናል ሐዘን ለተሰማቸው በሙሉ፥ ለነፍሳቸው ዘላለማዊ ዕረፍት ጸሎት እንዲያቀርቡ እና ጌታ እግዚአብሔር የማይጠፋ የክብር አክሊል እንዲሰጣቸው ጸሎት እንደሚያቀርቡ አረጋግጠውላቸዋል።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ብፁዕ ካርዲናል ድሪን እንደ ምህረት አብነት በመጥቀስ፥ ሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር የሚታረቁበትን ምስጢር በማደል ላበረከቱትን አገልግሎት ማድነቃቸው ይታወሳል።
በአርጄንቲና ውስጥ የተወለዱት ካርዲናል ሉዊስ ፓስካል ድሪ፥ ኑዛዜን በማስገባ ለበርካታ ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ኢየሱስን፥ “ጌታ ሆይ! ብዙ ይቅር በማለቴ እኔንም ይቅር በለኝ” ይሉ እንደ ነበር ተነግሯል።
ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ፓስካል ድሪ አርጀንቲና ውስጥ ፌዴራሲዮን በተባለ አካባቢ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሚያዝያ 17/1927 ዓ. ም. ከጠንካራ ካቶሊካዊ ቤተሰብ የተወለዱ ሲሆን፥ ከ9 ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው መካከል 8ቱ የገዳም ሕይወት የመረጡ እንደሆነ ታውቋል።
ሚስዮናዊ እና መንፈሳዊ መሪ ሆነው ያገለገሉት ብጹዕ ካርዲናል ሉዊስ ፓስካል ድሪ፥ ሐዋርያዊ አገልግሎታቸው የተቀረፀው በቅዱስ ፓድሬ ፒዮ እና በቅዱስ ሊዮፖልድ ማንዲች ምሳሌዎች እንደሆነ ታውቋል።
ካርዲናል ሉዊስ ፓስካል ድሪ በአንድ ወቅት ስለ ሕይወታቸው ሲያሰላስሉ፥ “እኔ ዲግሪ የለኝም፣ የትምህርት ማዕረግ የለኝም። ሕይወት ግን ብዙ አስተምሮኛል፤ በጣም ድሃ ሆኜ በመወለዴ ዘወትር የምሕረት፣ የዕርዳታ እና የመቀራረብ ምክሮችን እንዳቀርብ እንደተጠራሁ ይሰማኛል። እነዚህን ምክሮቼን ማንም ሳይረዳቸው ወይም ሳይቀበላቸው እንደሄድ ማሰብ የለበትም” ማለታቸውም ይታወሳል።