ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሁለት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስጦታ ተቀበሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በውጭ አገር በሚያደርጓቸው ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ወቅት እንዲረዳቸው ተብሎ የተሠሩ ሁለት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስጦታነት ተቀብለዋል።
በጣሊያን ኤክሌንሲያ የተባለ ኩባንያ ከቫቲካን ግዛት የጸጥታ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር የተሠሩት እነዚህ ተሽከርካሪዎች መበታተን ሳያስፈልጋቸው በረጅም ርቀት በረራዎች እንዲጓጓዙ ተደርገው የተሠሩ ናቸው።
የልገሳው ዜና የተሰማው ቫቲካን ሰኔ 29/2017 ዓ. ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሆን፥ በተሽከርካሪዎቹ ሥራ የተከናወነው፥ በምህንድስና ዲዛይን ውህደት፣ በፍተኛ የሜካኒካል፣ የኤሌክትሮኒክስ፣ የማኑፋክቸሪንግ እና የእጅ ጥበብ ተሳትፎ መሆኑን መግለጫው ገልጿል።
መግለጫው አክሎም፥ እነዚህ ሁለቱም ተሽከርካሪዎች የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ፍላጎቶች በሚያሟላ መንገድ የተሠሩ መሆናቸውን አስረድቶ በተለይም የሞቴር ሥራው፣ የፊት ለፊት እጀታ እና ከዋና መደገፊያው በታች በኩል ያሉ የጎን መደገፊያዎች ታክለውበት እና ደህንነቱን የጠበቀ የእጅ መያዣ እንዲሁም ተሽከርካሪው ላይ ሲወጡ እና ሲወርዱ የተሻለ ምቾት እንዲኖር ተደርጎ የተሠራ መሆናቸውን መግለጫው አስታውቋል።
የቫቲካን ግዛት የጸጥታ አስከባሪ አካላት የፕሮጀክቱን እያንዳንዱን ምዕራፍ በመቆጣጠር ማዕከላዊ ሚናን የተጫወተ ሲሆን፥ ዓላማውም ከፍተኛ ምቾት እና ደኅንነት ለማረጋገጥ፥ በተለይም ተሽከርካሪዎቹ በዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ወቅት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የተሠሩ መሆናቸው ታውቋል። በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ተሳታፊ የሚሆነው የጣሊያን አየር መንገድም የአየር ትራንስፖርት ቴክኒካዊ መስፈርቶችን በመግለጽ በፕሮጀክቱ ላይ መተባበሩ ታውቋል።
ተሽከርካሪዎቹ በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ውስጥ ሰኔ 26/2017 ዓ. ም. በተካሄደው የግል መስተንግዶ ላይ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በስጦታነት ቀርበዋል።