MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የሕይወት ምርጫን በማስተዋል ማድረግ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ምዕመናን እንዲተባበሯቸው የፈለጉትን የጸሎት ሃሳብ በዓለም አቀፉ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ በኩል ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት ይፋ አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ለሐምሌ ወር እንዲሆን በማለት ባቀረቡት የጸሎት ሃሳብ፥ ለሕይወታችን ትክክለኛ የሆነውን መንገድ መምረጥ እንድንችል እና ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚለየንን ማንኛውንም ነገር መቃወም እንድንችል መጸለይ እንደሚገባ ጋብዘውናል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“የሕይወት መንገዶችን መምረጥ እና ከኢየሱስ ክርስቶስ እና ከቅዱስ ወንጌሉ የሚያርቀንን ነገር በሙሉ ላለመቀበል የማስተዋል ችሎታን ለመማር እንጸልይ” ብለዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ይህን ግብዣ ያቀረቡት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የቪዲዮ መልዕክት አማካይነት ለሐምሌ ወር 2017 ዓ. ም. ባቀረቡት የጸሎት ሐሳብ እንደሆነ ታውቋል።

ቅዱስ አባታችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በዓለም አቀፍ የጸሎት አውታረ መረብ በኩል ካቀረቡት የቪዲዮ መልዕክት ጋር ክርስቲያኖችን በአስተዋይነት ሂደታቸው የሚያግዛቸውን ጸሎትንም ያቀረቡ ሲሆን፥ መንፈስ ቅዱስ ውሳኔዎቻችንን እንዲያሳውቅ እና የእግዚአብሔርን ድምፅ በትኩረት ማዳመጥን እንድንማር ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

“በምናዳምጥበት ጊዜ ልባችን ውስጥ ያለውን የተሰወረ መንገድ ለይተን ማወቅ እና በእግዚአብሔር ዘንድ አስፈላጊ የሆነውን ነገር መረዳትን እንማራለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የሕይወት አካሄዳችንን፣ የውስጥ ስሜቶቻችንን እና የሚያስጨንቁንን ነገሮችን ለማወቅ፥ ቆም ማለትን የሚያስተምር ጸጋ እንዲሰጠን እግዚአብሔርን በጸሎት ጠይቀዋል።

“ምርጫችን ከቅዱስ ወንጌል ወደሚገኝ ደስታ ሊመራን ይገባል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ምንም እንኳን የጥርጣሬ እና የድካም ጊዜያት ቢኖሩም ዘወትር እንደ አዲስ ለመጀመር እንፈልጋለን” በማለት ብርታትን ተመኝተው፥ “በጉዞአችን መጨረሻ የምጽናናው፥ ትክክለኛ ውሳኔያችን በሚያስገኝልን ፍሬ ነው” ሲሉ አረጋግጠዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጸሎታቸው ማጠቃለያ፥ “ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚያርቀንን ነገር ውድቅ አድርገን እሱን የበለጠ እንድወደው እና እንዳገለግለው የሚያግዘንን ጸጋ ለማወቅ እግዚአብሔር ይርዳን” ብለዋል።

ማስተዋልን ማሳደግ እና ፈተናን መቃወም

ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት የቪዲዮ መልዕክት ጋር አብሮ የወጣው ጋዜጣዊ መግለጫው፥ እያንዳንዱ ሰው እንዳያስተውል ወይም በፍርሃት እንዲያዝ የሚያደርጉ በሕይወት ውስጥ ማለቂያ የሌላቸው አጋጣሚዎች መኖራቸውን አስታውሷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የማስተዋልን ጸጋ በጠየቁበት የጸሎት ሃሳባቸው፥ በልባችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ድምጽ በጥልቅ በማዳመጥ ለሕይወታችን ትክክለኛውን መንገድ መምረጥ የምንችልበትን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠን መጠየቃቸውንም መግለጫው አክሏል።

ጫካ ውስጥ መንገድ ጠፍቶባት የምትፈልገውን አንዲት ወጣት የሚያሳየው የቪዲዮ ቅንብሩ፥ ወጣቷ የምትሄድበትን መንገድ መፈለግ ስትጀምር ራሷን ከችግር ነፃ በማድረግ እርምጃዋን የሚመራ ጠቋሚ ማግኘቷን ያሳያል። የቪዲዮ ቅንብሩ አክሎም፥ ወጣቷ ቅዱስ ወንጌልን ለማበብ ከከፈተች በኋላ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል ወዳለበት ዋሻ ውስጥ ገብታ የሕይወት መመሪያን ለማግኘት በጽሞና ጸሎት ማቅረቧን ያሳያል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የመጀመሪያ ጸሎት፥ ቅዱስ አጎስጢኖስን በኑዛዜው ውስጥ፥ “አምላኬ ሆይ! አንተን ለማወቅ ራሴን እንዳውቅ አድርገኝ!” በማለት ያቀረበውን ጸሎት የሚያስተባ መሆኑ ተመልክቷል።

ጋዜጣዊ መግለጫው በማከልም፥ “በእግዚአብሔር ፊት ራስን በእውነት ማስቀመጥ፣ ወደ ራስ መመለስ፣ ድክመትን አምኖ መቀበል እና እግዚአብሔር እንዲፈውስ መጠየቅ አስፈላጊ ነው” ሲል ገልጾ፥ እነዚህ እርምጃዎች ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ትክክለኛ ግንኙነት ዳግም እንድንወለድ የሚያግዙን ናቸው” ሲል አስረድቷል

“ይህ ሂደት ‘ማስተዋል’ በመባል ይታወቃል” ያለው መግለጫው፥ ክርስቲያኖች ወደ እግዚአብሔር ዘንድ የሚወስዳቸውን መንገድ እንዲያውቁ የሚረዳቸው፥ በዕለታው ተግባራት ውስጥ የተለማመድናቸው እና ቀድሞውኑ በልባችን ውስጥ የሚገኝ መሆኑንም አስታውሷል።

አባ ክሪስቶባል ፎኔስ፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት አውታረ መረብ ዳይሬክተር በመግለጫው ላይ፥ እያንዳንዳችን ማስተዋልን በደንብ መማር እንደሚገባ በማብራራት እና በእርሱ መመራት እንዳለብን ተናግረዋል።

በማስተዋል ማደግ፥ ጸሎትን፣ ግላዊ ማሰላሰልን፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን እና መንፈሳዊ መመሪያዎችን ማጥናትን እንደሚያካትት እና ከሁሉም በላይ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ጥልቅ ወዳጅነት መመሥረት አስፈላጊ ነው” ሲሉ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከእግዚአብሔር ዘንድ ማስተዋልን ሲጠይቁ፥

“የማስተዋል ብርሃን የሆንክ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ውሳኔዎቻችንን በለስላሳ እስትንፋስ የምትመራ፣ ድምጽህን በጥሞና እንድሰማው ፀጋህን ስጠን። የተሰወረውን የልባችንን መንገድ እንድንመለከት፣ ላንተ ተገቢ የሆነውን በትክክል እንድገነዘብ እና ልባችንን ከመከራ እንድናድን አግዘን።

አካሄዴን ለማወቅ፣ እኔ የማላስተውላቸው፥ ነገር ግን በውስጤ ያሉ የሚያስጨንቁኝን ሃሳቦች እና ስሜቶች ቆም ብዬ እንዳስብ የሚያስተምር ጸጋን እንድትሰጠኝ እለምናለሁ። ወደ ቅዱስ ወንጌል ደስታ የሚመሩ ምርጫዎችን እናፍቃለሁ። ምንም እንኳን በጥርጣሬ እና በድካም ውስጥ ማለፍ ቢኖርብኝም፥ ዘወትር ወደ አንተ ለመድረስ መጣርን፣ እንተን ማሰላሰልን እና መፈለግን እንደገና መጀመርን አስተምረኝ።

ምክንያቱም በጉዞዬ መጨረሻ ላይ ያንተ ማጽናናት የትክክለኛ ውሳኔዬ ውጤት ነውና። ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚያርቀኝን ነገር እንድንቅ የሚቀሰቅሰኝን፣ እርሱን ይበልጥ የምወድበትን እና የማገለግልበትን ጥልቅ ግንዛቤ ስጠኝ፤ አሜን!” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

 

09 Jul 2025, 16:39