ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ጋዛ ውስጥ ተኩስ እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቅድስት ሀገር አስከፊ ጦርነት እየተካሄደ ባለበት በዚህ ወቅት፥ ርዕሥ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ዓርብ ሐምሌ 11/2017 ዓ. ም. በስልክ ተነጋግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጋር ባደረጉት ንግግር፥ በጋዛ ድርድር እና የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ ማቅረባቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል አስታውቋል።
በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ውስጥ ሆነው ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር በስልክ የተነጋገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ሐሙስ ሐምሌ 10/2017 ዓ. ም. የእስራኤል ጦር በጋዛ በሚገኘው በቅድስት ቤተሰብ ካቴድራል ላይ ባካሄደው ወታደራዊ ጥቃት የሦስት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን እና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን በማስመልከት ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር መነጋገራቸውን ጽሕፈት ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል።
መግለጫው አክሎም፥ ቅዱስ አባታችን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በውይይታቸው ወቅት፥ ዳግመኛ ድርድር እንዲደረግ፣ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ ጦርነቱ እንዲቆም በድጋሚ ጥሪ ማቅረባቸውን አስታውቋል።
መግለጫው ከዚህም በላይ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ልጆቻቸው፣ አረጋውያን እና ሕሙማን ከባድ ዋጋ እየከፈሉ የሚገኝበት የጋዛ ሕዝብ አሳዛኝ ሰብዓዊ ሁኔታ እንደሚያሳስባቸው በድጋሚ መናገራቸውን አስታውቋል።
መግለጫው በመጨረሻም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የአምልኮ ቦታዎችን እና በተለይም በፍልስጤም እና በእስራኤል ውስጥ የሚገኙ ምእመናን እና የመላውን ሕዝብ ድኅንነት የመጠበቅ አስፈላጊነትን በማስመልከት በድጋሚ መናገራቸውን አስታውቋል።
በጋዛ የሚገኘው የቅድስት ቤተሰብ ካቴድራል ብቸኛው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሲሆን፥ ሐሙስ ሐምሌ 10/2017 ዓ. ም. ማለዳ በእስራኤል ጦር በተፈጸመው ጥቃት የቁምስናው መሪ ካህን አባ ገብርኤል ሮማኔሊን ጨምሮ አሥር ሰዎች ሲቆስሉ ሦስት ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።
በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት በመግለጫው፥ “ይህን በሰውም ሆነ በሥነ-ምግባር ኢ-ፍትሐዊ የሆነውን ድርጊት ለመግታት መሪዎች ድምፃቸውን እንዲያሰሙ እና አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉ” በማለት ጥሪውን አቅርቧል።