ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ጥቃት ለተፈጸመባቸው የጋዛ ምዕመናን ያላቸውን ቅርበት ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ፥ ከግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ቴዎፍሎስ 3ኛ ጋር በመሆን፥ የእስራኤል ጦር ጥቃት የፈጸመበትን በጋዛ የሚገኝ ብቸኛውን የቅድስት ቤተሰብ ካቶሊካዊ ቁምስናን ዓርብ ሐምሌ 11/2017 ዓ. ም. ጎብኝተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ሁለቱ የአብያተ ክርስቲያናቱ መሪዎችች ወደ ሥፍራው ሲደርሱ ከፓትርያርክ ፒሳባላ ጋር ባደረጉት የመልዕክት ልውውጥ፥ ጥቃቱ ለተፈጸመባቸው የቁምስናው ምዕመናን ያላቸውን ቅርበት ገልጸው፥ በጸሎት በማስታወስ፥ እንክብካቤን እና ድጋፍን በማድረግ እንዲሁም ተኩስ እንዲቆም ጥሪ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ይህ አሳዛኝ ክስተት እንዲቆም የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ሲናገሩ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ግድያው የሚቆምበት ጊዜ አሁን ነው፤ የተፈጸመው ነገር ፍትሃዊ አይደለም፤ ከዚህ በኋላ ተጎጂዎች እንዳይኖሩ ማረጋገጥ አለብን” በማለት ደጋግመው መናገራቸውን አስረድተዋል።
በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ፥ በሁሉም የቅድስት ሀገር አብያተ ክርስቲያናት ስም ባደረጉት ንግግር፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ቀደም ሲል ላደረጉት ትብብር እና ላረጋገጡላቸው የጸሎት ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ያሳሰባቸው የጋዛ ሁኔታ
የእስራኤል ታንኮች ሐሙስ ዕለት በጋዛ በሚገኝ የቅድስት ቤተሰብ ካቴድራል ላይ በከፈቱት ተኩስ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ የካቴድራሉን መሪ ካኅን አባ ገብርኤል ሮማኔሊን ጨምሮ አሥር ሰዎች መቁሰላቸው ታውቋል።
የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት ከተጀመረበት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 2023 ዓ. ም. አንስቶ፣ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየቀኑ ማለት ይቻላል ከአባ ገብርኤል ጋር በስልክ ይገናኙ እንደነበር ይታወሳል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በጋዛ ለምትገኘው ብቸኛ ካቶሊካዊ ቁምስና ሐሙስ ሐምሌ 10/2017 ዓ. ም. በላኩት መልዕክት፥ ተጎጂዎችን እና በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙትን በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠው፥ ፈጣን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ በማቅረብ፥ በቀጣናው ውይይት በማድረግ፣ እርቅ እና ዘላቂ ሰላም እንደሚገኝ ጥልቅ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ወደ ጋዛ የተደረገ የአንድነት መግለጫ ጉብኝት
የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ማለትም የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ እና የግሪክ ኦርቶዶክስ ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ቴዎፍሎስ 3ኛ፥ ጥቃቱ የተፈጸመበትን ቁምስና ዓርብ ሐምሌ 11/2017 ዓ. ም. በጎበኙበት ወቅት፥ በቅርቡ በተፈጸሙት ጥቃቶች ከተጎዱት ጎን እንደሆኑ መናገራቸውን በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት መግለጫ አስታውቋል።
የሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች፥ የመጀመሪያ ሕክምና መስጫ መሣሪያዎች እና በመቶ ቶን የሚቆጠር የምግብ ዕርዳታን ለማግኘት ከሰብዓዊ ዕርዳታ ሰጭ አጋር ድርጅቶች ጋር የሠሩ ሲሆን፥ ይህም ለክርስቲያኑ ማኅበረሰብም ሆነ ለሌሎች የጋዛ ነዋሪዎች ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል።
የፓትርያርኩ ጽሕፈት ቤት እንደገለጸው፥ በጥቃቱ የተጎዱት ከጋዛ ውጭ ሕክምናን ወደሚያገኙባቸው ተቋማት መውሰዳቸውን በመግለጫው አረጋግጦ በማከልም፥ ለሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ደህንነት ጸሎት እንዲደረግ አሳስቦ፥ በሥፍራው የሚታየው ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዲቆምም ጠይቋል።
በኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት፥ ለክርስቲያን ማኅበረሰብ እና በአካባቢው ለሚገኝ መላው የጋዛ ሕዝብ ባለው ቁርጠኝነት የጸና መሆኑን አስታውቆ፥ ነዋሪውን እንደማይረሳ እና ብቻውን እንደማይተወው አረጋግጧል።
የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በአምልኮ ሥፍራ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አወገዙ
በኢየሩሳሌም የሚገኙት የሃይማኖት አባቶች እና የአብያተ ክርስቲያናት ሃላፊዎች በተናጠል ባወጡት መግለጫ፥ በጋዛ ካቶሊካዊ ቁምስና ውስጥ ተጠልለው ከሚገኙት ወገኖች ጋር ያላቸውን የጋራ አጋርነት ገልጸዋል።
የአብያተ ክርስቲያናቱ ሃላፊዎች አክለውም፥ “በማይናወጥ አንድነት ይህንን ወንጀል አጥብቀን እናወግዛለን” ብለው፣ የአምልኮ ቤቶች ደኅንነታቸው ሊጠበቁ የሚገባቸው ቅዱስ ቦታዎች እና እንዲሁም በዓለም አቀፍ ሕግም የተጠበቁ ናቸው” ብለዋል። “ልዩ እንክብካቤ የሚያሻቸው ሕጻናትን ጨምሮ ወደ 600 የሚጠጉ ስደተኞች ባሉበት ቤተ ክርስትያን ላይ ማነጣጠር ዓለም አቀፍ ሕጎችን መጣስ እና ይህም ደግሞ የሰውን ልጅ ክብር የሚነካ፣ የሰውን ሕይወት ቅድስና የሚረግጥ እና የተቀደሰ ቦታን የሚያራክስ ተግባር ነው” ብለዋል።
የአብያተ ክርስቲያናቱ ሃላፊዎች በጋዛ የሚገኙትን ማኅበረሰቦች በጸሎታቸው እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠው፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በጋዛ አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት ተደርጎ ጦርነቱን እንዲያስቆም ጠይቀዋል።
ሃይማኖታዊ እና ሰብዓዊ ተቋማት በሙሉ ከጥቃት የሚተርፉበትን ዋስትና እንዲሰጣቸው እና እንዲሁም በመላው የጋዛ ሰርጥ ለተራበው ሕዝብ እፎይታን እንዲያገኙላቸው ተማጽነዋል።