ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ከጠፈር ተመራማሪው ቡዝ አልድሪን ጋር በስልክ ተወያዩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የዛሬ 56 ዓመት ጨረቃን በመርገጥ ምድር ምን እንደምትመስል በዓይኑ ከተመለከተ ሁለተኛው ሰው ቡዝ አልድሪን ጋር በስልክ መልዕክት ተለዋውጠዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛም የሰማያትን ውበት በቴሌስኮፕ ከተመለከቱ በኋላ የተናገሯቸው ቃላት ስለ ፍጥረት ምስጢራዊነት፣ ታላቅነት እና ደካማነት ያሰላሰሉበት እንደ ነበር ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የእስራኤል ጦር ጋዛ ውስጥ በሚገኝ የቅድስት ቤተሰብ ካቴድራል ላይ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ የጦርነት አረመኔያዊ ድርጊት እንዲያቆም፣ ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈልግ፣ የሰብዓዊነት ሕግን ማክበር እንደሚገባ፣ ሲቪሎችን ከአደጋ የመጠበቅ ግዴታ እንዲከበር፣ የጋራ ቅጣት እንዲያቆም፣ ኃይልን ያለ አግባብ መጠቀም እና ዜጎችን ማፈናቀል እንዲያበቃ በማለት ልባዊ ጥሪ ማቅረባቸውን ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ገልጸዋል።
ጋዛ ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈጸመው ወረራ የተገደሉትን ሦስት ሰዎች አንድ በአንድ በስም መጥቀስ ክርስቲያን በመሆናቸው ሳይሆን እያንዳንዱ ሕይወት እንደማንኛውም የአምልኮ ሥፍራ ቅዱስ መሆኑን ለማረጋገጥ፥ የጅምላ ግድያ ሰለባ ለሆኑት ሌሎች ንጹሃን ሰዎችም ስም ለመስጠት እና በየቀኑ በቁጥር ብቻ የሚገለጽ እያንዳንዱ ተጎጂ ስም እና ታሪክ እንዳለው ለማስታወስ መሆኑን አክለው አስረድተዋል።
እነዚያ የአደጋ ጊዜያት እንደ ቅብ ሥዕሎች አንዳቸው ከሌላው የተለዩ መሆናቸውን የተናገሩት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ በጊዜ እርከን የሚቀራረቡ ቢሆንም ነገር ግን የተለያዩ መሆናቸውን ገልጸው፥ የሰላምን ታላቅነት እና የጦርነትን ትርጉም የለሽነት የሚናገሩ መሆናቸውን በማስረዳት፥ በምልክት፣ በምስሎች እና በቃላት አማካይነት የሚደረጉ ግንኙነቶች ጦር መሣሪያን እንዴት ማስታጠቅ እና ማስፈታት እንደሚችሉ አብራርተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከቡዝ አልድሪን ጋር ያደረጉት የስልክ ውይይት በተወሰነ ቅጽበት ወደ ጸሎትነት መቀየሩን ያስታወሱት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ስለ ሰማይ፣ ስለ ጨረቃ፣ ስለ ከዋክብት እና ከዚያም ስለ ሰው ልጅ በመናገር የእግዚአብሔርን ሥራ ታላቅነት ከሚናገረው ከመዝ. 8 ጋር የሚመሳሰል መሆኑን አስረድተዋል።
“የተነገሩት እና ያልተነገሩት፣ የተደረጉት እና ያልተደረጉት ነገሮች፥ እያንዳንዳችንን በኃላፊነት በፊት ለማስቀመጥ ጥቂት ቃላት እና ጥቂት ምስሎች በቂ ናቸው” ሲሉ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ አስረድተዋል።
ይህንን ለመገንዘብ ትንሽ ቆም ብሎ እንደገና ለመጀመር ጥቂት ጊዜን እንደሚወስድ የተናገሩት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ ማንም ሰው የያዘው እውነት ወይም የተቀበለው መከራ የንጹሃን ሰው ሕይወት መጥፋት ትክክለኛነት ለማረጋገጥ ፍፁም እና በቂ ነው ብሎ ማመን እንደማይቻል አስረድተዋል።
ምክንያቱም የሰውን ክብር መጣስ እኛን በአምሳሉ የፈጠርን እግዚአብሔርን ማስከፋት፣ ሁላችን የተወለድንበትን ታሪክ መካድ እና የጋራ መኖሪያ ምድራችን ድንቅ ፍጥረትን ማጥፋት እንደ ሆነ አስረድተዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያን በ2013 የኦስካር ሽልማት አሸናፊ “ግራቪቲ” በሚል ፊልም ላይ የተሳተፉት ሁለት ጠፈርተኞች ምድርን ከጠፈር ሆነው በአድናቆት ከተመለከቱ በኋላ አንዱ ሌላውን፥ “ድንኳንህን የት ነው የተከልከው?” ሲል መጠየቁን ያስታወሱት ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ፥ በዮሐንስ ወንጌል መቅድም ላይ የእግዚአብሔር ቃል “ድንኳኑን በመካከላችን ተከለ” በማለት የተናገረራቸው ኃይለኛ ቃላት እንደሆኑ አስረድተዋል።
ይህች በጦርነት የተበታተነች እና በተስፋ ቃል የበለጸገች ትንሽዬ ፕላኔታችን በፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ እንደተጻፈው፥ እግዚአብሔር ራሱ በውስጧ ሊኖር እና ሊቤዣት የመረጣት ስለሆነ ጦርነቶች ሊያፈርሷት ቢቃጡም እንደማትሸነፍ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ ዶ/ር ፓውሎ ሩፊኒ ገልጸዋል።