ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከልጆች ጋር በመነጋገር ግንኙነትን መገንባት እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ዓርብ ሰኔ 27/2017 ዓ. ም. በቫቲካን ካገኟቸው አዳጊ ሕፃናት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ “በልጅነት ዕድሜ እንኳን ቢሆን እርስ በእርስ የምንገናኝበትን መንገድ መገንባት መማር እና ሌሎችን የምንረዳባቸውን ዕድሎች መፈለግ እንችላለን” ብለው፥ አክለውም ልጆች በመስዋዕተ ቅዳሴ ላይ በመገኘት፣ ሌሎችን እንደራሳቸው በመቀበል፣ ሰላምን ለመገንባት በመጣር ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወዳጅነትን ለመፍጠር እንዲተጉ አበረታትተዋ።
ቫቲካን በሚያስተባብረው ዓመታዊ የበጋ ወቅት የዕረፍት ጊዜ መርሃ ግብር ላይ የሚሳተፉት ከ300 በላይ ልጆች በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ጋር የተገናኙት ዓርብ ሰኔ 27/2017 ዓ. ም. እኩለ ቀን ላይ ሲሆን፥ ከዚያ ጥቂት ቀደም ብሎ በካሪታስ ኢጣሊያ አስተናጋጅነት ከዩክሬን የመጡ ወደ ሦስት መቶ የሚሆኑ ሌሎች ልጆች ጋር ተገናኝተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከተለያዩ የዕድሜ ክልሎች ከተወጣጡ ሦስት ሕጻናት ለቀረቡላቸው ሦስት ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ውይይት አድርገዋል። ቫቲካን የሚያስተባብረው ይህ ዓመታዊ ዝግጅት ስድስተኛ ዓመቱን እንደያዘ የተገለጸ ሲሆን፥ አስተባባሪው የቅዱስ ጆን ቦስኮ ሳሌዥያዊ ካኅን አባ ፍራንኮ ፎንታና ሲሆኑ፥ ለቅዱስ ጆን ቦስኮ የወጣቶች ማዕከላትም በተመሳሳይ መልኩ ዝግጅቶችን እንደሚያስተባብሩ ታውቋል።
ለልጆች ለበጋ ወቅት ዝግጅት የቀረበ የውይይት ጭብጥ፥ ሕጻናት ከሌሎች ጋር ማውራት፣ መገናኘት እና ቃላትን፣ ሃሳቦችን እና የጨዋታ ጊዜን ከሌሎች ጋር ማሳለፍ በጣም አስቸጋሪ እየሆነ በመጣበት ጊዜ ጭፍን ጥላቻን እንዲያሸንፉ መርዳት የሚቻልበት መንገድ የሚመለከት እንደሆነ ታውቋል።
መስዋዕተ ቅዳሴን እንደ ልጅ መካፈል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በልጅነታቸው መስዋዕተ ቅዳሴን ለመካፈል ይሄዱ እንደሆን ለቀረበላቸው የመጀመሪያ ጥያቄ፥ “አዎን በእርግጥ! ዘወትር በእያንዳንዱ እሁድ ከእናታቸው እና ከአባታቸው ጋር እሄድ ነበር” በማለት በጋለ ስሜት መልሰዋል። ቀጥለውም ከልጅነት ጀምሮ የነበራቸውን የቺካጎ ትዝታዎችን ሲያካፍሉ፥ በስድስት ዓመታቸው አካባቢ በቁምስናቸው ውስጥ የመንበረ ታቦት ላይ አገልጋይ እንደ ነበሩ፥ ወደቁምስናቸው ትምህርት ቤት ከመሄዳችን በፊት ከጠዋቱ በአሥራ ሁለት ሰዓት ተኩል መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚሳተፉ፥ እናታቸው ዘወትር ወደ መስዋዕተ ቅዳሴ ለመሄድ እንደሚቀሰቅሷቸው እና በመስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ማገልገል እጅግ ያስደስታቸው እንደ ነበር በማስታወስ፥ ከልጅነታቸው ጀምሮ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ቅርብ እንደሆነ፣ የቅርብ ጓደኛ እንደሆነም ያስተምሯቸው እንደ ነበር እና መስዋዕተ ቅዳሴ ያንን ጓደኛ የሚያገኙበት መንገድ እና ምስጢረ ቁርባን ከመቀበላቸው በፊትም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የሚሆኑበት መንገድ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚያን ጊዜ መስዋዕተ ቅዳሴው በላቲን ቋንቋ ይቀደ እንደ ነበር ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የላቲን ቋንቋን መማር እንደ ነበረባቸው፥ ነገር ግን በዩናይትድ ስቴትስ ተወልደው በዚያው በማደጋቸው መስዋዕተ ቅዳሴው ወደ እንግሊዝኛ ተቀይሮ ማግኘታቸውን አስታውሰዋል። ነገር ግን በዚህ መካከል ዋናው መስዋዕተ ቅዳሴው የሚቀርብበት ቋንቋ ሳይሆን ከሌሎች ልጆች ጋር መስዋዕተ ቅዳሴን የማገልገል ልምድ፣ ከልጆች ጋር የነበራቸው ጓደኝነት እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከኢየሱስ ጋር ያለው ቅርበት ምንጊዜም የሚያስደስታቸው እና የማይረሱት መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።
የእርስ በርስ መገናኛ ድልድዮች መገንባት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከበጋው የዕረፍት ጊዜ ጭብጥ ጋር በተገናኘ፥ ልጆች በአንዳንድ ነገር ከሚለዩዋቸው ልጆች ጋር እንዴት መቀራረብ እንደሚችሉ የቀረበላቸውን ጥያቄ ከመመለሳቸው በፊት ከዩክሬን ለመጡት ልጆች በእንግሊዘኛ ቋንቋ ሰላምታ አቅርበው፥ “እንደዚህ ያሉ ልምዶች ማለትም ከተለያዩ አገሮች፣ ቋንቋዎች እና ብዙ ልዩነቶች ካሏቸው ጋር መገናኘት በጣም አስፈላጊ ነው” ብለው ልጆች እርስ በእርስ መገናኘትን፣ መከባበርን እና ጓደኛሞች መሆንን የመማር ልምድ እንዲኖራቸው አበረታቷቸዋል።
ለተቀሩት የቡድኑ አባላት በጣሊያንኛ ቋንቋ ባደረጉት ንግግር፥ ዩክሬን በጦርነቱ ምክንያት በጣም እየተሰቃየች ያለች አገር ናት” በማለት አሳስበዋቸዋል። “በቋንቋ ልዩነት ምክንያት የመግባባት ተግዳሮት ሊያጋጥም ይችላል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ነገር ግን ከሌላ ሰው ጋር የመገናኘት ዕድል ሲኖር መከባበርን መማር አስፈላጊ መሆኑን አበክረው ተናግረው፥ በልዩነቶች ላይ ሳያተኩሩ እርስ በእርስ በመከባበር እንዴት መገናኘት እንዳለብን፣ እርስ በርስ መገናኘት የምንችልባቸውን የጓደኝነት፣ የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት ድልድዮች ከገነባን አብሮ ወደፊት መጓዝ እንችላለን” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህን ይበሉ እንጂ ዘወትር ቀላል እንደማይሆን አምነው፥ አንዳንድ ጊዜ ልዩ ጥረትን እንደሚጠይቅ፣ በሃሳብ፣ በአመለካከት ሆነ በአነጋገር የሚመሳሰል ሰው ማግኘት ከባድ እንደ ሆነ እና ያም ቢሆን እርስ በርስ መከባበርን መማር እና እንደ ጓደኛሞች አብሮ መኖር የሚቻል መሆኑን ማወቅ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለሰላም ተግቶ መሥራት
በመጨረሻም በዩክሬን ያለውን ግጭት በተመለከተ ወጣቶች በዚያች አገር ሰላምን ለመገንባት ምን ማድረግ እንደሚችሉ የተጠየቁት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከልጅነታችን ጀምሮ ሁላችንም ሰላምን እና ጓደኝነትን መፍጠር መማር እንችላለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምክሮችንም ሲለግሱ፥ ለጦርነት መሄድ እንደማይገባ እና ፈጽሞ ጥላቻን ማራመድ እንደማገባ አሳስበዋል። ለጓደኝነት የማይጋብዙ ብዙ ሌሎች በርካታ ትናንሽ ነገሮች መኖራቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ “ያ ሰው ያለው የሚያምር ነገር እኔ የለኝም” በሚል በልብ ውስጥ ቅናት ወይም ደስ የማይል ስሜት ሊሰማ ይችላል” ብለው፥ ይልቁንስ ኢየሱስ ክርስቶስ ወዳጅነትን፣ ከሁሉም ጋር ወንድማማችነትን እና እህትማማችነትን ማሳደግ እንድንማር መጥራቱን አስረድተው፥ በዚህ ልምድ ጣሊያናዊ፣ አሜሪካዊ ወይም ዩክሬናዊ፥ አገራችን የት ይሁን የት፥ ሁላችንም የእግዚአብሔር ልጆች ነን” ብለዋል።
ልጆች ከልጅነታቸው ጀምሮ እርስ በእርስ መከባበርን እንዲማሩ ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፥ ሌላውን እንደራስ ማየት፣ ከራሳችን የተለየ ቋንቋ ቢናገሩ እንኳን ለልዩነት የሚጋብዝ መሆን እንደሌለበት አሳስበው፥ ወደ ሌሎች ለመቅረብ ብዙ የተለያዩ መንገዶች መኖራቸውን የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ከእነዚህም ጥቂቶቹ ካለን ውስጥ ለሌላቸው ማካፈል እና ሁልጊዜ የመረዳዳት መንገድ መፈለግ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፥ ሕጻናትም ቢሆኑ የሰላም፣ የጓደኝነት እና የፍቅር አራማጆች በመሆን እነዚህን እሴቶች በሁሉም መካከል የማሳደግ ዕድሎችን መፈለግ ይችላሉ” ሲሉ አስገንዝበዋል።