MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ለኢዮቤልዩ በዓላቸው ወደ ሮም ለመጡት ወጣት ነጋዲያን አቀባበል አደረጉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ለኢዮቤልዩ በዓላቸው ወደ ሮም ለመጡት ወጣት ነጋዲያን አቀባበል አደረጉ  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “የወጣት ነጋዲያን ድምጽ እስከ ምድር ዳርቻ ይሰማል” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ለመክበር ከዓለም ዙሪያ ወደ ሮም የመጡ ወጣት ነጋዲያንን በደስታ ተቀብለው የመክፈቻ ንግግር አድርገውላቸዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት በርካታ ወጣቶች ባደርጉት ንግግር ለሰላም እንዲጸልዩ ጋብዘው፥ “በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባለን እምነት አብረን እንጓዝ” ሲሉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለኢዮቤልዩ በዓላቸው ወደ ሮም ለመጡ በርካታ ወጣቶች ማክሰኞ ሐምሌ 22/2017 ዓ. ም. አመሻሽ ላይ አቀባበል አድርገውላቸዋል። በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ረዳት ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ ከመሩት የመክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በመዞር ለወጣቶች ሰላምታ ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለወጣት ነጋዲያን ባሰሙት ንግግር፥ የምድር ጨው እና የዓለም ብርሃን ናችሁ” ሲሉ አስታውሰው፥ ኢየሱስ ክርስቶስን ለማወቅ ያላችሁ ጉጉት እና ስለ እርሱ ምታሰሙት ድምጽ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይሰማል” ሲሉ ተናግረዋል።

በወጣቶች የተስፋ ኢዮቤልዩ በዓል መጀመሪያ ቀናት ላይ ባሰሙት ንግግር ዓለም የተስፋ መልዕክቶችን እንደሚፈልግ ገልጸው፥ ወጣቶች ራሳቸው የተስፋ መልእክት እንደሆኑ እና ተስፋን ወደ ሁሉ ሰው ዘንድ ማምጣትን መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመቀጠልም፥ “ሁላችሁም በዓለም ውስጥ ዘወትር የተስፋ ምልክቶች እንደምትሆኑ ተስፋ እናደርጋለን” ብለው በመጪዎቹ ቀናት ውስጥ የእግዚአብሔርን ጸጋ እና የተስፋ መልዕክትን ለሮም ከተማ ነዋሪዎች፣ ለጣሊያ ሕዝብ እና ለዓለም ብርሃን የሚያመጣ ኃይል የመሆን ዕድል ታገኛላችሁ ብለው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባለን እምነት አብረን በመጓዝ፥ ጩኸታችንም ለዓለም ሰላም ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ወጣቶችን “ስለ ሰላም እንጸልይ” በማለት የጋበዙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም አስታራቂ በመሆኑ ሁላችንም የዓለም ብርሃን ምስክሮች እንሁን” ብለዋል። ለወጣቶች ቡራኬአቸውን ከሰጡ በኋላ መልካም ሳምንት ተመኝተው፥ ነሐሴ 26 እና 27/2017 ዓ. ም. ሮም ውስጥ በቶር ቬርጋታ ሰፊ ሜዳ በወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል ማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት ላይ በድጋሚ እንደሚገናኙ አሳስበዋል።

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተሰበሰቡት በርካታ ወጣቶች
በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የተሰበሰቡት በርካታ ወጣቶች   (@Vatican Media)

የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ምስክርነት

የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል መክፈቻ መስዋዕተ ቅዳሴን የመሩት፥ በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ረዳት ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ በዕለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ባሰሙት ስብከት፥ “ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በግልጽ እንደተናገረው፥ ከሁሉም በላይ እምነት በራሳችን የማንጀምረው የእርስ በርስ ግንኙነት ነው” ብለዋል።

“ከሞት ስለተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ መመስከርን ፈጽሞ መፍራት አይገባም” ብለው፥ ምክንያቱም ክርስቲያኖች እንድንሆን የሚያደርገን ይህ ምስክርነታችን ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

በቅድስት መንበር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ረዳት ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ሪኖ ፊዚኬላ በስብከታቸው ማጠቃለያ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ባለፈው እሁድ የተናገሩትን በማስታወስ፥ “በመዝጊያው መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ወጣቶች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንደሚገናኙ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

30 Jul 2025, 16:53