ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ የቅዱስ ዶሚኒኮስ ማኅበር ገዳማውያን መንፈስ ቅዱስን በጥሞና እንዲያዳምጡ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የማኅበራቸውን ጠቅላላ ጉባኤ በፖላንድ ክራኮቪያ ከተማ ለማካሄድ የተሰበሰቡት የቅዱስ ዶሚኒኮስ ማኅበር ገዳም የአውራጃ ተወካዮችን በጸሎት እንደሚተባበሯቸው ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው የቃለ ስብከት መሪ ለሆኑት አባ ጄራርድ ቲሞነር በላኩት መልዕክት፥ “ጉባኤውን የሚያካሂዱባቸው እነዚያ የጸጋ ቀናት በማያሳዝን ተስፋ ላይ የተመሠረቱ የመታደስ እና ፈተናዎች በበዙበት ዓለም ውስጥ የምሥራቹን ቃል እንዲያውጁ እግዚአብሔር እንደጠራቸው የሚያቁባቸው አጋጣሚዎች ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።
መንፈስ ቅዱስን ማዳመጥ
ቅዱስነታቸው የማኅበሩ ጉባኤን መሪ ርዕሥ መሠረት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕከት፥ የቅዱስ ዶሚኒኮስ የስብከት ተነሳሽነት ዋና ዓላማ የሆኑ አራት ዓይነት ታዳሚዎችን በተለይም ኢየሱስን ገና የላውቁ፣ የክርስትና እምነት ተከታዮች፣ ራሳቸውን ከኢየሱስ ክርስቶስ የራቁት እና ወጣቶች የሚሉት ወቅታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
“ቤተ ክርስቲያንን በሙሉ እውነት መምራት የቀጠለውን መንፈስ ቅዱስን በጥሞና እንድታዳምጡ እጸልያለሁ” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመልዕክታቸው አረጋግጠዋል።
በቅዱስ ዶሚኒኮስ ብርታት እና መንፈሳዊነት መታመን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመቀጠልም፥ የቅዱስ ዶሚኒኮስ ማኅበር ገዳማውያን ራሱ ቅዱስ ዶሚኒኮስ በመረጠው የቅዱስ ወንጌል ሕይወት የኢየሱስ ክርስቶስ አካል የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል ያላቸውን ቁርጠኝነት እንደሚያጠናክሩት ተስፋ አድርገዋል።
“የወንድማማችነት እና የጸሎት ልምዳችሁ እንደ ቅዱስ ዶሚኒኮስ ማኅበር አባላት አንድ አድርጓችሁ በኅብረት ትስስር እንድትጠናከሩ እና የስብከት አገልግሎት ጥሪያችሁን በተሟላ ሁኔታ እንድትኖሩ” በማለት መልዕክት ጽፈዋል።
የማኅበሩ አባላት ለቅዱስ ዶሚኒኮስ ፍቅር እና መንፈሳዊነት ታማኝ በመሆን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተልዕኮዋቸውን እንደሚወጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አደራ በመስጠት፥ ለማኅበር አባላት በሙሉ ቡራኬያቸውን በመስጠት መልዕክታቸውን አጠቃልለዋል።