MAP

የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በምሽት ሲታይ የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ በምሽት ሲታይ 

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ የጦር መሣሪያ ንግድን አውግዘው በጀርባው ያለውን የገንዘብ ማግኛ መንገድን ተቃወሙ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በካስቴል ጋንዶልፎ ከሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያቸው ወደ ሐዋርያዊ መንበራቸው ተመልሰዋል። ቅዱስነታቸው ከሥፍራው ከመነሳታቸው በፊት ዓለም አቀፍ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ መላሽ ሰጥተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በካስቴል ጋንዶልፎ አሥራ ስድስት ቀናትን ካሳለፉ በኋላ ማክሰኞ ሐምሌ 15/2017 ዓ. ም. ማምሻውን ወደ ቫቲካን ተመልሰዋል። ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ትንሽ ቀደም ብሎ ከሥፍራው የተመለሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ጉዞአቸውን ወደ ቫቲካን ከመጀመራቸው አስቀድመው ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ቅዱስነታቸው ለጋዜጠኞቹ በሰጡት ምላሽ፥ በጦርነት ላይ የተሰማራ ሰው መሣሪያውን እንዲያስቀምጥ ጠይቀው፥ “ከጀርባው ያለውን ገንዘብ የማግኛ መንገድ እንዳይከተል እያንዳንዱን ሰው ማበረታታት አለብን” ብለዋል።

እንደ ጋዛ ባሉ የጦርነት ቀጠናዎች ሐዋርያዊ ጉብኝት የማድረግ አጋጣሚ እንዳለ የተጠየቁት ቅዱሳነታቸው፥ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ የሚመኟቸው በርካታ ቦታዎች እንዳሉ ገልጸው፥ ነገር ግን ጉብኝታቸው ለተፈጠረው ቀውስ የግድ መልስ የሚገኝበት ሊሆን አይችልም” ብለዋል።

“ብዙ ጊዜ ሰዎች በጦር መሣሪያ ንግድ ምክንያት ዋጋ የሌላቸው ይሆናሉ” ብለው፥ ለእያንዳንዱን የሰው ልጅ ክርስቲያን ይሁን ሙስሊም፥ ለሁሉም ሃይማኖት ተከታይ ሰብዓዊ ክብር ያለማቋረጥ መቆም አለብን” ብለው፥ ሁላችንም በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠርን የእግዚአብሔር ልጆች በመሆናችን ጥረታችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።

በካስቴል ጋንዶልፎ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ውስጥ ጥሩ ጊዜ ማሳለፋቸውን የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ የሚያማምሩ ቦታዎችን ማየት መቻላቸውን፣ የተወሰኑ ሥራዎችን እየሠሩ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ሲከታተሉ እንደቆዩ ገልጸው፥ የቤተ ክርስቲያን ድምጽ አስፈላጊ እንደሆነ እና ለዚህም እግዚአብሔርን አመስግነው፥ “ሰላምን ለማሳደግ የምናደርገውን ጥረት እንቀጥል” በማለት ቃለ ምልልሳቸውን ደምድመዋል።

 

 

 

 

23 Jul 2025, 16:55