ር.ሊ.ጳ ሊዮ ሞትን ማታለል አንችልም፣ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት ሕይወትን ማገልገል ይኖርብናል አሉ
ር.ሊ.ጳ ሊዮ ሞትን ማታለል አንችልም፣ የዘላለምን ሕይወት ለማግኘት ሕይወትን ማገልገል ይኖርብናል አሉ!
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በካስቴል ጋንዶልፎ ከሚገኙት ምእመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ሲጸልዩ ክርስቲያኖችን በማሳሰብ ሞትን በማጭበርበር ሳይሆን በአገልግሎት እና በፍቅር ሌሎችን በመንከባከብ የዘላለም ሕይወት እናገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
የአውሮፓዊያኑን የበጋ ወር እረፍት በካስቴል ጋንዶልፎ ማድረጋቸውን የቀጠሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሮም አቅራቢያ ወደሚገኝ ተራራማ ከተማ ከመጡት ምዕመናን ጋር በመሆን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ማድረጋቸው ተገልጿል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በነፃነት አደባባይ ለተሰበሰቡት ባደረጉት ንግግር በወንጌል ውስጥ ለኢየሱስ የቀረበለትን ጥያቄ በማሰላሰል “መምህር ሆይ፣ የዘላለም ሕይወትን እንድወርስ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?" በማለት የሕግ መምህር የነበረው ሰው ስላነስው ጥያቄ አስታውሰዋል።
ቅዱስ አባታችን የሰውየው ጥያቄ የሰውን ልብ ጥልቅ ምኞት የሚገልጽ መሆኑን ተገንዝበዋል፣ ይህም “ከውድቀት፣ ከክፋት እና ከሞት የጸዳ ሕልውና” ነው ብለዋል።
በኃይል የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንደማንችል ወይም ለማግኘት መደራደር እንደማንችል ይልቁንም መውረስ እንዳለብን ጠቁመዋል።
"ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር እንደሚያደርጉት እግዚአብሔር ብቻ የሚሰጥ የዘላለም ሕይወት ለእኛ ርስት ሆኖ ተሰጥቶናል" ብሏል።
በዚህ ምክንያት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እንደ ገለጹት ከሆነ፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማድረግ እንዳለብን ተናግሯል፣ ይህም ማለት እግዚአብሔርን በፍጹም ልባችን መውደድ እና ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን መውደድ ማለት ነው ያሉ ሲሆን "እነዚህን ሁለት ነገሮች ስናደርግ ለአብ ፍቅር ምላሽ እንሰጣለን" ብሏል። "የእግዚአብሔር ፈቃድ አብ ራሱ በመጀመሪያ የተከተለው የሕይወት ሕግ ነው፣ በልጁ በኢየሱስ ያለ ቅድመ ሁኔታ እኛን በመውደድ አሳይቷል" ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ክርስቲያኖች ለእውነተኛ ፍቅር ትርጉም ኢየሱስን እንዲመለከቱ አሳስበዋል፣ ፍቅር ለጋስ ነው፣ ይቅር ባይ እና ሰፊ ነው፣ በራሳችን ላይ ተዘግቶ አይተወንም ብለዋል።
እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰው ልጆች እንደቀረበ ሁሉ እኛም በዙሪያችን ያሉትን እንድንንከባከብ ተጠርተናል ያሉት ቅዱስነታቸው “የዓለም አዳኝ የሆነውን የኢየሱስን ምሳሌ በመላበስ፣ እኛ ደግሞ የተጠራነው መጽናኛ እንድናመጣ እና ተስፋ እንዳንቆርጥ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ተስፋ የቆረጡትን ሰዎች ተስፋቸውን መልሰው እንዲያገኙ መርዳት ነው" ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እግዚአብሔርን እና ባልንጀሮቻችንን እንድንወድ ከሁሉ የላቀው ትእዛዝ የሰዎችን ሕግጋት ሁሉ የሚበልጥ እና እውነተኛ ፍቺአቸውን የሚሰጣቸው መሆኑን በማስታወስ ተናግረዋል።
"ለዘላለም ለመኖር ሞትን ማታለል አይጠበቅብንም፣ ነገር ግን ህይወትን ለማገልገል በዚህ አብረን ጊዜያችንን ሌሎችን በመንከባከብ ማሳለፍ ይኖርብናል" ብለዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሕይወትን ለማገልገል ስንፈልግ “በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ የሰላም የእደጥበብ ባለሙያዎች ልንሆን ይገባል" ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው አስተንትኖዋቸውን አጠቃለዋል።