MAP

በሮም ውስጥ የሚገኝ መጠለያ አልባ ሰው በሮም ውስጥ የሚገኝ መጠለያ አልባ ሰው  (ANSA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ "ድሃን መርዳት ከበጎ ተግባርነት ይልቅ የፍትህ ጉዳይ ነው" ሲሉ አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በኅዳር 7/2018 ዓ. ም. ለ9ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የድሆች ቀን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ድሆች የተወደዱ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እንደሆኑ፥ እነርሱን መርዳት ፍትሃዊ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የሰው ልጅ ደኅንነት በጦር መሣሪያ እንደማይረጋገጥ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ የኢዮቤልዩ ዓመት አሮጌ እና አዲስ የድህነት ዓይነቶችን ለመዋጋት የሚያግዙ ፖሊሲዎችን ለማርቀቅ እንደሚረዳ ቤተ ክርስቲያን ተስፋ እንደምታደርግ ገልጸው፥ የሥራ እና ትምህርት ዕድሎች፣ የመኖሪያ ቤት እጥረት እና የጤና አገልግሎቶች በጦር መሣሪያ ኃይል እንደማይቃለሉ አስረድተዋል።

“ድሆችን መርዳት ከበጎ አድራጎት ሥራነት ይልቅ የፍትህ ጉዳይ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ሁሉም ዓይነት ድህነት ወንጌልን በተጨባጭ እንድንኖር እና ውጤታማ የሆኑ የተስፋ ምልክቶችን እንድናሳይ የቀረቡ ጥሪዎች ናቸው” በማለት በኅዳር 7/2018 ዓ. ም. ለ9ኛ ጊዜ ለሚከበረው የዓለም የድሆች ቀን ባስተላለፉት መልዕክት አሳስበዋል።

የድሆች ጠባቂ በሆነው በቅዱስ አንጦኒዮስ ዓመታዊ በዓል ዕለት ሰኔ 6/2017 ዓ. ም. የታተመው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መልዕክት፥ በክርስቲያን ተስፋ አስፈላጊነት ላይ በማሰላልሰል የቅዱስ ዓመት ጭብጦችን ማለትም ድህነትን፣ ግድየለሽነትን እና ግጭትን በመቃወም ተጨባጭ የድጋፍ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ በጥብቅ የሚያሳስብ እንደሆነ ታውቋል።

ድሆች እጅግ የተወደዱ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ናቸው!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመልዕክታቸው፥ የዓለም የድሆች ቀን፥ ድሆች የቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ አገልግሎት ዋና ማዕከል መሆናቸውን የሚያስታውስ፥ በበጎ አድራጎት ገጽታ ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያን የምታከብረውን እና የምታበስረውን ሁሉ ለማስታወስ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። “ድሆች ግዙፍ ዕቃ ሳይሆኑ ነገር ግን እጅግ የተወደዱ የቤተ ክርስቲያን ልጆች እና በአሁኑ ጊዜ ወንጌልን በተግባር ለመኖር የሚያግዙ አዳዲስ መንገዶችን እንድንፈልግ የሚያደርጉን ናቸው” ብለው፥ እግዚአብሔር በድምፃቸው፣ በታሪካቸው እና በተሰቃየ ፊታቸው ባለጠጎች እንድንሆን ፈልጎ ድኅነትን መርጧል” ሲሉ ተናግረዋል።

ከድኅነት ሁኔታዎች አንፃር ወንጌልን በተግባር እንድንኖር የቀረበው ጥሪ በኢዮቤልዩ ዓመት የበለጠ ተጨባጭ እንደሆነ ገልጸው፥ “ቅዱስ በር በሚዘጋበት ወቅት በጸሎት፣ በመለወጥ እና በምስክርነት ዓመቱን በሙሉ በእኛ ላይ የፈሰሱ መለኮታዊ ስጦታዎችን መጠበቅ እና ወደ ሌሎች ማስተላለፍ አለብን” ብለዋል።

ተጨባጭ የተስፋ ምልክቶችን መፍጠር

ቅዱስነታቸው፥ “ማንኛውም ዓይነት ድህነት የሚያጋጥማቸው ሰዎችን ለመርዳት የተጠራነው፥ ክርስቲያናዊ በጎ አድራጎትን የሚመሰክሩት አዲስ የተስፋ ምልክቶችን ለመፍጠር ነው” በማለት አጽንዖት ሰጥተዋል።

“ቸርነት የሚጎድለው ሰው እምነትን እና ተስፋን ማጣት ብቻ ሳይሆን ከባልንጀራው ላይ ተስፋን ይቀማል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ድህነት መስተካከል እና መወገድ ያለባቸው መዋቅራዊ ምክንያቶች መኖራቸውን የሚያስታውስ፥ እንደ ትምህርት ቤቶች እና ሆስፒታሎች ያሉ ተቋማትን በመጥቀስ፥ አቅመ ደካሞችን እና የተገለሉትን ተቀብሎ ለመንከባከብ የተፈጠሩ እና በሁሉም ሀገራት የሕዝብ ፖሊሲዎች አካል መሆን እንዳለባቸው በማሳሰብ፥ ነገር ግን ጦርነት እና የኑሮ አለመመጣጠን ፖሊሲዎች ተግባራዊ እንዳይሆን የሚያግዱ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ድሆች የተስፋ ምስክሮች ናቸው

“ተግባራዊ ቁርጠኝነት በፈተናዎች ውስጥ ውድ ሃብት በመሆን፥ በሞቱ እና በትንሳኤው ያዳነን እና በመካከላችን ተመልሶ በሚመጣው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ልባችንን በሚያስቀምጥ በክርስቲያናዊ ተስፋ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት” ብለው፥ በጉዞአቸው ላይ እግዚአብሔርን ደጋፊያቸው ለማድረግ ካላቸው ፍላጎት አንጻር ድሆች ይህንን ተስፋ በተለየ መንገድ ሊለማመዱት እንደሚችሉ አስረድተዋል።

“ድሆች የጠንካራ እና አስተማማኝ ተስፋ ምስክሮች ሊሆኑ ይችላሉ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ምክንያቱም በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ፣ በእጦት፣ በመከራ እና በመገለል የተገነቡ መሆናቸውን በማስረዳት፥ ሥልጣን እና የሃብት ብዛት ድሆችን በማሰቃየት ብዙውን ጊዜ የችግር ሰለባ እንደሚያደርጋቸው አስረድተዋል።

መንፈሳዊ ድህነት

“የወንጌል ደስታ” የሚለውን የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳንን የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ድሆች ላይ የሚደርስ የከፋ መድልዎ የመንፈሳዊ ትኩረት እጦት ነው” ሲሉም አስምረውበታል።

የእምነት ሕግ እና የተስፋ ሚስጥር የሆኑት የዚህ ምድር ሃብቶች፣ ቁሳዊ እውነታዎች፣ ዓለማዊ ደስታዎች፣ ኢኮኖሚያዊ ደህንነቶች ምንም እንኳን አስፈላጊ ቢሆኑም፥ ልብን ለማርካት በቂ እንዳልሆኑ ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ ሃብት ብዙውን ጊዜ ሰዎችን በማታለል ወደ ድህነት እንደሚወስድ፥ ከሁሉም በላይ አንድ ሰው እግዚአብሔር እንደማያስፈልገው እና ​​ሕይወቱን ያለ እግዚአብሔር ድጋፍ መምራት እንደሚችል አድርጎ እንዲያስብ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል።

 

14 Jun 2025, 16:29