ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በናይጄሪያ ቤኑ ግዛት በጭፍጨፋ የተገደሉትን በጸሎት አስታወሱ
ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እሁድ ሰኔ 8/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ያሰሙትን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት ከዚህ ቀጥሎ እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ እንደምን አረፈዳችሁ! ዛሬ ጠዋት የስፖርት ኢዮቤልዩ በዓልን በመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት አክብረናል። በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ ለምትገኙ ስፖርተኞች በሙሉ ሰላምታዬን አቀርባለሁ። ስፖርታዊ ጨዋታዎች ወይም እንቅስቃሴዎች በተወዳዳሪዎች መካከል ዘወትር በልግስና መንፈስ እንዲሆን፣ ተወዳዳሪዎችን በሚያደስት እና በሚያዝናና መልክ እንዲሆን እመክራችኋለሁ። ምክንያቱም የሰው ልጅ በመደሰት እና በመዝናናት ፈጣሪውን ስለሚመስል ነው።
ስፖርት ሰላምን ለመገንባት ከሚረዱ መንገዶች አንዱ ነው። ምክንያቱም እርስ በርስ መከባበርን እና ታማኝነትን የሚያስተምር በመሆኑ የአንድነት እና የወንድማማችነት ባሕል እንዲያድግ ያግዛል። ውድ እህቶቼ እና ወንድሞቼ፣ ሁሉንም ዓይነት ግፍ እና ጭቆና ተቃውማችሁ ይህ የአንድነት እና የወንድማማችነት ባሕል የሚያድግበትን ስልት እንድትለማመዱት አበረታታችኋለሁ።
በልዩ ልዩ አካባቢዎች አውዳሚ ጦርነቶች የሚካሄዱበት ይህ ዓለማችን ከዚህ አደጋ ለመውጣት ብዙ እገዛን ይፈልጋል! በማይናማር የተኩስ አቁም ስምምነት ቢደረግም ጦርነቱ ቀጥሏል። በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። ሁሉም ወገኖች ወደ ሰላም እና ወደ መረጋጋት የሚያመጣቸውን የጋራ የውይይት መንገድ እንዲከተሉ አደራ እላለሁ።
ሰኔ 6/2017 ዓ. ም. ምሽት በናይጄሪያ ቤኑ ግዛት በዬልዋታ ከተማ አስከፊ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል። በዚህም ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ሰዎች በከፍተኛ ጭካኔ የተገደሉ ሲሆን፥ ከእነዚህም አብዛኞቹ በአካባቢው በሚገኝ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተስተናገዱ ተፈናቃዮች ነበሩ። በተለያዩ ጥቃቶች በተጎዳች ናይጄሪያ ውስጥ ደህንነት፣ ፍትህ እና ሰላም እንዲሰፍን እጸልያለሁ። በተለይ በቤኑ ግዛት በገጠራማው አካባቢ ለሚገኙት ክርስቲያን ማኅበረሰቦች እና የማያቋረጥ የጥቃት ሰለባ ለሆኑት ማኅበረሰቦች እጸልያለሁ።
ከሁለት ዓመት በላይ በሁከት ስትሰቃይ የቆየችውን የሱዳን ሪፐብሊክንም በጸሎት አስባለሁ። በኤልፋሸር ቁምስና በቦምብ ጥቃት የተገደሉ የቁምስናው መሪ ካኅን የአባ ጁሙ ግድያ አሳዛኝ ዜና ደርሶኛል። ለአባ ጁሙ እና በጥቃቱ የሞቱትን በሙሉ በጸሎቴ እንደማስታውሳቸው አረጋግጣለሁ።
ጦረኞች ውጊያቸውን እንዲያቆሙ፣ ሰላማዊ ሰዎችን ከአደጋ በማትርፍ ለሰላም እንዲነጋገሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በከባድ ሰብዓዊ ቀውስ ለተጎዱት ሕዝቦች ቢያንስ አስፈላጊውን ዕርዳታ የመስጠት ጥረቱን እንዲያጠናክር አደራ እላለሁ። በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በዩክሬን እና በመላው ዓለም ሰላም እንዲሰፍን የምናቀርበውን ጸሎት እንቀጥል።
ዛሬ ከሰዓት በኋላ በሮም በሚገኘው በቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ወጣት ሰማዕት ፍሎሪበርት ቧና ቹይ ብጽዕና ይታወጃል። በሃያ ስድስት ዓመቱ ወጣት ፍሎሪበርት የተገደለው፥ ክርስቲያን እንደመሆኑ መጠን፥ በአቅመ ደካሞች እና ድሆች ላይ ይደርስ የነበረውን መከራ እና ግፍ ይቃወም ስለነበር ነው። ምስክርነቱ ለኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እና ለመላው የአፍሪካ ወጣቶች ድፍረት እና ተስፋ ይስጣቸው!
ለወጣቶች የማስተላልፈው መልዕክትም፥ ከአንድ ወር ተኩል በኋላ በሮም በሚከበረው የወጣቶች ኢዮቤልዩ በዓል እንገናኛለን! የሰላም ንግሥት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን። ለሁላችሁም መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ!”