ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “የቅድስት መንበር ጽ/ቤት ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያንን የሚያስተባብር ነው"።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ከቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በቫቲካን ሐሙስ ግንቦት 28/2017 ዓ. ም. በተገናኙ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፥ ጽሕፈት ቤቱ ለጳጳዊ ተልዕኮ ውጤታማነት ለሚያበረክተው እገዛ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ቅዱስነታቸው ለአባላቱ ባደረጉት ንግግር፥ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊንን ለሥራቸው አመስግነው፥ የቅዱስ ጴጥሮስ ሐዋርያዊ የተተኪነት አገልግሎት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ለሰጡት ቀጣይነት ላለው ትብብር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪነት አገልግሎታቸውን ከጀመሩ አንድ ወር እንኳ እንዳልሞላቸው የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ብቻቸውን ሆነው ወደፊት መራመድ እንደማይችሉ ገልጸው፥ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች በሚያደርጉት ትብብር ላይ መተማመን እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ ጽሕፈት ቤቱን ከልብ አመስግነዋል።
የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ታሪክ ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የሚጀምር ሲሆን፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እና ከሌሎች መንግሥታት ጋር የግንኙነቶች ማዕከል ሆኖ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዓለም አቀፋዊ እየያዘ መጥቷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ከምዕመናን ወገን የተወጣጡ እንደሆኑ እና ከ50 በላይ የሚሆኑት ሴት ምዕመናን ገዳማውያን መሆናቸውን በመጥቀስ ይህም የቤተ ክርስቲያኒቱን ገጽታ የሚገልጽ መሆኑን አስረድተዋል።
“ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አብሮ የሚሠራ ታላቅ ማኅበረሰብ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ጥያቄዎችን፣ ችግሮችን፣ ፈተናዎችን እና ተስፋዎችን በጋራ እንካፈላለን” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በማከልም፥ “አንድነት እና ካቶሊካዊነት በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ተልዕኮ ሁለት አስፈላጊ ልኬቶች ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።
“ከጊዜ እና ከታሪክ ጋር ተጣምረን የተፈጠርን ነን” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ የወንጌል ደስታ ለሁሉም ሰው እንዲደርስ እና በዘመናችን ባሉ ባህሎች እና ቋንቋዎች እንዲተላለፍ ለማድረግ እግዚአብሔር እንደ ሰው የወንዶችን እና የሴቶችን ቋንቋ እንደ መረጠ ሁሉ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንም ያንን መንገድ እንድትከተል ተጠርታለች ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት፥ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ባህሎችን እና ስሜቶችን እንድታከብር የሚያስችላትን የካቶሊካዊነት እና ሁለንተናዊነት ዕይታን መጠበቅ አለበት” ብለዋል።
“ይህ ዓለም አቀፋዊነት የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶችን በወዳጅነት ትስስር ላይ በመመሥረት በሮም እና በየአገራቱ በሚገኙ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ኅብረት ለማሳደግ ያስችላል” ብለዋል።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ያደረጉትን ማሻሻያ ያስታወሱት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ቤተ ክርስቲያን ለታሪክ ተግዳሮቶች ትኩረት መስጠት እንደሚገባት ማሰባቸውን ተናግረዋል።
“ስለዚህ አንድነቱ ወደ እውነታው ተጨባጭነት እና በተለያዩ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤቶች አባላት ወደ ተነሱት ጉዳዮች ይመራል” ብለው፥ “ዓለም አቀፋዊነት የቤተ ክርስቲያኗን ሁለገብ አንድነት ምስጢር በማነሳሳት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን ተግባር የሚያግዝ የጋራ ሥራን ይጠይቃል” ብለዋል።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ፥ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት በጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች እና ተቋማት መካከል አስተባባሪ ማዕከል ሆኖ እንዲያገልግል መፈለጋቸውን አስታውሰው፥ በዚህም መሠረት ጽሕፈት ቤቱ በእነዚህ ሁለት ገጽታዎች መካከል እንደ አገናኝ ሆኖ ማገልገል አለበት ብለዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2022 ዓ. ም. በንፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የታወጀው “ወንጌልን ስበኩ” የተሰኘ ሐዋርያዊ ድንጋጌ የማስተባበር ሚና ሙሉ ግንዛቤን ያገኘ ባለመሆኑ በድጋሚ ሊታይ እንደሚገባ ጠይቀዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1963 ዓ. ም. ከሰጡት ማሳሰቢያ ጋር ለቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ባለ ሥልጣናት ጥበብ እና የወንጌል መንፈስ ያላቸውን ቅርበት እና ጥልቅ ምስጋና በመግለጽ ንግግራቸውን አጠናቅቀዋል።
“ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቱ በምኞት ወይም በፉክክር እንዳይደናቀፍ” ሲሉ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የተናገሩትን በመጥቀስ፥ “ይልቁን ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ሲሉ ራሳቸውን በደስታ የሚለግሱ የእምነት እና የበጎ አድራጎት ማኅበረሰብ ወንድሞች እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ልጆች ይሁን” በማለት ለቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ያደረጉትን ንግግር አጠቃልለዋል።