MAP

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ቤተ ክኅነት አካዳሚ የሚሰጠውን የሚስዮናዊነት አገልግሎት ትምህርት የፈጸሙ ካኅናትን በቫቲካን ተቀብለው ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ቤተ ክኅነት አካዳሚ የሚሰጠውን የሚስዮናዊነት አገልግሎት ትምህርት የፈጸሙ ካኅናትን በቫቲካን ተቀብለው  (@VATICAN MEDIA)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የወደፊቶቹ የቫቲካን ልዑካን በትህትና እና በእምነት እንዲያገለግሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በጳጳሳዊ ቤተ ክኅነት አካዳሚ አስተባባሪነት የሚዘጋጀውን የሚስዮናዊነት የአገልግሎት ዓመት በብርታት የፈጸሙ ካኅናትን በቫቲካን ተቀብለው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ቤተ ክርስቲያን በምትልካቸው ቦታዎች ሁሉ የክኅነት ሕይወታቸውን በትህትና፣ በቅርበት እና በእምነት እንዲኖሩ አሳስቧቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ጳጳሳዊ ቤተ ክኅነት አካዳሚ የሚሰጠውን የሚስዮናዊነት አገልግሎት ትምህርት የፈጸመውን የካኅናት ቡድን በቫቲካን ውስጥ ዓርብ ሰኔ 13/2017 ዓ. ም. ተቀብለው ካመሰገኑ በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ ቤተ ክርስቲያን በምታሰማራቸው የትም ሥፍራ ሕይወታቸውን በትሕትና፣ ለሌሎች ቅርብ በመሆን እና በወንጌል ምስክርነት እንዲኖሩ ጥሪ አቅርበውላቸዋል።

“በደስታ እቀበላችኋለሁ! ለእያንዳንዳችሁ ልባዊ ሰላምታዬን አቀርብላችኋለሁ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የአካዳሚው ፕሬዘዳንት እና የትምህርት ዘርፍ መሪ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሳልቫቶሬ ፔናኪዮ፥ በሁሉም የዓለም ማዕዘናት ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የተዘጋጁ ካህናትን በማነጽ ላበረከቱት አስተዋጽዖ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የጳጳሳዊ ቤተ ክኅነት አካዳሚ ዋና ዓላማ የቤተ ክኅነት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣት ካኅናትን ለቅድስት መንበር ዲፕሎማሲዊ አገልግሎት በልዩ የትምህርት መርሐ ግብር ማዘጋጀት እንደሆነ ይታወቃል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የአካዳሚው የትምህርት መርሃ-ግብር ዋና አካል የሆነው የሚስዮናዊነት ዓመት፥ የመጨረሻ የዝግጅት ደረጃ ብቻ ሳይሆን፥ የእያንዳንዱ ካኅን የወደፊት አገልግሎት በእውነተኛ እና ሐዋርያዊ ተሳትፎ ላይ የተመሠረተውን የሽልማት ልምድን እንደሚወክል ገልጸዋል።

አገልግሎትን መሠረተ ያደረገ ትምህርት

በቫቲካን የዲፕሎማሲ ትምህርት ቤት ውስጥ ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ከሚገኙ ሌሎች ካኅናት ጋር በቅርቡ ያደረጉትን ስብሰባ በመጥቀስ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ ከእርሳቸው በፊት በነበሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የተዘጋጀው የትምህርት ሞዴል ጠቀሜታን ሲያስረዱ፥ አገልግሎትን መሠረት ባደረገ ትምህርት ካኅናትን ለማዘጋጀት ያለመ በመሆኑ ካኅናቱ ጠንካራ ሐዋርያዊ እረኞች ሆነው እንዲቆዩ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን የሚደረግ እንክብካቤ፥ ለሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ በኃላፊነት የተሰጠ በመሆኑ በዲፕሎማሲያዊ አገልግሎት ሆነ በሌሎች ሐዋርያዊ ተልዕኮዎች ውስጥ እንደ እነርሱ የተመደቡ ካኅናት ታማኝ እና የማይተካ አገልግሎት እንደሚያስፈልገው አስምረውበታል።

“የክኅነት ስጦታችሁን በትሕትና እና በየዋህነት እንድትኖሩት፣ በመደማመጥ እና ከሌሎች ጋር በመቀራረብ እንድትኖሩ አሳስባችኋለሁ” ብለው፥ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በታማኝነት የደጉ እረኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ካኅናቱ በአደራ የሚሰጣቸውን ተግባራት በሚሲዮናዊነት ወቅት በልዩ ልዩ አካባቢዎች በትጋት በመፈጸማቸው አመስግነው፥ በመጨረሻም፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ከሕዝቦች እና ከልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያላቸውን ቅርበት በጸሎትም ሆነ በተጨባጭ ምስክርነት በሚገልጹ ካኅናት ላይ መተማመን መቻል አለባቸው” ብለዋል።

 

21 Jun 2025, 16:16