MAP

ሩስያ በካርኪቭ በሚገኘው የመኖሪያ ሕንፃ ላይ የፈጸመችው የቦምብ ጥቃት ሩስያ በካርኪቭ በሚገኘው የመኖሪያ ሕንፃ ላይ የፈጸመችው የቦምብ ጥቃት  (ANSA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሩሲያ ሰላምን የሚያበረታቱ እርምጃዎችን እንድትወስድ ተማጸኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ የሃሳብ ልውውጥ አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ የሃሳብ ልውውጥ፥ ሩስያ ሰላምን የሚደግፉ እና የሚያበረታቱ እርምጃዎችን እንድትወስድ በማሳሰብ በሩስያ እና በዩክሬን መካከል ውይይት አስፈላጊ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ግንቦት 27/2017 ዓ. ም. ረፋድ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አቅርበው ከሰዓት በኋላ ከሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ ሃሳብ ተለዋውጠዋል።     

ቅዱስነታቸው ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ያደረጉት ውይይት በተለይ በዩክሬን ጦርነት ላይ ያተኮረ እንደ ነበር የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

አቶ ማቴዮ ብሩኒ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ውይይት በሰብዓዊ ሁኔታ እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ዕርዳታን በማመቻቸት አስፈላጊነት ላይ​​ ያተኮረ እንደ ነበር ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሩስያ ሰላምን የሚደግፉ እና የሚያበረታቱ እርምጃዎችን እንድትወስድ በመማጸን፥ በሁለቱ ወገኖች መካከል አወንታዊ ግንኙነቶችን በማድረግ ለጦርነቱ መፍትሄ ለመፈለግ የሚያስችል የጋራ ውይይት እንደሚያስፈልግ አጽንኦት መስጠታቸውን አቶ ማቴዮ ብሩኒ አክለው ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እና ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በውይይታቸው፥ በጣሊያን የቦሎኛ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ማትዮ ማርያ ዙፒ እስረኞችን ለመለዋወጥ እያደረጉት ስላለው ጥረትም ተወያይተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የሩስያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ኪሪልን በመጥቀስ፥ በሐዋርያዊ የአገልግሎት ሥልጣን መጀመሪያ ላይ ለላኩላቸው የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አመስግነው፥ “የጋራ ክርስቲያናዊ እሴቶች ሰላምን ለመሻት፣ ሕይወትን ከአደጋ ለመታደግ እና እውነተኛ የእምነት ነፃነትን ለመከተል የሚረዳ ብርሃን ነው” ማለታቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

 

 

 

05 Jun 2025, 10:32