MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት የቀረበውን ጸሎት በመሩበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት የቀረበውን ጸሎት በመሩበት ወቅት   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ መንፈስ ቅዱስ የእርቅ መንገዶችን እንዲከፍት ጸሎት አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እሑድ ሰኔ 1/2017 ዓ. ም. እኩለ ቀን ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ጋር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት የቀረበውን ጸሎት መርተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በዓለ ሃምሳ ወይም የጴንጠቆስጤ በዓል በተከበረበት ዕለት ባቀረቡት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጸሎት ላይ ባሰሙት ስብከት፥ በጦርነት በተከፋፈሉ ሰዎች መካከል መንፈስ ቅዱስ እርቅን እንዲያወርድ በማለት ጸሎታቸውን አድርሰዋል።

በብርሃነ ትንሳኤው ሰሞን ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ከሚቀርብ ጸሎት ቀደም ብሎ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ወደ ሰማንያ ሺህ ከሚጠጉ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኚዎች ጋር ሆነው ያቀረቡትን የበዓለ ሃምሳ መስዋዕተ ቅዳሴን መርተዋል።


በዕለቱ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ጋር ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ጸሎት ባቀረቡበት ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ስብከት፥ መንፈስ ቅዱስ ለልባችን እና በጦርነት ለተመሰቃቀለው ዓለማችን ሰላምን ለማምጣት ኃይል እንዳለው አስታውሰዋል።

“ከመንፈስ ቅዱስ የሰላም ስጦታን እንለምን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ከምንም በላይ በልቦች ውስጥ ሰላም እንዲኖር፥ በቤተሰብ፣ በማኅበረሰብ እና በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ ሰላምን ማሰራጨት የሚችለው ሰላማዊ ልብ ብቻ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ከሙታን የተነሳው የኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ጦርነት ባሉባቸው ቦታዎች ሁሉ የእርቅ መንገዶችን ሊከፍት እንደሚችል አስገንዝበው፥ ከዚህም ጋር በስልጣን ላይ የሚገኙትን ሰዎች ልብ እንዲያብራላቸው እና ለሰላም ውይይት ድፍረትን እንዲጣቸው ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በእነዚህ ቀናት ውስጥ የሚፈጽሟቸውን መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶችን በብዙሃን መገናኛዎች አማካይነት ለሚከታተሉ በርካታ ሰዎች ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2025 ቅዱስ ዓመት የኢዮቤልዩ በዓላቸውን በሮም ለማክበር የተገኙ በርካታ የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበራትን፣ እንቅናቄዎችን እና አዳዲስ ማኅበረሰቦች አመስግነዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ምክንያት በማድረግ ከቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበራት፣ እንቅናቄዎች እና አዳዲስ ማኅበረሰቦች ጋር ሆነው ካሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ማጠቃለያ ላይ ወደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰማይ ንግሥት ዘንድ ጸሎት አድርሰዋል።

ቅዱስነታቸው በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ስብከት፥ ምዕመናን በኢዮቤልዩ በዓል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመታደስ የኢየሱስ ክርስቶስን ተስፋ ወደ ሕዝቦች ሁሉ እንዲያደርሱ አደራ ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስብከታቸው ማጠቃለያ፥ በጣሊያን እና በሌሎች ሀገራት የትምህርት ዘመናቸውን በማጠናቀቅ የዕረፍት ጊዜያቸውን ለጀመሩ ተማሪዎች መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ለሁሉም ተማሪዎች እና መምህራን በተለይም በመጪዎቹ ቀናት ትምህርታቸውን ለመጨረስ ፈተና በመውሰድ ላይ ለሚገኙት ተማሪዎች በሙሉ ሰላምታቸውን ማቅረብ እንደሚፈልጋልጉ ገልጸዋል።

 

09 Jun 2025, 18:13