ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ወደ መንፈስ ቅዱስ ባቀረቡት ጸሎት ጥላቻ ተወግዶ ሰላም እንዲሰፍን ተማጸኑ
ክቡራት እና ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እሁድ ሰኔ 1/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ያሰሙትን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት ከዚህ ቀጥሎ እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ‘ከትንሣኤው በኋላ ወደ ሰማይ በማረጉ የከበረ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን የላከበት መታሰቢያ ዕለት ደረሰ’ (ቅዱስ አጎስጢኖስ ስብከት 271. 1)። ዛሬም ደግሞ ሐዋርያት ተቀምጠው በነበሩበት ክፍል ውስጥ የሆነው ነገር በመካከላችን እንደ አዲስ ተፈጽሟል። በሚያስደንግጥ ኃይለኛ ነፋስ፥ እንደ እሳት የሚያበራ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በእኛ ላይ ወረደ (ሐዋ. 2፡1-11)።
ከሐዋ. 2: 1-11 ተወስዶ በተነበበው የመጀመሪያው ንባብ እንደሰማነው፥ መንፈስ ቅዱስ በሐዋርያት ሕይወት ውስጥ አንድ ያልተለመደ ነገር ፈጽሟል። የኢየሱስ ክርስቶስን ሞት ተከትሎ ሐዋርያት በፍርሃት እና በሐዘን ተውጠው በተዘጋ ቤት ውስጥ ተቀምጠው ሳለ መንፈስ ቅዱስ በላያቸው ወረደ። በዚህ ወቅት የተከሰቱትን ክስተቶች ለመተርጎም እና ከሞት የተነሣውን ኢየሱስ ክርስቶስን በቅርበት እንዲለማመዱ የሚያግዛቸውን የውስጣዊ ግንዛቤ አዲስ መንገድ ተቀበሉ። መንፈስ ቅዱስ ፍርሃታቸውን በማሸነፍ የውስጥ ሰንሰለቶቻቸውን ሰባበረ፤ ቁስላቸውን ፈወሰ፤ ጥንካሬን በመስጠት ወደ ሰዎች ሁሉ ዘንድ ሄደው የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራዎች የሚያውጁበትን ድፍረት ሰጣቸው።
የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ በዚያን ጊዜ በኢየሩሳሌም ከተማ ውስጥ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ በርካታ ሰዎች እንደ ነበሩ ይነግረናል። እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ይናገር ነበር (ሐዋ. 2 : 6)። መንፈስ ቅዱስ ድንበርን ተሻግሮ የሚሄድ በመሆኑ በበዓለ ሃምሳ ወይም በጴንጠቆስጤ ዕለት ሐዋርያቱ ወደ ነበሩበት ቤት ገባ። የቀወድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እንዳብራሩት፥ ‘መንፈስ ቅዱስ ማስተዋልን ይሰጣል፤ መንፈስ ቅዱስ የባቢሎን ግንብ በመፍረሱ ምክንያት በነዋሪዎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት፣
የእርስ በርስ ግጭት እና በመካከላቸው የተፈጠረውን የአዕምሮ እና የልብ መረበሽ ያስተካክላል። መንፈስ ቅዱስ ድንበሮችን ይከፍታል። ቤተ ክርስቲያን እንደ ሁል ጊዜው አዲስ መሆን አለባት። በሕዝቦች መካከል ያለውን ድንበር በመክፈት በመደብ እና በዘር መካከል ያለውን ድንበር ማፍረስ አለባት። በእርሷ ውስጥ የተረሱ ወይም የተናቁ ሰዎች ሊኖሩ አይችሉም። በእርሷ ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወንድሞች እና እህቶች የሆኑ ነጻ ሰዎች ይኖራሉ’ (የበዓለ ሃምሳ ስብከት፥ እ.አ.አ 2005)።
እዚህ ላይ ለአፍታ ያህል ቆም ብዬ ከእናንተ ጋር ላሰላስልበት የምፈልገው የጴንጤቆስጤ ወይም የበዓለ ሃምሳ ምስል አለን።
መንፈስ ቅዱስ ድንበሮችን ከሁሉም በፊት ልባችንን ይከፍታል። መንፈስ ቅዱስ ሕይወታችንን ለፍቅር የሚከፍት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። በእኛ ውስጥ ሆኖ የልባችንን ደንዳናነት፣ የአስተሳሰባችን ጠባብነትን፣ ራስ ወዳድነትን፣ ፍርሃታችንን እና ስለ ራሳችን ብቻ እንድናስብ የሚያደርገንን ትምክህተኝነት ይሰብራል። በግለኝነት አዙሪት ውስጥ እየተናጠ የሚገኘውን ሕይወታችንን ሊገጥም ይመጣል። በሚያሳዝን ሁኔታ በማደግ ላይ ባለው የማኅበራዊ ሚዲያ ዓለም ውስጥ የበለጠ ብቸኞች የመሆን አደጋ አለ። በማኅበራዊ ሚዲያ አማካይነት የማያቋርጥ ግንኙነት ቢኖርም ነገር ግን የእርስ በእርስ ግንኙነት መፍጠር አልቻልንም። ሁል ጊዜ በሕዝብ መካከል ብንሆንም ነገር ግን ግራ ተጋብተን ብቸኞች ሆነናል።
የእግዚአብሔር መንፈስ አዲስ የመቀራረብ መንገድን በማሳየት ሕይወትን እንድንለማመድ ያደርገናል። የሚሸፍነንን ጭምብል በማስወገድ ከራሳችን ጋር ያገናኘናል። የእርሱ ስጦታ የሆነውን ደስታ እንድንለማመድ በማስተማር ከእግዚብሔር ጋር እንድንገናኝ ያደርገናል። ከኢየሱስ ክርስቶስ ቃላት እንደሰማነው፣ በፍቅር በመኖር ብቻ ለቃሉ ታማኞች ሆነን የምንለወጥበትን ጥንካሬን እንደምናገኝ ይነግረናል። መንፈስ ቅዱስ የውስጥ ድንበሮቻችንን በመክፈት ሕይወታችን እርስ በርስ የመቀባበል እና የመታደስ ቦታ እንዲሆን ያደርጋል።
መንፈስ ቅዱስ ከሌሎች ጋር ያለንን የግንኙነት ድንበርን ይከፍታል። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ስጦታ የምናገኘው በውስጣችን ሊኖር ከሚመጣው፥ በእርሱ እና በአብ መካከል ባለው ፍቅር አማካይነት እንደሆነ ነግሮናል። በዚህ የፍቅር ስጦታ አማካይነት ግትርነታችንን አሸንፈን፥ ፍርሃትንም አስወግደን ልባችንን ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን የመክፈት ችሎታን ይሰጠናል። መንፈስ ቅዱስ እንደ ጥርጣሬ፣ ጭፍን ጥላቻ እና ሌሎችን የመጠቀም ፍላጎትን የመሳሰሉ፥ ግንኙነታችንን የሚያውኩ ጥልቅ እና ድብቅ አደጋዎችን ይከላከላል። ግንኙነቶች ጤናማ እንዳይሆኑ የሚያደርጉ፣ ብዙውን ጊዜ ወደ ሁከት የሚመሩ እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰቱ ያሉ በርካታ የግድያ ተግባራት መኖራቸውን በሕመም ስሜት አስባለሁ።
መንፈስ ቅዱስ በሌላ በኩል እኛን በማሳደግ ጥሩ እና ጤናማ የሆኑ ግንኙነቶችን ለመመስረት የሚያስችለንን የፍቅር፣ የደስታ፣ የሰላም፣ የትዕግስት፣ የቸርነት፣ የልግስና፣ የታማኝነት፣ የጨዋነት እና ራስን የመግዛት ፍሬን ይሰጠናል (ገላ 5፡22)። በዚህ መንገድ መንፈስ ቅዱስ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለንን የግንኙነት ድንበር በማስፋት የወንድማማችነት ደስታን ይሰጠናል። ይህ ለቤተ ክርስቲያን እጅግ ወሳኝ ነው። በእውነት ከሞት የተነሣው የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እና የጴንጤቆስጤ ደቀ መዛሙርት በመሆናችን፥ በመካከላችን ድንበርን ወይም መለያየትን ሳንፈጥር፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እርስ በእርስ በመወያይት እና በመስማማት፣ ልዩነቶቻችንን ማስታረቅ እና እንደ ቤተ ክርስቲያን ሁሉንም በእንግድነት የምንቀበል መሆን እንችላለን።
መንፈስ ቅዱስ በሰዎች መካከል ያሉ ድንበሮችን ይከፍታል። በጴንጠቆስጤ ዕለት ሐዋርያት ከሰዎች ጋር መግባባት የሚችሉበትን ቋንቋ ይናገሩ ነበር። በባቢሎን ግንብ መፍረስ ምክንያት የተፈጠረው ግራ መጋባት መንፈስ ቅዱስ ባመጣው ስምምነት ተፈቷል። የእግዚአብሔር መንፈስ ልባችንን አንድ ሲያደርግ እና ሌሎችን እንደ ወንድሞቻች እና እህቶቻች እንድንመለከታቸው በሚያደርገን ጊዜ፣ ልዩነቶች የመለያየት እና የግጭት ምክንያት ሳይሆኑ ነገር ግን ሁላችንም በወንድማማችነት እንድንጓዝ የሚያደርጉን የጋራ ሃብትቶቻችን ይሆናል።
መንፈስ ቅዱስ መሰናክሎችን በማስወድ የግዴለሽነት እና የጥላቻ ግንቦችን ያፈርሳል። ምክንያቱም እርሱ ሁሉን ነገር ስለሚያስተምረን እና ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገራቸውን ስለሚያስታውሰን ነው (ዮሐ. 14፡26)። መንፈስ ቅዱስ ከሁሉ በፊት የሁሉ ነገር ማዕከል እና ፍጻሜ የሆነውን የፍቅርን ትእዛዝ ያስተምረናል፣ ያስታውሰናል፣ በልባችን ውስጥም ይጽፍልናል። ፍቅር በሚገኝበት ቦታ ለጭፍን ጥላቻ፣ ከጎረቤቶቻችን ለሚለየን የምቾት ሥፍራ፣ በሚያሳዝን ሁኔታ ዛሬ በፖለቲካው ዘርፍም ብቅ እያለ ለምናየው የአግላይነት አስተሳሰብ ሥፍራ አይኖርም።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአንድ የጰንጠቆስጤ በዓል ላይ ባሰሙት ስብከት፥ ‘ዛሬ በዓለማችን ውስጥ ብዙ አለመግባባቶች አሉ፤ ትልቅ መለያየትም አለ። ሁላችንም እርስ በእርሳችን የተገናኘን ብንሆንም ነገር ግን በግዴለሽነት ደንዝዘን በብቸኝነት ተጨናንቀናል’ ማለታቸው ይታወሳል (ግንቦት 28/2023 እ.አ.አ)። በዓለማችን ውስጥ እየታዩ ያሉት ጦርነቶች የዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ምልክቶች ናቸው። መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን ያለውን ድንበር እንዲከፍት፣ የልዩነት ግድግዳን እንዲያፈርስ፣ ጥላቻን እንዲያስወግድ እና በሰማያት ያለው የአንድ አባት ልጆች ሆነን ለመኖር የሚያስችለንን የፍቅር እና የሰላም ስጦታን እንለምን።
ወንድሞች እና እህቶች፣ ጴንጤቆስጤ ወይም መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን እና ዓለምን ያድሳል! ኃይለኛ የመንፈስ ቅዱስ ንፋስ በመካከላችን እና በውስጣችን ይምጣ። የልባችንን ድንበር ይክፈት፣ ከእግዚአብሔር ጋር የመገናኘት ጸጋን ይስጠን። የፍቅር አድማሳችንን ያሳድግልን። ሰላም የሚነግስባትን ዓለም ለመገንባት የምናደርገውን ጥረታችንን ያጽናልን።
መንፈስ ቅዱስ የጎበኛት፣ በጸጋ የተሞላች እጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም ከእኛ ጋር በመሆን ጸሎታችንን ወደ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እንድታደርሰው እንማጸናታለን።”