ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “የቅድስት መንበር ሠራተኞች ቅድስና፥ ቅድስት መንበርን ሊደግፍ ይገባል” አሉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት መንበር ኢዮቤልዩን ባከበረችበት ሰኞ ሰኔ 2/2017 ዓ. ም. ጠዋት ከሐዋርያዊ መንበር ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ሠራተኞች እና ባለስልጣናት ጋር አሳልፈዋል።
የበዓሉ ሥነ-ሥርዓት የጀመረው፥ የቅዱስ ቁርባን እና የእመቤታችን ማርያም ገዳማዊያት ማኅበር አባል የሆኑት እህት ማርያ ግሎሪያ ሪቫ ባቀረቡት አስተንትኖ እንደ ነበር ተገልጿል። በመቀጠልም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የኢዮቤልዩ መስቀል ይዘው ከቅድስት መንበር ባለሥልጣናት ጋር ዑደት በማድረግ ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ቅዱስ በር መርተዋል።
ከዑደቱ በኋላ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ለሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቶች ሠራተኞች እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ፥ በሐዋርያዊ መንበር መንፈሳዊ መሠረት ላይ በማስተንተን ስብከታቸውን አቅርበዋል።
“ቅድስት መንበር በሁለት የጋራ ምሰሶዎች በልዩ መንገድ ተመሥርታለች ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ እነዚህም ማርያማዊ እና ሐዋርያዊ እንደሆኑ አስረድተው፥ “በኢየሱስ ክርስቶስ እና በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በመታገዝ የሐዋርያዊ አገልግሎት ፍሬያማነት እና ቅድስና የምታረጋግጥ በመሆኗ ማርያማዊት ነች” ብለዋል።
የቅድስት መንበር የኢዮቤልዩ በዓል፥ በበዓለ ሃምሳ ማግሥት፥ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቤተ ክርስቲያን እናት መታሰቢያነት በሚቀርብ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት የሚከበር መሆኑን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።
“በዕለቱ ቅዱስ ዮሐንስ ካጻፈው የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የተነበበው የወንጌል ክፍል፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ የተወደዱ ደቀ መዛሙርት አደራን ለእናቱ እንደሰጣት ይናገራል” ብለው በማከልም፥ “የቤተ ክርስቲያን ፍሬያማነት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍሬያማነት” እንደሆነ እና ይህም የሚረጋገጠው በቤተ ክርስቲያን አባላት ሕይወት እንደሆነ በማስረዳት፥ ስለዚህም “እያንዳንዱ ክርስቲያን ከመስቀል ላይ የሚገነዘበውን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር በተግባር ለመኖር ተጠርቷል” ሲሉ ተናግረዋል።
“የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና የቤተ ክርስቲያን ፍሬያማነት ከቅድስናዋ ማለትም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባላት አንድነት የተቆራኘ በመሆኑ፥ ቤተ ክርስቲያኑ ቅድስት እንደ ሆነች ሁሉ ቅድስት መንበርም ቅድስት ናት” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ሐዋርያዊ መንበር የቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ቅድስናን የሚያስጠብቀው ቤተ ክርስቲያን በቅድስና የኖረች በመሆኗ እንደሆነ አስረድተዋል።
“ቤተ ክርስቲያን በእያንዳንዱ አባሎቿ ቅድስና ውስጥ የምትኖር መሆኗ እውነት ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “በመሆኑም ቅድስት መንበርን ለማገልገል ከሁሉ የተሻለው መንገድ እያንዳንዳችን እንደ ሕይወታችን ሁኔታ፥ በተሰጠን ሃላፊነት መሠረት ቅዱሳን ለመሆን መጣር ነው” ብለዋል።
በአገልግሎቱ ምክንያት ከባድ የግል ሸክም የተሸከመውን ካህን እንደ ምሳሌ ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፥ በቅድስት መንበር ሐዋርያዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ በሚችለው አቅም ሁሉ ሥራውን በፍቅር እና በእምነት የሚያከናውን መሆኑን ተናግረዋል።
በአስቸጋሪ የቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ሆነው በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤቶች የሚሠሩ ወንድ እና ሴት ምእመንን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ “እነርሱም ቢሆኑ ሥራቸውን በቁርጠኝነት ሲያከናውኑ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና የቤተ ክርስቲያንን ፍሬያማነት ይመሰክራሉ” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በበዓለ ሃምሳ ቀን መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርት ላይ ሲወርድ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም አብረዋቸው እንደነበረች ገልጸው፥ “ይህም የቅድስት ድንግል ማርያም የቤተ ክርስቲያን እናትነት የሚያሳይ፥ እናትነቷም ሁል ጊዜ እና በሁሉ ቦታ የሚኖር ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
“የቤተ ክርስቲያን ፍሬያማነት፥ ከተወጋው ከኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ከሚፈስ፥ የቅዱሳት ምስጢራት ምልክት ከሆነው ደም እና ውሃ ጋር አብሮ ከሚፈስ ፀጋ ጋር ዘወትር የተቆራኘ ነው” ሲሉ ያስረዱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስን በመጥቀስ፥ እናት ቤተ ክርስቲያን የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪዎችን አገልግሎት የምትመራው በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቸርነት ተደግፋ እንደሆነ ተናግረዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በስብከታቸው ማጠቃለያ፥ የቅድስት መንበር ሠራተኞች እና ባለ ሥልጣናት የእግዚአብሔርን ቃል ለአካሄዳቸው ብርሃን እንዲያደርጉት አደራ ብለዋል።
በመጨረሻም፥ “እግዚአብሔር አባት ሆይ! ቤተ ክርስቲያንህ በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር እንድትደገፍ፣ በመንፈስ ቅዱስ የበለጠ ፍሬያማ እንድትሆን፣ በልጆቿ ቅድስና እንድትደሰት እና መላውን የሰው ልጅ በማህፀኗ እንድትሰበስባቸው” በማለት በኅብረት ባቀረቡት ጸሎት ሥነ-ሥርዓቱን ደምድመዋል።