ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ወጣቶች ዘወትር ለሚጠራቸው እግዚአብሔር ምላሽ እንዲሰጡ አሳሰቡ
ክቡራት ክቡራን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን፥ ያስተነተኑበትን የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ እናነብላችኋለን፥
ኢየሱስም እንዲህ አለ:- “መንግሥተ ሰማያት ለወይኑ የአትክልት ቦታ ሠራተኞችን ሊቀጥር ማልዶ የወጣ ባለቤት ትመስላለችና። ከሠራተኞቹ ጋር በቀን አንድ ዲናር ተስማምቶ ወደ ወይኑ አትክልት ሰደዳቸው። ወደ ሦስት ሰዓት ገደማ ወጥቶ በገበያ ቦታ ሥራ ፈትተው የቆሙ ሌሎችን አየ፤ እነርሱንም:- ‘እናንተም ወደ ወይኔ አትክልት ቦታ ሂዱ፤ የሚገባውንም እሰጣችኋለሁ’ አላቸው። እነርሱም ሄዱ። ደግሞም በስድስት እና በዘጠኝ ሰዓት ወጥቶ እንዲሁ አደረገ። ወደ አሥራ አንድ ሰዓት ገደማም ወጥቶ ሌሎችን ቆመው አገኘና፥ ‘ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈትታችሁ እዚህ ለምን ትቆማላችሁ?’ አላቸው። እነሱም:- ‘የሚቀጥረን ስለ አጣን ነው፤” አሉት። እርሱም:- ‘እናንተም ወደ ወይኔ አትክልት ቦታ ሂዱ፤’ አላቸው” (ማቴ. 20: 1-7)።
ክቡራት እና ክቡራን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ከኢየሱስ ምሳሌዎች አንዱን እንደገና ማየት እፈልጋለሁ። በዚህም ጊዜ ቢሆን ምሳሌው ተስፋችንን የሚያጎለብት ታሪክ አለው። በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ ለሕይወታችን ትርጉም ማግኘት እንደማንችል ይሰማናል፤ ምንም የማንጠቅም፣ ለምንም ብቁዎች እንዳልሆንን ይሰማናል። ልክ በገበያ ቦታ ሥራ ፈትተው የሚቀጥራቸውን ሰው እንደሚጠብቁ ሠራተኞች ማለት ነው። ነገር ግን አንዳንዴ ጊዜ በከንቱ ያልፋል፣ ሕይወትም ያልፋል። እውቅና ወይም አድናቆት አይሰማንም። ምናልባት በጊዜ አልደረስንም ይሆናል፤ ሌሎች ስለ ቀደሙን ሊሆን ይችላል ወይም ችግር ይዞን ሊሆን ይችላል።
የገበያ ቦታ ምሳሌ ለዘመናችንም ተገቢ ምሳሌ ነው። ምክንያቱም ገበያ የንግድ ቦታ ነው። በሚያሳዝን ሁኔታ አንድን ነገር ለማግኘት ሲሉ ፍቅር እና ክብርም ቢሆን ይዛል ይሸጣል። አድናቆት እና እውቅና ካልተሰጠን እራሳችንን ለመጀመሪያው ተጫራች ለመሸጥ እንጋለጣለን። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወታችን ዋጋ ያለው መሆኑን ያስታውሰናል፤ ምኞቱም ይህንን እንድናውቅ ለማገዝ ነው።
አስተያየት በምንሰጥበት በዛሬው ምሳሌ ላይም የሚቀጥራቸውን ሰው የሚጠብቁ ሠራተኞችን እናገኛለን። በማቴ. ምዕ. 20 ላይ ነን። በዚህም ውስጥ ባህሪው እንግዳ የሆነ፣ የሚገርም እና ፈታኝ ገፀ ባህሪን እናገኛለን። ሠራተኞቹን ለመፈለግ የወጣው የወይኑ ቦታ ባለቤት ነው። ይህ ሰው ከሠራተኞች ጋር የግል ዝምድና መመሥረት እንደሚፈልግ ግልጽ ነው።
እንዳልኩት ሁሉ፥ ይህ ተስፋ የሚሰጥ ምሳሌ ነው። ምክንያቱም የወይኑ ቦታ ባለቤት ለሕይወታቸው ትርጉም ለመስጠት የሚጠባበቁትን ሠራተኞች ለመፈለግ ተመላልሶ እንደሚወጣ የሚነግረን ስለ ሆነ ነው። የወይኑ እርሻ ባለቤት ገና ጎህ ሳይቀድ ከቤቱ ይወጣል። ከዚያም በየሦስት ሰዓታት ልዩነት ወደ ወይኑ ቦታ የሚልካቸውን ሠራተኞች ፈልጎ ይመለሳል። በዚህ መርሃ ግብሩ መሠረት ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት በኋላ እንደገና እንዲሄድ የሚያደርግ ምንም ምክንያት አይኖርም። ምክንያቱም የሥራ ቀን የሚያበቃው በአሥራ ሁለት ሰዓት ላይ ነው።
ይህ ደከመኝ ሰለቸኝ የማይል ጌታ ቀኑ እየመሸ ሲሄድ በቤቱ ከመቆየት ይልቅ በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ ለእያንዳንዳችን ሕይወት ዋጋ ሊሰጥ ይፈልጋል። በገበያ ቦታ የቆሙት ሠራተኞች ያ ቀን ከንቱ ሆኖ ቀረ ብለው ተስፋ ሳይቆርጡ አልቀሩም። ነገር ግን አንድ ሰው አሁንም ያምንባቸው ነበር። በሥራ ቀን የመጨረሻ ሰዓት ላይ ሠራተኞችን መውሰድ ምን ትርጉም አለው? ሆኖም ግን በሕይወታችን ውስጥ ትንሽ ነገር መሥራት የምንችል መስሎን የሚታየን ጊዜ ዘወትር ጠቃሚ ነው። እግዚአብሔር ሕይወታችንን የሚወድ በመሆኑ ዘወትር ትርጉም የማግኘት ዕድል አለ።
የዚህ የወይኑ ቦታ ባለቤት እውነተኛነት በቀኑ መጨረሻ በክፍያ ሲጠናቀቅ ይታያል። ገና ጎህ ሳይቀድ ወደ ወይን ቦታ ለሚገቡት የመጀመሪያ ሠራተኞች አንድ ዲናር ለመክፈል ተስማምቶ ነበር። ይህም የተለመደ የቀን ደሞዝ ነበር። ለሌሎችም ፍትሃዊ የሆነ ክፍያ እንደሚሰጣቸው ይነግራቸዋል። እንግዲህ እዚህ ላይ ነው ምሳሌው እንድናስብ የሚያደርገን። ፍትሃዊ ሲባል ምን ማለት ነው? የወይኑ ቦታ ባለቤት ለሆነው ማለትም ለእግዚአብሔር እያንዳንዱ ሰው ለመኖር የሚያስፈልገው ነገር እንዲኖረው ማድረግ ብቻ ነው። ሠራተኞቹን በግል ጠራቸው፤ ክብራቸውንም ያውቃል፤ በዚህም መሠረት ሊከፍላቸው ፈልጎ ለሁሉም አንድ አንድ ዲናር ሰጣቸው።
ታሪኩ ከመጀመሪያው ሰዓት ጀምሮ ሠራተኞቹ ቅር እንደተሰኙ ይናገራል። የወይን ቦታ ባለቤት ባህሪን ውበት ማየት አልቻሉም። በፍትሃዊነት ሳይሆን ነገር ግን ከለጋስነቱ እና ከበጎነቱ የተነሳ ተገቢውን ብቻ ሳይሆን አስፈላጊነቱን ጭምር የተመለከተውን የወይን ቦታ ባለቤት ማወቅ አልቻሉም። እግዚአብሔር፥ ሙሉ፣ ዘላለማዊ እና አስደሳች ሕይወት የሚገኝበት መንግሥቱን ለሁሉ ሰው ሊሰጥ ይፈልጋል። ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ የሚያደርገው ይህ ነው። ደረጃን ሳያስቀምጥ ልባቸውን ለሚከፍቱለት በሙሉ ራሱን ይሰጣል።
ከዚህ ምሳሌ አንጻር የዛሬው ክርስቲያን፥ ‘ክፍያው ተመሳሳይ ከሆነ ወዲያው ሥራ መጀመር ለምን አስፈለገ? የበለጠ መሥራት ለምን አስፈለገ?’ ብሎ በማሰብ ሊፈተን ይችላል። ቅዱስ አውግስጢኖስም እነዚህን ለመሰሉ ጥርጣሬዎች መልስ ሲሰጥ፡- ‘አንተ ደመወዝ እንዳለህ ተረድተህ ነበር ግን እርግጠኛ የማትሆን፥ የሚጠራህን ለምን ታስወግደዋለህ? በተስፋ ቃል የሚሰጥህን ዘግይተህ እንዳትወስድ ተጠንቀቅ’ ብሏል።
በተለይ ለወጣቶች ይህን መናገር እፈልጋለሁ። ጊዜ አትስጡ! ነገር ግን በወይኑ ቦታ እንድንሠራ ለሚጠራን ጌታ በጋለ ስሜት መልስ ስጡ። አትዘግዩ! እጆቻችሁን ለሥራ አዘጋጁ! ምክንያቱም እግዚአብሔር ለጋስ ስለሆነ አትከፉም! በወይኑ አትክልት ውስጥ በመሥራታችሁ ምክንያት በውስጣችሁ ለተሸከማችሁት እና የሕይወቴ ትርጉም ምንድን ነው? ብላችሁ ለምታቀርቡት ጥልቅ ጥያቄ መልስ ታገኛላችሁ።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ምንም ቢሆን ተስፋ አንቁረጥ! በጨለማው የሕይወት ጊዜ እንኳ ቢሆን፣ ለምንፈልገው መልስ ሳናገኝ ጊዜው እያለፈ ቢሆንም፣ እርሱን የምንጠብቅ እኛን ሊያገኘን ተመላልሶ የሚወጣውን እግዚአብሔርን እንጠይቀው። እርሱ ለጋስ ነው። በቅርቡም ይመጣልና!”