ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ተስፋችን ወደሆነው እና ሊፈውሰን ወደሚችል ኢየሱስ ዘንድ እንቅርብ!”
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በቫቲካን ባቀረቡት ሳምንታዊ የጠቅላላ አስተምህሮ ክፍል፥ ተስፋችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር እንደሚያድሰን እና በእምነት ወደ እርሱ የምንቀርብ ከሆነ ሊፈውሰን እንደሚችል አስረድተው፥ ለዚህ ማሳያ በሆኑ ሁለት ተአምራት ላይ በማስተንተን አስተምረዋል።
“በሕይወት ውስጥ ብስጭት እና ተስፋ መቁረጥ አለ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14፥ ሞትንም መለማመድ እንደሚቻል ከዚያች ሴት እና ከዚያ አባት እንማራለን ብለው፥ ፈዋሻችን፣ አዳኛችን እና ተስፋችን ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንቅረብ” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች የሚያቀረቡትን አስተምህሮ በመቀጠል፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ያለውን የፈውስ ኃይል በሚገልጹ ሁለት ተአምራት ላይ በማስተንተን “ተስፋችን ኢየሱስ ነው” የሚለውን የኢዮቤልዩ መሪ ርዕሥ መሠረት በማድረግ ሳምንታዊውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል።
በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባለው ሙሉ እምነት የሚገለጹ ሁለት ተአምራት
የመጀመሪያው ተዓምር፥ ቅዱስ ማርቆስ በጻፈው የጌታችን የኢየሱስ ወንጌል ላይ፥ ለብዙ ጊዜ በሕመም ስትሰቃይ የቆየች አንዲት ሴት በኅብረተሰቡ ዘንድ እንደ ርኩስ ተቆጥራ ስትገለል ብትቆይም በኢየሱስ ክርስቶስ የመፈወስ ኃይል በማመኗ
በሕዝቡ መካከል እርሱን ለመንካት እጆቿን በዘረጋጅ ጊዜ ኢየሱስ እንደፈወሳት እና “ልጄ ሆይ! እምነትሽ አድኖሻልና በሰላም ሂጂ” ማለቱን አስታውሰዋል።
ቅዱስ ማርቆስ በጻፈው የጌታችን የኢየሱስ ወንጌል ውስጥ የተገለጸውን ሁለተኛውን ተዓምር ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ሴት ልጁ እንደሞተችበት ተነግሮት የተጨነቀ አባት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ላቀረበው በእምነት የተሞላ ልመና ምላሽ በመስጠት ልጅቱን ከሞት ማስነሳቱን አስታውሰዋል። ኢየሱስም ለዚህ ሰው፥ “አትፍራ ነገር ግን እምነት ብቻ ይኑርህ” ማለቱን አስታውሰው፥ ወደ ሰውዬው ቤት ሄዶ ሁሉም ሰው ሲያለቅስ ባየ ጊዜ፥ “ልጁ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም” ማለቱንም አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “እነዚህ ሁለት የቅዱስ ወንጌል ክፍሎች በእምነት ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የምንቀርብ ከሆነ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር እንደሌለ ይገልጣሉ” ብለዋል።
የኢየሱስ ክርስቶስ ድርጊት ከበሽታ መፈወስ ብቻ ሳይሆን ከሞትም የሚያስነሳ ነው” በማለት አፅንዖት የሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የዘላለም ሕይወት ለሆነው እግዚአብሔር የአካል ሞት እንደ እንቅልፍ እንደሆነ ገልጸው፥ “መፍራት ያለብን እውነተኛ ሞት የነፍስ ሞት ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ሕይወታችንን ከውስጥ መለወጥ
ኢየሱስ ክርስቶስ ልጅቱን ወደ ሕይወት ካመጣት በኋላ የምትበላውን እንዲሰጧት ለወላጆቿ ሲነግራቸው፥ ወደ ሰውነታችን ያለውን ቅርበት የሚያሳይ ሌላ ተጨባጭ ምልክት መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጠቁመዋል።
ይህም ሁኔታውን በጥልቀት እንድንረዳ በማስቻል እራሳችንን እንድንጠይቅ ያደርገናል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እኛ ራሳችንን በቅዱስ ወንጌል ካልመገብን ልጆቻችን በችግር ሲወድቁ እና መንፈሳዊ ምግብ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ እንዴት አድርገን መስጠትን እናውቃለን?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በእያንዳንዱ ተዓምር ላይ በማሰላሰል፥ በእግዚአብሔር ባለን እምነት ላይ የሚያደናቅፈን ነገር እንዳይፈጠር እና አስጨናቂ የሆኑ ሁኔታዎችን እንዴት አድርገን መፍታት እንደምንችል አስረድተው፥ “አንዳንድ ጊዜ እኛ ባናውቅም ነገር ግን በሚስጥር እና በእውነተኛ መንገድ ጸጋው ወደ እኛ ደርሶ ቀስ በቀስ ሕይወታችንን ከውስጥ ይለውጠዋል” ብለዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ ያደርገናል
“ብዙ ጊዜ በርካቶች ይህን ለማስተዋል የዘገዩ ናቸው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ምናልባት ዛሬ ብዙ ሰዎች በኢየሱስ ከስቶስ የመፈወስ ኃይል ሳያምኑ ነገር ግን በውጫዊ መንገድ ብቻ ወደ እርሱ ቀርበው ይሆናል” ብለው፥ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ብንሆንም ነገር ግን ልባችን ሌላ ቦታ ሊሆን ይችላል!” ብለዋል።
“እነዚህ ሁለቱ በቅዱስ ወንጌል ውስጥ የተጠቀሱት ተዓምራት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሊፈውስ የማይችለው ምንም ነገር እንደሌለ እና እርሱ አዲስ የሚያደርገን በመሆኑ ወደ እርሱ እንድንሄድ የሚያሳስቡን ናቸው” በማለት የዕለቱ አስተምህሮአቸውን ደምድመዋል።