ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ብፁዕ ካርዲናል ዩሊዩ ሆሱ የተስፋ ነቢይ ነበሩ” ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሮማኒያ የክሉዥ-ገርላ ሀገረ ስብከት ካቶሊካዊ ጳጳስ የነበሩ የብፁዕ ካርዲናል ዩሊዩ ሆሱ መታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴን ሰኞ ግንቦት 25/2017 ዓ/ ም. በመሩበት ዕለት ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ብፁዕ ካርዲናል ዩሊዩ በሃይማኖቶች መካከል አንድነትን፣ ይቅር ባይነትን እና ምዕመናንም የእርሳቸውን የተስፋ፣ የድፍረት እና የምሕረት ምሳሌ እንዲከተሉ ማበረታታቸውን አስታውሰዋል።
ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ሰኞ ግንቦት 25/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ የተፈጸመው የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ፍራንችስኮስ በሮማኒያ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት 5ኛ ዓመት መታሰቢያ ለማክበር እንደሆነም ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በወቅቱ ካርዲናል ዩሊዩ ሆሱን ጨምሮ ሰባት የግሪክ ካቶሊካዊ ሰማዕታት የብጽዕና ማዕረግ ይፋ ማድረጋቸው ሲታወስ፥ ተግባራዊ የሆነው በሮማኒያ የአይሁድ ማኅበረሰቦች ፌዴሬሽን ተነሳሽነት ከአንድ ዓመት በፊት ለሟቹ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥያቄ ቀርቦ በተደረሰው ስምምነት መሠረት እንደ ነበር ይታወሳል።
ካርዲናል ዩሊዩ ሆሱ ሮማኒያ ኮሚኒስት አገዛዝ ሥር በነበረችበት ወቅት ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1969 ዓ. ም. በእስር እያሉ በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እጅ የካርዲናልነት ማዕረግ መቀበላቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጠቅሰዋል። “ዛሬ በተወሰነ መልኩ ወደዚህ ጸሎት ቤት ገብተዋል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ካርዲናሉ በከባድ ስደት ውስጥ ቢሆኑም ለሮም ቤተ ክርስቲያን ታማኝ ሆነው የቆዩበትን ድፍረት እና ጽናት አስታውሰዋል።
በሮማኒያ የአይሁድ ማኅበረሰቦች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ሲልቪዩ ቬክስለር፣ ለሮማኒያ የግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች፣ ለሲቪል ባለ ስልጣናት እና ሌሎች ተሳታፊዎቹ ባደረጉት ንግግር፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የካርዲናል ዩሊዩ ሆሱ ውርስ ከሁሉም የዘር እና የሃይማኖት ድንበሮች የሚያልፍ የወንድማማችነት ምልክት ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል።
የተጨቆኑት ከጥቃት መከላከል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው፥ “ለካርዲናል ዩሊዩ ሆሱ ‘በአገራት መካከል ጻድቅ የሆነ’ የሚል ማዕረግ ለመስጠት የተካሄደው ሂደት፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1940 እና 1944 መካከል በናዚ ወረራ ወቅት በሰሜናዊ ትራንስሊቫኒያ የሚኖሩ አይሁዶችን ከጉዳት ለመጠበቅ ያደረጉትን ቆራጥ ጥረት መሠረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የካርዲናሉ ተግባር በራሳቸውም ሆነ በግሪክ-ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ ሥጋት መፍጠሩን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ገልጸው፥ አይሁዳውያን እንዳይሰደዱ ለመከላከል ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አስታውሰዋል።
በወቅቱ የነበሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት፥ የካርዲናሉን ድምጽ በመደገፍ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሚያዝያ 2/1944 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክት፥ “ለሁላችሁም የምናቀርብላችሁ አቤቱታችን፥ ዛሬ ከጠንካራ በጎ አድራጊነት የተወለደ ክርስቲያናዊ እና ሮማኒያያዊ ዕርዳታ የበለጠ መልካም ተግባር እንደሌለ አውቃችሁ፥ አይሁዶችን በሃሳባችሁ ብቻ ሳይሆን በመስዋዕትነታችሁም እንድትረዷቸው ነው!” ማለታቸውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አስታውሰዋል።
በሮማኒያ የአይሁድ ማኅበረሰብ የቀድሞ ዋና መምህር የነበሩት ሞሼ ካርሚሊ-ዌይንበርገር በሰጡት ምስክርነት፥ የካርዲናል ዩሊዩ ሆሱ ጣልቃ መግባት በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዶች ሕይወት ከሞት መታደጉን አስታውሰዋል።
በይቅርታ ላይ የተመሠረተ እምነት
ካርዲናል ዩሊዩ ሆሱን፥ “የውይይት ሰው እና የተስፋ ነቢይ” ሲሉ የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2019 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተሰጣቸው የብጽዕና ማዕረግ ሰማዕት እና የክርስቲያናዊ በጎነት አርአያ መሆናቸውን ያረጋገጠ ነው” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ብጽዕናቸው የታወጀላቸው ካርዲናሎች “እግዚአብሔር ወደዚህ የመከራ ጨለማ የላከን ይቅርታ ለማድረግ እና ሁሉም እንዲለወጡ ለመጸለይ ነው” ማለታቸውን በመጥቀስ እንደተናገሩት፥ የይቅርታ ዘላቂ ኃይል ስደትን እና መከራን በመጋፈጥ የሚለውጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
“እነዚህ ቃላት የሰማዕታትን መንፈስ ያካትታሉ” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በእግዚአብሔር ላይ የማይናወጥ እምነት፣ ከጥላቻ የጸዳ ሆኖ ከምሕረት መንፈስ ጋር በመዳመር መከራን የሚያደርሱ አሳዳጆችን ማፍቀር እንደሚገባ የሚያሳስብ ነው” ብለዋል።
ለዛሬው ዓለም መመስከር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካርዲናል ዩሊዩ ሆሱ ምሳሌነት እና “የእኛ ዘመን” በሚለው ሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ አስተምህሮ መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ሲገልጹ፥ ክርስቲያናዊ ካልሆኑ ሃይማኖቶች ጋር ያለውን ግንኙነት በማስመልከት በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ የተጻፈው ሠነድ 60ኛ ዓመቱን ሊያከብር መቃረቡን ተናግረዋል።
“ካርዲናል ዩሊዩ ሆሱ ለሮማኒያ አይሁዶች ያደረጉት ነገር ከፍተኛ መስዋዕትነት ያስከፈላቸው ቢሆንም ዛሬ ግን የነጻነት፣ የድፍረት እና የልግስና አርአያ አድርጎአቸዋል” ብለው፥
ምእመናን “እምነታችን ሕይወታችን ነው” የሚለውን የብጹዕ ካርዲናል ዩሊዩ ሆሱን መሪ ቃል እንደራሳቸው አድርገው እንዲቀበሉ፣ ሁሉንም ዓይነት ጥቃቶች በመቃወም በተለይም መከላከያ በሌላቸው እና አቅመ ደካማ በሆኑት እንደ ህጻናት እና ቤተሰብ ባሉት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን “አሻፈረኝ!” እንዲሉ ጠንካራ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት በሙሉ የእግዚአብሔርን ቡራኬ በመለመን የብፁዕ ካርዲናል ዩሊዩ ሆሱ ምሳሌ ለዛሬው ዓለም ብርሃን ሆኖ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።