ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከጣሊያኑ ፕሬዝደንት አቶ ሴርጆ ማታሬላን ጋር በግል ተገናኙ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከልጆቻቸው እና ከበርካታ የልጅ ልጆቻቸው ጋር ወደ ቫቲካን ከመጡት
የጣሊያን ፕሬዝዳንት አቶ ሴርጆ ማታሬላ ጋር በግል ተገናኝተው ተወያይተዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል እንዳታወቀው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የጣሊያኑን ፕሬዚደንት አቶ ሴርጆ ማታሬላን በሐዋርያዊ መንበራቸው ተቀብለው ማነጋገራቸው ታውቋል።
ፕሬዝደንት ሴርጆ ማታሬላ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ለአንድ ሰዓት ያህል ከተገናኙ በኋላ በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ውስጥ ከብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን እና ከመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ምክትል ዋና ጸሐፊ ከብጹዕ አቡነ ሚሮስሎው ዋቻስኪ ጋር ተገናኝተዋል።
በቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት ውስጥ በተካሄደው ውይይት፥ ከጣሊያን መንግሥት ጋር ለነበረው መልካም የሁለትዮሽ ግንኙነት አድናቆት መሰጠቱን መግለጫው ገልጿል። "በዩክሬን እና በመካከለኛው ምሥራቅ እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች ላይ ትኩረት በማድረግ በዓለም አቀፍ ርዕሠ ጉዳዮች ላይም ውይይት መደረጉን መግለጫው አክሎ አስታውቋል።
በተለይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ከተወያዩባቸው ማኅበራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለጣሊያን መንግሥት የምታደርገውን አስተዋጽኦ እንደሆነ የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።
07 Jun 2025, 14:58