MAP

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ከአውሮጳ አገራት የጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር ተገናኙ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ከአውሮጳ አገራት የጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር ተገናኙ   (@VATICAN MEDIA)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የአውሮፓ ጳጳሳት ለሲኖዶሳዊነት እና ለሰላም የሚያደርጉትን ጥረት አበረታቱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ከአውሮጳ አገራት ካቶሊካዊ ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል። ቅዱስነታቸው ከጳጳሳቱ ጋር በአብያተ ክርስቲያናት አንድነት የጋራ ውይይት፣ ሲኖዶሳዊነትን በሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች ላይ እና በአውሮፓ ውስጥ በመካሄድ ላይ የሚገኘውን የወንጌል ስርጭት በማስመልከት ተወያይተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ሰኔ 21/2017 ዓ. ም. የአውሮፓ ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት (ሲሲኢኢ) ፕሬዚደንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት በቫቲካን ተቀብለው ባደረጉት ውይይት፥ ቤተ ክርስቲያኒቱ በአውሮጳ አኅጉር ውስጥ በክርስቲያኖች አንድነት የጋራ ውይይት፣ በሲኖዶሳዊነት እና በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ላይ ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

ቅዱስነታቸው እሑድ ሰኔ 22/2017 ዓ. ም. በተከበረው የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ዓመታዊ በዓል ላይ የነበሩት የቁስጥንጥንያ የክርስቲያኖች አንድነት የፓትርያርክ ጽሕፈት ቤት ልዑካን ቡድን ጋር ከመገናኘታቸው ቀደም ብሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ያገኙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጊንታራስ ግሩሻስ፥ የአውሮፓ ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት (ሲሲኢኢ) ፕሬዚደንት እና ብፁዕ ካርዲናል ላዲስላቭ ኔሜት፥ የጉባኤዎቹ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚደንት ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ግሩሻስ ከዜና አገልግሎቱ ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የጉባኤዎቹ ምክር ቤት በቀዳሚነት የክርስቲያኖች አንድነትን (CCEE) አስመልክቶ በአውሮፓ ውስጥ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በማስመልከት ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፥ ከሌሎች ዋና ዋና ጭብጦች መካከል በአብያተ ክርስቲያናት መካከል እየተደረገ ባለው የጋራ ውይይት ቀጣይነት የሚል እንደሚገኝበት ታውቋል።

በአውሮፓ ውስጥ የክርስቲያኖች አንድነት

“ከ25 ዓመታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈረመውን እና በኋላ ተሻሽሎ የቀረበውን ‘የክርስቲያኖች አንድነት’ ሠነድ ለመፈረም በዝግጅት ላይ እንገኛለን” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጊንታራስ ግሩሻስ፥ አዲሱ ማዕቀፍ በተለይ በአውሮፓ ውስጥ ለሚገኙ ክርስቲያኖች አንድነት እንደሚያገለግል አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተለይም በሲኖዶሳዊነት አውድ ውስጥ በአውሮጳ አብያተ ክርስቲያናት መካከል የሚደረግ የክርስቲያኖች አንድነት የጋራ ውይይት እንዲቀጥል ምክር ቤቱን ማበረታታቸውን ገልጸዋል። የባህል እና የቋንቋ ስብጥር ባለበት አውሮፓ ውስጥ ሲኖዶሳዊነትን መተግበር ፈታኝ መሆኑን የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጊንታራስ ግሩሻስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የምክር ቤቱን ተልዕኮው ለማስቀጠል ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በመካከለኛው ምሥራቅ እና በአውሮፓ ውስጥ ያለውን አሳሳቢ ጦርነት እና ግጭት ያስታወሱት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጊንታራስ ግሩሻስ፥ ጦርነት ተወግዶ ሰላም እንዲወርድ መጸለይን እና ዲፕሎማሲ ማጠናከርን እንደሚቀጥሉ ተናግረው፥ በዩክሬን ውስጥ ያለውን ዘላቂ ቀውስ እና የሩሲያው ፕሬዚደንት ቪላድሚር ፑቲን ምኞቶች እንደ ችግር ምንጭነት ጠቅሰው፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጥሪ ጋር ከወታደራዊ ወጪዎች ይልቅ ለሰላም እና ለድሆች መቆም እንደሚገባ ተናግረዋል።


እንደገና ማስታጠቅ መፍትሔ ሊሆን አይችልም

የአውሮፓ ጳጳሳት ጉባኤዎች ምክር ቤት (ሲሲኢኢ) ምክትል ፕሬዚደንት ብፁዕ ካርዲናል ላዲስላቭ ኔሜት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በቅርቡ ያቀረቡትን ምክረ ሃሳብ በመደገፍ በሰጡት አስተያየት፥ የጦር ትጥቅ በማስመልከት የተራጩ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በማስጠንቀቅ፥ “ያለ ጦር መሣሪያ ትጥቅ መኖር አንችልም፣ ለሰላም ብቸኛው መፍትሄ የጦር መሣሪያን እንደገና መታጠቅ ነው” በሚል የሚሰራጩ መልዕኮቶች ውብ ቢመስሉም ነገር ግን የተሳሳቱ አስተያየቶች መሆናቸውን አስረድተዋል።

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) ለደቡቡ የዓለማችን ክፍል ወሳኝ የሆነውን ዕርዳታ ማገድ ያስከተለውን ከፍተኛ ጉዳት የጠቀሱት ብፁዕ ካርዲናል ላዲስላቭ ኔሜት፥ መዘዙ በወጣቶች እና በሕጻናት ላይ ሞት ማስከተሉን እና በገንዘብ ድጋፍ መቋረጥ ምክንያት በርካታ ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን አስታውሰዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጊንታራስ ግሩሻስ፥
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጊንታራስ ግሩሻስ፥

ብጹዕ ካርዲናል ላዲስላቭ ኔሜት በአውሮፓ ውስጥ ያለውን የእምነት ሁኔታን በማስመልከት በሰጡት ሰፋ ያለ አስተያየት፥ ከልክ ያለፉ አሉታዊ ግምገማዎች መኖራቸውን ተናግረው፥ እንደሚነገረው ሳይሆን ነገር ግን በጣም ጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በአንዳንድ ክልሎች ያለውን አነስተኛ ተሳትፎ ያልሸሸጉት ብጹዕ ካርዲናል ላዲስላቭ ኔሜት፥ በተለይ በምዕራብ፣ በመካከለኛው እና በምሥራቅ አውሮፓ ውስጥ በወጣቶች መካከል የሚታየው የሃይማኖተኛነት ስሜት ማደግን ጨምሮ አብዛኞቹ የአውሮፓ አገራት ጥሩ ሃይማኖታዊ ሕይወት እንዳላቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኦርቶዶክስ ማኅበረሰቦች አስፈላጊነት

የኦርቶዶክስ ማኅበረሰቦች ሕያውነትን የሚያደንቁት ብጹዕ ካርዲናል ላዲስላቭ ኔሜት፥ በጋራ የመማር አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት በመስጠት ከኦርቶዶክስ ማኅበረሰብ ብዙ መማር እንደሚቻል ገልጸው፥ ስብከተ ወንጌል ወደፊት ስለሚጓዝበት መንገድ ተጠይቀው ሲመልሱ፥ ደፋር ነገር ግን ሁሉን አቀፍ ምሥክርነት መስጠት እንደሚገባ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ ለመናገር የበለጠ ደፋር መሆን፣ ማግለልን፣ ጽንፈኝነትን እና ልዩነትን ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ላዲስላቭ ኔሜት፥
ብፁዕ ካርዲናል ላዲስላቭ ኔሜት፥
30 Jun 2025, 17:16