MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ክርዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና መምህራኖቻቸው ጋር ሲገናኙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ክርዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና መምህራኖቻቸው ጋር ሲገናኙ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች በክኅነታዊ ሕይወት ላይ ጥልቅ ስሜት እንዲኖራቸው አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ለማክበር ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ንግደት ያደረጉ ወደ 4000 የሚጠጉ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎችን እና መምህራኖቻቸውን በቫቲካን ተቀብለዋል። ቅዱስነታቸው በኢየሱስ ቅዱስ ልብ እና በክኅነት ሕይወት ላይ በማሰላሰል ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች በክኅነት ሕይወት ጥልቅ ስሜት እንዲኖራቸው አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎችን እና መምህራኖቻቸው ማክሰኞ ሰኔ 17/2017 ዓ. ም. ተቀብለው ባስተላለፉት መልዕክት፥ የኢዮቤልዩ በዓላቸውን ለማክበር ወደ ሮም የመጡት የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች ነጋዲያን ብቻ ሳይሆኑ የተስፋ ምስክሮችም እንደሆኑ ገልጸው፥ “በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ያለውን የተስፋ ነበልባል የሚያቀጣጥሉ ናቸው” በማለት ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ባሰሙት አስተንትኖ ለዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እንደተናገሩት “ለኢየሱስ ክርስቶስ በሚቀርብ ምስጋና፣ ሐሤት እና ደስታ፣ የልብ ርኅራኄን እና ምሕረት፣ እርስ በእርስ በእንግድነት የመቀባበል እና የመቀራረብ ዘይቤን ለመለማመድ፥ ለጋስ እና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ አገልግሎትን ለመስጠት መንፈስ ቅዱስ ከምስጢረ ክኅነት በፊት ስብዕናቸውን እንዲቀባ መፍቀድ ይገባል ብለዋል።

የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና መምህራን ኢዮቤልዩ

ኢየሱስ እንደሚወድ መውደድ መማር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ የዘርዓ ክህነት ትምህርት አስፈላጊነት ሲገልጹ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደወደደው መውደድን ለመማር የዘርዓ ክህነት ትምህርት በልብ ላይ ያተኮረ መሆን አለበት” ሲሉ አፅንኦት ሰጥተዋል።  

ይህም የውስጣዊ ሕይወት ዕድገት፣ ማለትም በመጀመርያ ማስተዋልን እና ወደ ልብ መመለስን የሚያካትት መሆን እንዳለበት፥ ከዚያም እግዚአብሔር የሚገኝበትን እና የሚናገረንን ቦታ ከማወቅ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል።

“ውስጣዊ ሕይወት ማወቅ የሕይወትን አቅጣጫ ለማወቅ ይረዳል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ ይህም የልብን ጥልቅ ስሜት ማወቅን ይጨምራል ብለዋል። ወደ ውስጣዊነት የሚወስደው ትክክለኛ መንገድ ጸሎት መሆኑን ገልጸው፥ ምክንያቱም “ከእግዚአብሔር ጋር ካልተገናኘን እራሳችንን በትክክል ማወቅ አንችልም” ብለዋል።

የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ደጋግመው እንዲዲገናኙ ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፥ ይህም እግዚአብሔር በእነርሱ ውስጥ፥ በሥነ ጥበብ፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሙዚቃ እና በሳይንስ ውስጥ እንደሚገኝ ማወቅ የሚችል ታዛዥ ልብ እንዲኖር ያደርጋል ብለው፥ ከሁሉም በላይ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳደረገው ሁሉ ሕጻናትን፣ ድሆችን እና የተጨቆኑትን፣ በተለይም የሕይወታቸው ትርጉም ለማግኘት የሚጥሩትን ወጣቶችን ማዳመጥን መማር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፥ የሕይወታቸውን ክስተቶች የመጠበቅ እና የማስተዋል ጥበብን እንዲማሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች ኢዮቤልዩ
የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች ኢዮቤልዩ   (@Vatican Media)

“በክኅነታዊ ሕይወት ጥልቅ ስሜት ይኑራችሁ!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፣ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ የዋህ እና ትሑት ልብ እንዲኖራቸው አደራ ብለው፥ እንደ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በብስለት ለማደግ የኢየሱስ ክርስቶስን ስሜት ለመቀበል ማስመሰልን እና ግብዝነትን ሁሉ መተው እንደሚገባ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በማጠቃለያቸው፥ “የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች ተግባር፥ ተስፋ አለመቁረጥ፣ በትንሽ ነገር ሳይረኩ ነገር ግን ለክኅነታዊ ሕይወት ከፍተኛ ፍቅር እንዲኖራቸው፥ ዛሬን እየኖሩ የወደፊቱን በትንቢታዊ ልብ መመልከት ነው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና መምህራኖቻቸው ጋር የደገሙትን የሐዋርያት ጸሎተ ሃይማኖት ከመምራታቸው በፊት ባስተላለፉት መልዕክት፣ የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንደሚያጠናክሩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ልባቸውን እንደ ልቡ ቅዱስ እንዲያደርግላቸው፥ ለእያንዳንዳቸው እና ለሰው ዘር በሙሉ ፍቅርን የሚያስተምር ልብ እንዲሰጥ በመጠየቅ ንግግራቸውን አጠቃልለዋል።

የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች ኢዮቤልዩ
የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች ኢዮቤልዩ   (@Vatican Media)

 

24 Jun 2025, 16:59