ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ዓለም በርኅራኄ ልብ እንዲሞላ የሚያሳስብ የጸሎት ሃሳብ ይፋ አደረጉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሰኔ ወር የጸሎት ሃሳብ፥ በተለምዶ ዓለም በርኅራኄ እንዲያድግ ወደ ልበ-ኢየሱስ ጸሎት የሚቀርብበትን የሰኔ ወር መሠረት በማድረግ እንደሆነ ታውቋል።
በዚህ መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዓለም አቀፉ የጸሎት አውታረ-መረብ በኩል ለመላዋ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት፥ በተያዘው የሰኔ ወር ውስጥ ምዕመናን በሙሉ ዓለም የርኅራሄ ልብ እንዲኖረው እንዲጸልዩ አደራ ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሚያዝያ 30/2017 ዓ. ም. የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ 266ኛው ር ዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሆነው ከተመረጡ በኋላ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወርሃዊ የጸሎት ሐሳብን ለመጀመሪያ ጊዜ አቅርበዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የሰኔ ወር መልዕክት የሚጀምረው፥ እያንዳንዳችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለን የግል ግንኙነት መጽናናትን በማግኘት፥ ከእርሱ ልብም ርኅራሄን እንድንማር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጸሎት ሲያቀርቡ የሚያሳይ እና ወደ ልበ ኢየሱስ የቀረበ ጸሎት የመጀመሪያ ቅጂ እንደሆነም ተመልክቷል።
ወደ ቅዱስ ልበ-ኢየሱስ የሚቀርብ ጸሎት
የቪዲዮ ቅንብሩ፥ “ጌታ ሆይ! ዛሬ ወደ ርኅሩኅ ልብህ መጥቻለሁ፤ ልቤ በቃሎችህ እንዲቃጠል ወደምታደርግ ወደ አንተ መጥቻለሁ፤ ለተናቁት፣ ለድሆች፣ ለሚሰቃዩት እና መከራ ለደረሰባቸው የሰው ልጆች በሙሉ ወደምትራራ ወደ አንተ መጥቻለሁ!” የሚለው የሴት ድምጽ ጸሎቱን ይመራል።
ቪዲዮው በመቀጠልም፥ ኢየሱስን የበለጠ ለማወቅ፣ በቅዱስ ወንጌል አማካይነት ስለ እርሱ ለማሰላሰል፣ ከእሱ ጋር ለመሆን እና ከእሱ እና ከበጎ አድራጎቱ ለመማር ያለውን ፍላጎትም ይገልጻል።
ጸሎቱ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በመለኮታዊ እና ሰብዓዊ ልቡ የሰውን ልጅ ያለ ልክ በመውደድ የእግዚአብሔር አብ ፍቅር እንዳሳየን በማስታወስ፥ “ልጆችህ በሙሉ ከአንተ ጋር የሚገናኙበትን ጸጋ ስጣቸው!” የሚል እንደሆነ ተመልክቷል።
በዚህ ስሜት፥ እግዚአብሔር በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ጣልቃ በመግባት እንዲቀርበን ይጠይቃል።
“ጌታ ሆይ! ለእቅዶቻችን አዲስ ቅርጽ ስጠው” በማለት የቀጠለው ጸሎቱ፥ “በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ፥ በጸሎት፣ በሥራ፣ በእርስ በርስ ግንኙነት እና በዕለት ተዕለት ተግባራችን አንተን ብቻ እንፈልግ አድርገን” የሚል እንደሆነ ተመልክቷል።
ጸሎቱ በመጨረሻም፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በመገናኘት በዓለም ውስጥ የርህራሄ እና የመጽናናት መልዕክተኞች እንድንሆን ይጠይቃል።
ከዚህ ጸሎት ጋር የተያያዙ ምስሎች የተቀረጹት በሮም በሚገኘው የኢየሱስ ቅዱስ ስም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲሆን፥ እድሳቱ በአቶ ፖምፔ ባቶኒ እየተካሄደ የሚገኘው ታዋቂው የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ምስል በያዝነው የሰኔ ወሩ መጨረሻ ተጠናቅቆ በፊሊፒንስ መዲና ማኒላ ሀገረ ስብከት ውስጥ በማካቲ ወደሚገኝ ብሔራዊ የቅዱስ ልብ ቤተ-መቅደስ እንደሚወሰድ ታውቋል።
ቅዱስ ልበ ኢየሱስ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ልብ ውስጥ
ቤተ ክርስቲያን ሰኔ ወርን ለኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ልብ በትውፊት መስጠቷ ይታወቃል። የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ልብ ከቤተ ክርስቲያን ሕይወት ጋር ያለው አግባብነት፥ በሁለቱም ሕዝባዊ አምልኮ እና አራት ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት ለሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳናቸው ዋና ርዕሥ አድርገው መምረጣቸውን ያመለክታል።
የወቅቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ስማቸውን የወሰዱት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ ሦስተኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1899 ዓ. ም. “ቅዱስ ዓመት” በማለት ለጻፉት ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳናቸው ዋና ርዕሥ በማድረግ፥ በዚህም መላውን የሰው ልጆች በልበ ኢየሱስ መቀደሳቸው ይታወሳል።
እንደዚሁም የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዩስ 11ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1928 ዓ. ም. “እጅግ ቤዛ” በሚለው ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳናቸው፥ ኃጢአታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ላይ ላስከተለው ቁስል የፍቅር ሥራን በመሥራት እንድንክስ መጋበዛቸው ይታወሳል።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛም በበኩላቸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1956 ዓ. ም. “ውሃ ትቀዳለህ” በማለት ባሳተሙት ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳናቸው፥ ለቅዱስ ልብ የሚሰጠውን ሥነ-መለኮታዊ መሠረት መቃኘታቸው ይታወሳል።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. “እርሱ ወደደን” በማለት በጻፉት ሐዋርያዊ ቃለ-ምዕዳናቸው፥ ለንቀት እና ግዴለሽነት ባህል ምላሽ ለመስጠት የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ልብን ማቅረባቸው ይታወሳል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ ቪዲዮ
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቪዲዮ ኦፊሴላዊ ዓለም አቀፍ ተነሳሽነት፥ የቅዱስ አባታችንን ወርሃዊ የጸሎት ሃሳብ ወደ መላው ዓለም ለማድረስ ዓላማ ያለው እንደሆነ ይታወቃል።
የሚከናወነውም በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት መረብ ወይም የጸሎት ሐዋርያነት አማካይነት እንደሆነ ይታወቃል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቪዲዮ እንደ ጎርጎሮሳውያን ከ 2016 ዓ. ም. ጀምሮ በሁሉም የቫቲካን ማኅበራዊ ሚዲያ አውታረ መረቦች አማካይነት ከ 247 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች አሉት እና ከ 23 በላይ ቋንቋዎች ተተርጉሞ በ 114 አገሮች ውስጥ ሽፋን ማግኘቱ ታውቋል።
የሚዘጋጀውም በአንድሪያ ሳሩቢ አስተባባሪነት በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቪዲዮ የጸሎት አውታረ መረብ ቡድን እና “በኮሮኔሽን ሚዲያ” ረዳትነት ተሠርቶ በ “ላ ማኪ” ኤጀንሲ እና በቫቲካን ሚዲያ ትብብር የሚሰራጭ መሆኑ ታውቋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት አውታረ መረብ ጳጳሳዊ ማኅበር ሲሆን፥ ካቶሊክ ምዕመናንን በጸሎት እና በተጨባጭ ተግባር የማሰባሰብ ተልዕኮ ያለው፣ ለሰው ልጅ እና ለቤተ ክርስቲያን ተግዳሮቶች ምላሽ ለመስጠት ተልዕኮ ያለው እንደ ሆነ ታውቋል።