ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ማንም ሰው አሸናፊ ወይም ቅዱስ ሆኖ አልተወለደም” ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ በዓላቸውን ለማክበር ከተለያዩ የስፖርት ዓይነቶች ለተወጣጡ በሺዎች ለሚቆጠሩ ስፖርተኞች፥ በቅድስት ሥላሴ እና በስፖርት መካከል ያለውን ግንኙነት በማስመልከት ባሰሙት ስብከት፥ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት ያልተለመደ ይምሰል እንጂ እያንዳንዱ የሰው ልጅ መልካም ተግባር የእግዚአብሔርን ወሰን የለሽ ውበት በተወሰነ መንገድ የሚያንጸባርቅ በመሆኑ ስፖርትም ከእነዚህ መልካም ተግባሮች መካከል አንዱ ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።
ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ ስፖርት ከሁሉም በላይ በውጭ ብቻ ሳይሆን በውስጣችን ከሌሎች እና እንዲሁም ከእግዚአብሔር ጋር እንድንገናኝ ሊረዳን የሚችል እንደ ሆነ ገልጸው፥ “ይህ ካልሆነ ስፖርት ትርጉም የሌለው ባዶ ፉክክር ብቻ ይሆናል” ብለዋል።
ስፖርት መሰጠትን ይጠይቃል
በስፖርት ውድድሮች ላይ ተመልካቾች ተጫዋቾችን ለማበረታታት የሚጠቀሙበት “ዳይ” የሚለውን የጣሊያን ቃል ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ትርጉሙም “መስጠት” ማለት እንደሆነ በማስታወስ፥ ሁሉም ሰው በዚህ ቃል ላይ እንዲያሰላስል አሳስበዋል። “ስፖርት ከአካላዊ ግንኙነት በላይ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ተውዳዳሪዎች ራሳቸውን ለግላዊ መሻሻል፣ ለደጋፊዎቻቸው፣ ለሚወዷቸው፣ ለአሰልጣኞቻቸው፣ ለጓደኞቻቸው፣ ለሰፊው ሕዝብ እና ለተጋጣሚዎቻቸውም ጭምር አሳልፈው እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፥ “ስፖርት የሕይወት ደስታ፣ ውድድር እና በዓል ነው” ማለታቸውን የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፥ “ለሌሎች ደስታን የሚሰጥ፣ የወዳጅነት ትስስርን የሚፈጥር፣ ውይይቶችን እና ግልጽነትን የሚያበረታታ በመሆኑ መደገፍ አለበት” ብለዋል።
በብቸኛ እና በዲጂታል ዓለም ውስጥ የሚወዳደር ማኅበረሰብ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ስፖርት ሰብዓዊ እና ክርስቲያናዊ እሴቶችን ለማዳበር ጥሩ መንገድ ነው” በማለት በጠቆሟቸው ሦስት ነጥቦች፥ ብቸኝነት ያጠቃው፣ ዲጂታል ማኅበረሰብ እና ተወዳዳሪ ማኅበረሰብ እንደ ሆነ ገልጸዋል።
“እኛ” ከሚለው “እኔ” ወደሚለው የተቀየረውን የብቸኝነት ማኅበረሰብ በቅድሚያ የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፥ ይህም ለሌሎች ያለው አሳቢነት እንዲቀንስ ማድረጉን ገልጸው፥ ሆኖም ግን ልዩ ልዩ ስፖርቶች ለዚህ ጉድለት መፍትሄ ሊሰጡ እንደሚችሉ በማስረዳት፥ ስፖርት ተባብሮ የመሥራትን እና የመጋራትን ጥቅም እንደሚያስተምር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጠቁመዋል።
በሁለተኛ ደረጃ፥ ስፖርቶች የዕርቅ እና በሕዝቦች እና በማኅበረሰቦች መካከል፣ በትምህርት ቤቶች፣ በሥራ ቦታዎች እና በቤተሰቦች መካከል ጠቃሚ የእርስ በርስ መገናኛ መንገዶች ሊሆኑ እንደሚችሉ አስረድተዋል። ዲጂታል የመገናኛ መንገድን በየዕለቱ እየተጋፈጠ የሚገኘውን ማኅበረሰብ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ስፖርቶች ሰዎችን ሊከፋፍሉ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለመቋቋም እንደሚረዱ አሳስበዋል።
ስፖርቶች ምናባዊውን ዓለምን ወደ ጎን በማለት ሌሎች አማራጮችን ሊሰጡ እንደሚችሉ ተናግረው፥“ስፖርቶች ከተፈጥሮ እና ከእውነተኛው ሕይወት ጋር ጤናማ ግንኙነት እና እውነተኛ ፍቅር እንዲኖረን ይረዳሉ” ብለዋል።
በሦስተኛ ደረጃ፥ ጠንካራ እና አሸናፊ የሚመስለውን ተፎካካሪ ማኅበረሰብ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ስፖርት በሌላ በኩል መሸነፍንም እንደያስተምረን ገልጸው፥ “በሰው ልጅ ሁኔታ ውስጥ ካሉት ጥልቅ እውነቶች መካከል አንዱን ማለትም ደካማ ጎናችንን፣ አቅማችንን እና ጉድለቶችን እንድንጋፈጥ ያስገድደናል” ብለው፥ በነዚህ ልምዶች አማካኝነት ልባችን ለተስፋ የሚከፍት በመሆኑ ስፖርት አስፈላጊ እንደሆነ አስረድተዋል።
“ፈጽሞ የማይሸነፉ ወይም የማይሳሳቱ ተወዳዳሪዎች አሉ” የሚለውን ሃሳብ ውድቅ ያደረጉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “አሸናፊ ስፖርተኞች ዘወትር በትክክል የሚሠሩ ማሽኖች አይደሉም” ብለው፥ ነገር ግን እውነተኛ ተወዳዳሪዎች በሚሸነፉበት ጊዜ ወደ ድል ለመመለስ ድፍረትን ያገኛሉ” ሲል ገልጸዋል።
“ማንም ሰው አሸናፊ ሆኖ አልተወለደም”
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፥ ቅዱስ ለመሆን የተፈጠሩ ብቸኛው ቅዱስ አይደሉም” ብለው፥ ውድድሮች በብዙ የዘመናችን ቅዱሳን ሕይወት ውስጥ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን፥ እንደ ግል ተግሣጽ እና እንደ የወንጌል ማስተማሪያነት ማገልገላቸውንም አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ዘንድሮ በጳጉሜ 2/2017 ዓ. ም. ቅድስናው የሚታወጅለት የአትሌቶች ባልደረባ የሆነውን ብፁዕ ፒየር ጆርጆ ፍራሳቲን በማስታወስ እንደተናገሩት፥ “ማንም አሸናፊ ሆኖ ያልተወለደ እና ማንም ቅዱስ ሆኖ ያልተወለደ መሆኑን የብጹዕ ፒየር ጆርጆ ፍራሳቲን ሕይወት እንደሚያሳይ በመጠቆም፥ የዕለት ተዕለት ስልጠናችን በመጨረሻ ወደ አሸናፊነት እርምጃ ሊያስጠጋን ይችላል” ሲሉ አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በስብከታቸው ማጠቃለያ ለተወዳዳሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ተወዳዳሪዎች በጥረታቸው መካከል ለቅድስት ሥላሴ፣ ለራስ፣ ለወንድም እና ለእህት ባላቸው ፍቅር ላይ እንዲያሰላስሉ እና ከሁሉም ወደሚበልጥ ወደ ዘላለም ሕይወት እንዲደርሱ ለምትረዳቸው ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ራሳቸውን እንዲሰጡ አሳስበዋል።