MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “በብስጭት ምክንያት ሕይወታችን ሊደናቀፍ አይገባም” ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ የእኛ ተስፋ!” የሚለውን የኢዮቤልዩ ዓመት መሪ ሃሳብ መሠረት በማድረግ ሳምንታዊውን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን አቅርበዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ረቡዕ ሰኔ 11/2017 ዓ. ም. ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት እና ምሳሌ በማስመልከት ባቀረቡት አስተምህሮ፥ “ሕይወታችን በብስጭት ምክንያት መደናቀፍ የለበትም” ሲሉ አሳስበዋል።

ክቡራት ክቡራን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን፥ ያስተነተኑበትን የቅዱስ ወንጌል ጥቅስ እናነብላችኋለን፥

“በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ቤተሳይዳ የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት። በእነዚህም ውስጥ ብዙ ድኩማን፥ ዓይነ ሥውሮች፥ አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሰዎች ይተኙ ነበር። አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውሃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውሃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ይፈወስ ነበር። በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው።ሕመምተኛውም “ጌታ ሆይ! ውሃው በተናወጥ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም፤ ነገር ግን እኔ በመምጣት ላይ እያለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” ብሎ መለሰለት። ኢየሱስ “ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ፤” አለው። ወዲያውም ሰውየው ዳነ፤ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ። ያም ቀን ሰንበት ነበረ።” (ዮሐ. 5: 2-9)።

ክቡራት እና ክቡራን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ከሕመም በሚፈውስ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ማሰላሰላችንን እንቀጥላለን። በተለይ እንደተዘጋብን እና የሞት መጨረሻን ያህል በሚሰሙን ነገሮች ላይ እንድታሰላስሉባቸው እጋብዛችኋለሁ። አንዳንድ ጊዜ በእውነቱ ተስፋ ማድረግን መቀጠል ትርጉም የለሽ ይመስላል። አቅም ሲወሰድብን የመዋጋት ፍላጎት የለንም። ይህ ሁኔታ በወንጌላት ውስጥ በሽባ ምስል ተገልጿል። ለዚህም ነው ዛሬ በዮሐ. 5፡2-9 ላይ ስለተጻፈው የሽባ ሰው ፈውስ ታሪክ ላይ የምናተኩረው።

ኢየሱስ ለአይሁዶች በዓል ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ። ወዲያውኑ ወደ ቤተመቅደስ አልሄድም። ይልቁን በጎች ለመሥዋዕትነት ከመቅረባቸው በፊት ታጥበው ወደነበሩበት ሄዶ ቆመ። በዚህ በር አጠገብ እንደ በጎቹ እንደ ርኩስ ተቆጥረው ከቤተ መቅደሱ የተገለሉ ብዙ ድውያን ነበሩ። በመከራቸው ወቅት የሚደርስላቸው ኢየሱስ ራሱ ነው። እነዚህ ሰዎች ዕጣ ፈንታቸውን ሊለውጥ የሚችል አንድ ተአምር ተስፋ ያደርጉ ነበር።  በእርግጥም ውሃው ንጹሕ እና መፈውስ እንደሚችል የሚታሰብ አንድ ኩሬ በበሩ አጠገብ ነበር። በተወሰኑ ጊዜያት ውሃው ይናወጥ ስለ ነበር በጊዜው እምነት መሠረት ወደ ኩሬው ቀድሞ የገባ ሁሉ ይድናል።

በዚህ ሁኔታ ወደ ኩሬው ቀድሞ መግባት በማይችሉ አቅመ ደካማ ሕመምተኞች መካከል ‘ጦርነት’ ተፈጠረ። እነዚህ ሕመምተኞች የደከሙ በመሆናቸው ወደ ኩሬው ለመግባት ራሳቸውን እየጎተቱ የሚሄዱበትን አሳዛኝ ሁኔታ መገመት እንችላለን። ያ ኩሬ ወይም የውሃ ገንዳ ቤተዛታ ተብሎ ይጠራ ነበር። ትርጉሙም ‘የምሕረት ቤት’ ማለት ነው። ‘የምሕረት ቤት’ ተብሎ የሚጠራው ይህ ቦታ፥ በኃጢአታቸው ምክንያት የቆሰሉት በሙሉ እግዚአብሔር የሚሰጠውን ፈውስ እና ተስፋ ለመቀበል የሚሰበሰቡባት የቤተ ክርስቲያን ምስል ሊሆን ይችላል።

ኢየሱስም ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል ሽባ ሆኖ ለቆየ አንድ ሰው ተናገረ። ያ ሰው በጊዜው የሚያደርገውን አጥቶ ተስፋ የቆረጠ ሰው ነበር። ምክንያቱም ውኃው ​​ሲንቀሳቀስ ራሱን ወደ ውሃው ውስጥ ማጥለቅ ፈጽሞ አይችልም ነበርና (ዮሐ. 5:7)። እንደ እውነቱ ከሆነ እኛን ብዙ ጊዜ የሚያደናቅፈን ብስጭት ነው፤ ተስፋ መቁረጥ ነው፤ በግዴለሽነት ውስጥ የመውደቅ አደጋም አለ።

ኢየሱስ ሽባውን ‘ልትድን ትወዳለህን?’ ብሎ ጠየቀው (ዮሐ. 5:6)። ይህ አስፈላጊ ጥያቄ ነበር። ምክንያቱም አንድ ሰው ለብዙ ዓመታት በሕመም ተሰቃይቶ ሲቆይ የመፈወስ ፍላጎት እንኳ ሊጠፋ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ሌሎች እንዲንከባከቡን በማስገደድ በበሽታ ውስጥ መቆየትን እንመርጥ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ ምን ማድረግ እንዳለብን ላለመወሰን የምናቀርበው ሰበብ ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ይህንን ሰው ወደ እውነተኛ እና ጥልቅ ፍላጎት ወሰደው።

ይህ ሽባ ሰው ኢየሱስ ላቀረበለት ጥያቄ ይበልጥ ግልጽ በሆነ መንገድ መለሰ። ይህም እውነተኛ የሕይወት ራዕይውን ያሳያል። በመጀመሪያ በመዋኛ ኩሬ ውስጥ የሚያስገባ ማንም እንደሌለው ተናገረ። ስለዚህም እርሱን መንከባከብ የነበረባቸው ሌሎች ሰዎች እንጂ እርሱ አይወቀስም። ይህ አመለካከት ከተጠያቂነት ለመራቅ መነሻ ይሆናል። ነገር ግን እርሱን የሚረዳ ሰው አለመኖሩ እውነት ነው? የቅዱስ አጎስጢኖስ ግልጽ መልስ እነሆ፡- በእርግጥ ለመፈወስ ‘ሰው’ ያስፈልገዋል፣ ነገር ግን ያ ‘ሰው’ እግዚአብሔር ራሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንግዲህ የሚፈለገው ሰው መጣ፤ ስለዚህ ፈውሱ ለምን ይዘገያል?”

ሽባው ሰው አክሎም፥ ወደ ውሃው ለመግባት ሲሞክር ዘወትር የሚቀድመው ሰው እንዳለ ነገረው። ይህ ሰው ስለ ሕይወት ያለውን ሰንካላ አመለካከትን እየገለጸ ነው። መጥፎ የሆኑ ነገሮች የሚደርሱብን ዕድለኞች ባለመሆናችን ወይም ዕጣ ፈንታችን ስለሆነ ነው ብለን እናስባለን። ይህ ሰው ተስፋ ቆርጧል። በሕይወት ትግል ውስጥ እንደተሸነፈ ይሰማዋል።

ኢየሱስም የዚህ ሰው ሕይወት በእጁ እንዳለ እንዲያውቅ አገዘው። ከከባድ ሕይወትም እንዲወጣ እና አልጋውንም ተሸክሞ እንዲሄድ ጋበዘው (ዮሐ. 5:8)። ያ ምንጣፍ ያለፈውን ሕመም እና ታሪኩን የሚወክል በመሆኑ መተው ወይም መጣል የለበትም። እስከዚያ ቅጽበት ድረስ ያለፈው የመከራ እና የሕመም ጊዜ ከምንም አግዶት ቆይቷል። ራሱን እንደሞተ ሰው አድርጎ እንዲዋሽ አስገድዶታል። አሁን ያን ምንጣፉን ወደፈለገው ቦታ መውሰድ ይችላል። ታሪኩን ምን ማድረግ እንደሚችል መወሰን ይችላል! ሃላፊነትን ወስዶ በእግሩ መሄድ በመቻሉ የትኛውን መንገድ መምረጥ እንዳለበት ወደማወቅ የደረሰ በመሆኑ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና ይድረሰው!

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! ሕይወታችን የቱጋ እንደተደናቀፈ ለማወቅ የሚያስችለንን የማስተዋል ስጦታ እንዲሰጠን እግዚአብሔርን እንጠይቀው። ከሕመማችን ለመፈወስ ያለንን ፍላጎት ለመግለጽ እንሞክር። መውጫውን ማየት ለማይችሉ እና ሽባ እንደሆኑ ለሚሰማቸው ሁሉ እንጸልይላቸው። እውነተኛ የምሕረት ቤት ወደ ሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ውስጥ ለመመለስ እንጠይቅ!”

 

 

 

18 Jun 2025, 17:25