ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ቤተሰቦች የሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምንጭ ናቸው!”
እሑድ ግንቦት 24/2017 ዓ. ም. ጠዋት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ በቀረበው የቤተሰብ፣ የሕፃናት፣ የአያቶች እና የአዛውንቶች ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል ማጠቃለያ መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ ቤተሰብ የአንድነት እና የእምነት ምንጭ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
ክቡራት እና ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ግንቦት 24/2017 ዓ. ም. ከዮሐ. ምዕ. 17 ተወስዶ በተነበበው ላይ በማስተንተን ያሰሙትን አስተንትኖ ትርጉም ሙሉ ይዘት ከዚህ ቀጥሎ እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“አሁን ሲነበብ የሰማነው ቅዱስ ወንጌል፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በመጨረሻው እራት ላይ በእኛ ስም ያቀረበውን ጸሎት ይገልጻል (ዮሐ. 17፡20)። ስጋን ለብሶ ሰው የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በምድራዊ ሕይወቱ ፍጻሜ ላይ በእኛ ወንድሞቹ እና እህቶቹ ስም ወደ አባቱ ዘንድ ያቀረበው ጸሎት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የልመና፣ የምስጋና እና የቡራኬ ጸሎት ሆኗል። ለእግዚአብሔር ፍቅር ምስጋና ይግባውና፥ እኛ እራሳችን በአስደናቂ ሁኔታ በመታመን በኢየሱስ ጸሎት ውስጥ ስንገባ የሰውን ልጅ በሙሉ የሚመለከት የታላቅ እቅድ አካል እንሆናለን።
ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ ሁላችን አንድ እንድንሆን ወደ አባቱ ዘንድ ዘወትር ይጸልያል (ዮሐ. 17:21)። ልንመኘው የምንችለው ትልቁ መልካም ነገር ይህ ነው። ምክንያቱም ይህ ዓለም ጠቅላላ አንድነት በፍጡራኑ መካከል ዘላለማዊ የአንድነት ፍቅር የሆነው እግዚአብሔር የሚያመጣ በመሆኑ ነው።
በዚህ አንድነት ውስጥ ስም እና መልክ አልባ ሕዝቦች እንድንሆን እግዚአብሔር አይፈልግም። አንድ እንድንሆን ይፈልጋል፤ ‘አንተም አባት ሆይ! በእኔ እንዳለህ እና እኔም በአንተ እንዳለሁ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ እንዲሆኑ’ (ዮሐ. 17:21)። ኢየሱስ ክርስቶስ የሚጸልይበት አንድነት እግዚአብሔር በሚፈልገው የአንድነት ፍቅር ላይ የተመሠረተ ሲሆን፥ ይህም ሕይወትን እና ድነትን ወደ ዓለም ያመጣል። ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ከሁሉ አስቀድሞ ሊያመጣ የወደደ ስጦታ ነው። የእግዚአብሔር ልጅ በሰብዓዊ ልቡ ወደ አባቱ ዘንድ በዚህ ቃል ይጸልያል፡- ‘እኔ በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በፍጹም አንድ እንዲሆኑ፥ አንተ እንደ ላክኸኝ እና በወደድከኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ዓለም እንዲያውቅ ነው’ (ዮሐ. 17:21)።
እስቲ እነዚህን ቃላት በአድናቆት እናዳምጥ። ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር እኛን የሚወደን እርሱን እንደወደደው እንደሆነ ይነግረናል። እግዚአብሔር እኛን የሚወደን አንድያ ልጁን ከወደደው ባነሰ መንገድ አይደለም። በሌላ አነጋገር ወሰን በሌለው ፍቅር ይወደናል ማለት ነው። እግዚአብሔር ለአንዲያ ልጁ ካለው ፍቅሩ ባነሰ ሁኔታ እኛን አይወደንም፤ ምክንያቱም እርሱ ገና ከመጀመሪያው አንስቶ ዓለምን ወዷልና። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ለአብ እንዲህ ሲል ይመሰክራል፡- ‘አባት ሆይ! ዓለም ሳይፈጠር በፊት ስለወደድከኝ (ዮሐ. 17:24)። እግዚአብሔር በምሕረቱ ዘወትር ሰዎችን በሙሉ ወደ ራሱ መሳብ ይፈልጋል። አንድ የሚያደርገን እና እርስ በርሳችን አንድ እንዲሆን የሚያደርገን በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት በሰጠን ሕይወቱ ነው።
ዛሬ የቤተሰብ፣ የልጆች፣ የአያቶች እና የአረጋውያን ኢዮቤልዩ ክብረ በዓል በሚከበርበት ወቅት ይህን የወንጌል መልዕክት ማዳመጥ በደስታ ይሞላናል።
ወዳጆቼ ሆይ! ከመመኘታችን አስቀድመን ሕይወት አግኝተናል። ንፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የጎርጎሮሳውያኑን አዲስ ዓመት መግቢያ በማስመልከት ታኅሳስ 23/2017 ዓ. ም. ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት፥ ‘እኛ ሁላችን የእግዚአብሔር ልጆች ነን። ነገር ግን እንዲህ ለመሆን አልመረጥንም’ ይህ ብቻ አይደለም! ልክ እንደተወለድን በሕይወት ለመኖር የሌሎች ዕርዳታ ያስፈልገናል። ብቻችን ብንቀር በሕይወት አንተርፍም ነበር። ሌላ ሰው በሥጋ እና በመንፈስ በመንከባከብ አድኖናል። እርስ በርስ ባለን ግንኙነት፣ በሰዎች ደግነት እና እንክብካቤ ዛሬ በሕይወት ለመቆየት ችለናል።
ያ የሰዎች ደግነት አንዳንድ ጊዜ ይከዳል። ለምሳሌ ነፃነት ሕይወትን ለመስጠት ሳይሆን ለመንጠቅ፣ ለመርዳት ሳይሆን ለመጉዳት በሚነሳበት ጊዜ የሰዎች ደግነት ይጠፋል። ነገር ግን በክፋት ምክንያት ሕይወት በሚጠፋበት ጊዜ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ወደ አባቱ ዘንድ መጸለዩን ቀጥሏል። ጸሎቱ ለቁስላችን ማስታገሻ ይሆናል። ስለ ይቅርታ እና ስለ እርቅ ይነግረናል። ያ ጸሎት አንዳችን ለሌላው እንደ ወላጅ ቤተሰብ፣ እንደ አያት፣ እንደ ወንድ እና ሴት ልጆች ያለንን የፍቅር ተሞክሮ ሙሉ ትርጉም ያለው ያደርገዋል።
ለዓለም ልንመሰክር የምንፈልገውም ይህን ነው! እግዚአብሔር አባታችን አንድ እንድንሆን እንደሚፈልግ ሁሉ በቤተሰባችን፣ በምንኖርበት አካባቢ፣ በሥራ ገበታችን እና በትምህርት ቤት አንድ እንድንሆን ተጠርተናል። ልዩ ልዩ ብንሆንም ነገር ግን አንድ ነን! ብዙዎች ብንሆንም ነገር ግን አንድ ነን! በሁሉም ሁኔታዎች እና የሕይወት ደረጃዎች መካከል ዘወትር አንድ ነን።
ወዳጆች ሆይ! በዚህ መንገድ እርስ በርሳችን የምንዋደድ ከሆነ፣ አልፋና ኦሜጋ፣ መጀመሪያ እና የመጨረሻ በሆነ በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረትን ከሆነ (ራዕ. 22፡13)፣ በሁሉም ዘንድ በማኅበረሰብ እና በዓለም ውስጥ በሙሉ የሰላም ምልክት እንሆናለን። ቤተሰቦች የሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ፈንታ መነሻ፣ መሠረት ወይም ምንጭ መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም።
ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ፣ በደስታ የሚሞላንን ነገር ብናገኝም እንድናስብ የሚያደርግ ምልክትም አለ። በርካታ ባለትዳሮች ወደ ብጽዕና እና ወደ ቅድስና ደረጃ የደረሱት በመለያየት ሳይሆን እንደ ባለትዳሮች አንድ ላይ መቆየት በመቻላቸው ነው።
የሕፃኑ ኢየሱስ ቅድስት ቴሬዛ ወላጆች ሉዊስ እና ዜሊ ማርቲንን፣ ብጹዕ ሉዊጂን እና ማርያ ቤልትራም ኳትሮኪ የተባሉ ያለፈው ክፍለ ዘመን የሮም ከተማ ቤተሰቦችን አስታውሳለሁ። በፍቅር እና በሰማዕትነት የተዋሃዱ ከፖላንድ የመጡ የኡልማ ወላጆች እና ልጆች አንርሳ። እንድናስብ የሚያደርግ ምልክት ያልኩት ይህን ነው።
እነዚህ ሰዎች ለትዳር ሕይወት ምስክሮች መሆናቸውን በመጠቆም፥ የዛሬው ዓለም ግንኙነቶችን እና ማኅበራዊ አንድነትን የሚያፈርሱ ሃይሎችን በማሸነፍ የአንድነት እና የዕርቅ ሃይል የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍቅር ለማወቅ እና ለመቀበል የጋብቻ ቃል ኪዳን አስፈላጊ መሆኑን ቤተ ክርስቲያን ትነግረናለች።
በዚህ ምክንያት በምስጋና እና በተስፋ በተሞላ ልብ ሁሉም ባለትዳሮች ጋብቻ ሃሳባዊ ሳይሆን ነገር ግን በወንድ እና በሴት መካከል ያለው የእውነተኛ ፍቅር መለኪያ መሆኑን አስታውሳለሁ። ፍፁም ፍቅር ታማኝ እና ፍሬያማ እንደ ሆነ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፥ ‘የሰው ልጅ ሕይወት’ በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው በቁ. 9 ላይ ገልጸዋል። ይህ ፍቅር አንድ ሥጋ በማድረግ በእግዚአብሔር አምሳል የሕይወት ስጦታን እንድትሰጡ ያስችላችኋል።
እንግዲያውስ ለልጆቻችሁ የአንድነት ምሳሌ እንድትሆኑ፣ እንዲሠሩ በምትፈልጉት መንገድ እንድትሠሩ፣ በነፃነት ታዛዥ እንዲሆኑ እንድታስተምሯቸው፣ ሁልጊዜም በውስጣቸው ያለውን መልካም ነገር እንድትመለከቱ እና ለመንከባከብ የሚያስችሉ መንገዶች እንድትፈልጉ አበረታታችኋለሁ። እናንተ ውድ ልጆች ሆይ! ወላጆቻችሁን አመስግኑ። ለሕይወታችሁ በስጦታነት በየቀኑ ለሚመጣው ሁሉ በየቀኑ አባቶቻችሁን እና እናቶቻችሁን ማመስገን ለምትሰጧቸው ክብር የመጀመሪያው መንገድ ነው (ዘጸ. 20፡12)። በመጨረሻም ውድ አያቶች እና አረጋውያን፥ የምትወዳቸውን ሰዎች በጥበብ እና በርህራሄ እንዲሁም ከዕድሜ ጋር በሚመጣው ትህትና እና ትዕግስት እንድትጠብቋቸው እመክራለሁ።
በቤተሰብ ውስጥ እምነት በሕይወት ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል። እንደ ምግብ በቤተሰብ ጠረጴዛ እና እንደ ፍቅርም በልባችን ውስጥ ይጋራል። በዚህ መንገድ ቤተሰቦች ሁል ጊዜ የሚወደንን እና የእኛን መልካም የሚሻ ኢየሱስ ክርስቶስን የሚያገኙበት ልዩ ቦታ ይሆናሉ።
በመጨረሻም፥ በክርስቲያናዊ ጉዟችን ላይ ተስፋን የሚሰጥ የእግዚአብሔር ልጅ ጸሎት አንድ ቀን ሁላችን አንድ እንደምንሆን ያሳስበናል (የቅዱስ አውጎስጢኖስ ስብከት ቁ. 127)። ይህ አንድነት አዳኝ በሆነው በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍቅር ውስጥ ይገኛል። እኛን ብቻ ሳይሆን አባቶቻችንን፣ እናቶቻችንን፣ አያቶቻችንን፣ ወንድሞቻችንን፣ እህቶቻችንን እና ልጆቻችንን እንዲሁም ወደ ዘላለማዊው ብርሃን ቀድመው የሄዱትም ጭምር በዚህ መስዋዕተ ቅዳሴ ወቅት ከእኛ ጋር መሆናቸው እንዲሰማን ያደርገናል።”