MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሮም አቅራቢያ “ሳንታ ማሪያ ዲ ጋለሪያ” በተባለ አካባቢ የሚገኘውን ማሰራጫ ሲጎበኙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሮም አቅራቢያ “ሳንታ ማሪያ ዲ ጋለሪያ” በተባለ አካባቢ የሚገኘውን ማሰራጫ ሲጎበኙ  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ከሮም ወጣ ብሎ የሚገኘውን የቫቲካን ሬዲዮ ማሰራጫ ማዕከልን ጎበኙ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የክኅነታቸው አርባ ሦስተኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ በሮም አቅራቢያ “ሳንታ ማሪያ ዲ ጋለሪያ” በተባለ አካባቢ የሚገኘውን የቫቲካን ሬዲዮ የአጭር ሞገድ ማሰራጫ ማዕከልን ጎብኝተዋል። የማሰራጫ ማዕከሉ በቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ሥር ከሚገኙ መምሪያዎች መካከል አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። ቅዱስነታቸው የማዕከሉ ሠራተኞች በበዓላት ቀንም ጭምር በታማኝነት ቀጣይነት ባለው መልኩ ለሚሰጡት አገልግሎት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛው በቫቲካን ግዛት እና በጣሊያን መንግሥት መካከል በተደረገው የላተራን ስምምነት የሚተዳደረውን የቫቲካን ሬዲዮ የአጭር ሞገድ ማሰራጫ ማዕከልን ሐሙስ ሰኔ 12/2017 ዓ. ም. ማለዳ የጎበኙት ሲሆን፥ በዕለቱ የክኅነታቸውን 43ኛ ዓመት በማስመልከት የተዘጋጀውን አነስተኛ የመታሰቢያ በዓልን ከማዕከሉ ሠራተኞቹ ጋር አክብረዋል።

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ወደ ሥፍራው ለተጓዙት ጋዜጠኞች በቴሌግራም ባስተላለፈው መልዕክት፣ ቅዱስነታቸው ከማዕከሉ ሠራተኞች ጋር ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቆ፥ በአርክቴክት ፒየር ሉዊጂ ኔርቪ የተነደፈውን የአጭር ሞገድ ማሰራጫ አዳራሽ እና የስርጭት መቆጣጠሪያ ክፍልን መጎብኘታቸውን ገልጿል።

የሬዲዮ ማዕከሉ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1957 ዓ. ም. በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ የተመረቀ ሲሆን፥ በሳንታ ማርያ ዲ ጋለሪያን በሚባል አካባቢ የሚገኘው የሬዲዮ ማሰራጭ ማዕከልን ለመጨረሻ ጊዜ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1991 ዓ. ም. የጎበኙት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ እንደ ነበሩ ይታወሳል።

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ማሰራጫ ማዕከሉን በጎበኙበት ወቅት ስለ አንቴናዎች አሠራር፣ ስርጭቶች እና የዲጂታል አደጋን የመከላከል ሥርዓትን በማስመልከት መጠየቃቸው አስታውሷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፣ በላቲን አሜሪካ እና በአፍሪካ በሚስዮናዊነት ባገለገሉበት ወቅት የቫቲካን ሬዲዮ አጭር ሞገድ ስርጭት ወደሚገኝባቸው ቦታዎች የሚደርሰውን መልዕክት መቀበል መቻላቸው እጅግ ጠቃሚ እንደሆነ ጠቁመው፥ የመገናኛ ዘዴው በሚስዮናዊ አገልግሎት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ማረጋገጣቸውን መግለጫው አስታውሷል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት በሙሉ ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ከሰጡ በኋላ፥ በዕለቱ በተከበረው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ በዓል ዓይነት በሌሎች በዓላትም በቀጣይነት እና በታማኝነት ሲያገለግሉ የቆዩትን የማዕከሉ ሠራተኞችን   አመስግነዋል።

የቅድስት መንበር መግለጫ በተጨማሪም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1951 ዓ. ም. ከቫቲካን ክልል ውጭ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዞታዎች በማስመልከት ከጣሊያን መንግሥት ጋር የተደረሰውን ስምምነት እና “ፍራቴሎ ሶሌ” የተሰኘውን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የግል ሐዋርያዊ ውሳኔን መሠረት በማድረግ የሬዲዮ ጣቢያውን ብቻ ሳይሆን የቫቲካን ግዛት የኤሌክትሪክ ኃይልን ሙሉ በሙሉ ለማሳደግ የተጀመረውን ውጥን በጥሞና ለመመልከት ዕድል ማግኘታቸውን ገልጿል።

 

 

21 Jun 2025, 16:23