ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከመንፈሳዊ ጥሪ አገልግሎት መሪዎች ጋር እንደሚገናኙ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በዘንድሮው ቅዱስ ዓመት የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና የካኅናት ኢዮቤልዩን ምክንያትበማድረግ፥ የቤተ ክኅነት ጉዳይን የሚከታተል ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፥ “ወዳጆች ብያችኋለሁ” (ዮሐ 15፡15) በሚል ርዕሥ ዓለም አቀፍ ስብሰባ ማዘጋጀቱ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የሚሳተፉበት እና በቫቲካን አካባቢ በሚገኝ የስብሰባ አዳራሽ ሐሙስ ሰኔ 19/2017 ዓ. ም. ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት እስከ ከቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ የሚካሄደው ይህ ስብሰባ፥ በመንፈሳዊ ጥሪ አገልግሎት እና በዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች ዝግጅት ላይ የተሰማሩ መሪዎችን እንደሚያሳትፍ ታውቋል።
ከዮሐ. 15:15 የተወሰደ እና “ወዳጆች ብያችኋለሁ” የሚለው የጥቅሱ ጭብጥ የክኅነት ጥሪ ማዕከላዊነት የሚያጎላ፣ ከመልካሙ እረኛ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ወዳጅነትን እና ለእግዚአብሔር ሕዝብ አስደሳች አገልግሎትን፥ ከምንም በላይ የደስታ ጥሪ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ግብዣ የማወቅ እና የመፈጸም ጥሪ ነው።
ጸሎት፣ መጋራት እና ምስክርነት
ብፁዕ ካርዲናል ላዛሮ ዩ ሄንግ-ሲክ፥ በቅድስት መንበር የቤተ ክኅነት ጉዳይ የሚከታተል ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና መሪ የስባሰባው ተካፋዮችን ከተቀበሉ በኋላ ስብሰባውን በጸሎት እና በንግግር ሲከፍቱት የኢዮቤልዩን የተስፋ ዓመት አስፈላጊነት በማጉላት እንደሚያስተዋውቁት ታውቋል።
በመጀመሪያው የስብሰባ ክፍለ ጊዜ ከዓለም ዙሪያ በተውጣጡ አምስት የመንፈሳዊ ጥሪ አገልግሎት ምሳሌዎች አማካይነት ዓለም አቀፋዊ ዕይታ ያላቸው ፍሬያማ ተሞክሮዎች እንደሚቀርቡ ታውቋል።
አባ ሆሴ አልቤርቶ ኤስትራዳ ግራሲያ፥ በሜክሲኮ ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ውስጥ የጥሪ አገልግሎት ዋና ጸሐፊ የነበሩት፣ የሞንቴሬይ ሀገረ ስብከት የጥሪ ማዕከል ለአካባቢ የዘርዓ ክኅነት ትምህርት አጋዥ ምሳሌሆኖ መገኘቱን በማስመልከት ማብራሪያን ይሰጣሉ።
ጣልያንን በመወከል ብሔራዊ የጥሪ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት አባ ሚካኤል ጃኖላ፥ በሀገሪቱ ውስጥ ስላለው የጥሪ መስክ የተለያዩ ገጽታዎችን በማስመልከት ንግግር ያደርጋሉ።
የአርጀንቲናዋ ተወካይ ዶ/ር ማርያ ሊያ ዜርቪኖ፥ ስለ ክኅነት ጥሪ፣ ስለ ምንኩስና ሕይወት እና የክርስቲያናዊ ጋብቻ ጥሪዎችን የሚያበረታታ ሚስዮናዊ የወጣቶች መንፈሳዊ አገልግሎት ተሞክሮአቸውን ያጋራሉ።
የአየርላንዷ ተወካይ እና የቅዱስ ቤተሰብ ተልዕኮ ዋና ዳይሬክተር እና ተባባሪ መሥራች ዶ/ር ሞራ መርፊ፥ በአየርላንድ ወጣቶች ራሳቸው በሚመሩት ፍሬያማ የጥሪ ተሃድሶ እንቅስቃሴ፥ ከ35 በላይ የዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች መኖራቸውን በማስመልከት ምስክርነትን ይሰጣሉ።
በስፔን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ የዘርዓ ክኅነት ጽሕፈት ቤት ንዑስ ኮሚቴ ዳይሬክተር አባ ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ቫኬር በጥሪ አገልግሎት ዙሪያ የጀመሩትን አዲስ ሀገራዊ ተነሳሽነት በማስመልከት ንግግር እንደሚያደርጉ ታውቋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መልዕክት
“ደስተኛ ካህናት” በሚል ርዕሥ በሚቀርብ ዝግጅት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ አሥራ አራተኛ ለስብሰባው ተካፋዮች መልዕክታቸውን የሚያስተላልፉ ሲሆን፥ ይህም የዛሬውን የክኅነት ጥሪ ትርጉምን፣ ውበቱን፣ ቅድስናውን እና የኅብረት ጥሪን በዕለት ተዕለት የአገልግሎት ሕይወት ውስጥ ለመደማመጥ እና ለማሰላሰል ጊዜን እንደሚሰጥ ታውቋል።
ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ንግግር ቀጥሎ ከስብሰባው ተካፋዮች የሚቀርቡ ጥያቄዎች፣ ምስክርነቶች፣ የጋራ ልምዶችን ጨምሮ የነጻ አስተያየት ጊዜ እንደሚኖር ይጠበቃል።
በስብሰባው ሁለተኛ ክፍል፥ በዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች ዝግጅት ውስጥ በአርአያነት የቀረቡ አምስት ሞዴሎችን የሚመለከት ሲሆን እንደርሱም፥
ከአፍሪካ ከመጡ የስብሰባው ተካፋዮች የሚቀርቡ ምስክርነቶች፣ የክኅነት ጥሪ በብዛት በሚታይበት አካባቢም ቢሆን በማስተዋል እና በጠንካራ ዝግጅት ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን የሚገልጹ፥ በትልልቅ የዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በሚገኙ ትናንሽ ማኅበረሰቦች አወቃቀሮች ውስጥ የእጅ ሥራ እንደ ማጠናከሪያ መሣሪያነት የሚካተት መሆኑን የሚገልጹ ልምዶች ይቀርባሉ።
በፊሊፒንስ-ማሎሎስን የሚገኘው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት ሁለንተናዊ የተሳትፎ እና የተልዕኮ-ተኮር ዝግጅቶች ከቁምስና ምዕመናን ጋር በቅርበት የተሳሰሩ መሆናቸውን የሚያስተዋወቅ ፅንሰ-ሀሳብ ይቀርባል።
ከኮሎምቢያ የመጡት የስብሰባው ተወካዮች፥ በሶኮሮ እና ሳን ጂል ሀገረ ስብከት የሚገኝ የሳን ካርሎ ከፍተኛ ዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት በማዕከላዊ ሕንፃ ዙሪያ በሚገኙ አምስት ትናንሽ መንደሮች ውስጥ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላቸው ሕያው ሆኖ እንደሚገኝ የሚያመላክት መሆኑን የሚያሳዩበት ይሆናል።
በብራዚል የዘርዓ ክኅነት ሚስዮናውያን ምክር ቤቶች ብሔራዊ ቅንጅት፥ የሚስዮናውያን ተሞክሮዎችን፣ የሕንጽት ጊዜያትን እና በየሦስት ዓመቱ የሚካሄደውን ብሔራዊ ጉባኤ የሚያበረታቱ ከ110 በላይ የአካባቢ ቡድኖችን በማካተት ውይይት እንደሚደርግበት ታውቋል።
በመጨረሻም በአሜሪካ ካንሳስ ግዛት ውስጥ የሚገኝ የዊቺታ ሀገረ ስብከት ለዘርዓ ክኅነት ተማሪዎች ዝግጅት ጎልቶ የሚወጣበት ሞዴል ሆኖ እንደሚቀርብ እና ይህም ብዙ ጥሪዎችን በሚስብ ውጤታማ አቀራረብ እውቅና ማግኘቱ ታውቋል።
የቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የዋዜማ ዝግጅት
የስብሰባው ዓላማ ጥሪን የማሳደግ ልምድን መለዋወጥ እና ወጣቶችን ማነሳሳት ብቻ ሳይሆን በካህናት፣ በዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤት መምህራን፣ በገዳማውያን እና ገዳማውያት እንዲሁም በመጀመርያ ዝግጅት እና በጥሪ አገልግሎት ውስጥ በተሳተፉ ምእመናን መካከል ወንድማማችነትን ለማምጣት ጭምር እንደሆነ ታውቋል።
ስብሰባው ከቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት ላይ ከተጠናቀቀ በኋላ ተሳታፊዎች በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በሚቀርበው የዘርዓ ክህነት ተማሪዎች እና የካኅናት ኢዮቤልዩ ዋዜማ ሥነ-ሥርዓትን መቀላቀል እንደሚችሉ ታውቋል።