“በመከራ ወቅት ስለ ተስፋ መናገር”
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በቅድስት አገር ጦርነት፣ መለያየት እና ስቃይ እየሰፋ ባለበት በዚህ ወቅት፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 59ኛውን ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ መገናኛ ቀንን በማስመልከት ከበዓለ ሃምሳ በፊት ባለው እሑድ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ነገር ግን ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁበልባችሁ ቀድሱት። በእናንተም ስላለች ተስፋ ምክንያት ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን በገርነት እና በአክብሮት አድርጉት፤ በክርስቶስ ያላችሁን መልካም ጸባይ በመንቀፍ የሚናገሩ ሰዎች በሐሜታቸው እንዲያፍሩ መልካም ሕሊና ይኑራችሁ” (1ኛ ጴጥ. 3:15-16)። የሚለውን በመጥቀስ ያቀረቡት አስቸኳይ ጥሪ ነው።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቃላት ጥልቅ የእረኝነት እና የትንቢታዊነት መልዕክት፥ በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የሚሠሩት ብቻ ሳይሆን ሁሉም ክርስቲያኖች ማኅበራዊ መገናኛን እንዴት መጠቀም እንደሚገባ ማሰላሰል እንዳለብን ይጋብዛል። ማኅበራዊ መገናኛዎች የሰላም መሣሪያ ወይስ ለግጭት ተጨማሪ እገዛን የሚያደርጉ ናቸው?
በጦርነት መካከል የተስፋ ቃልን መናገርነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጥር 18/2017 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት የዓለም አቀፍ መገናኛ ቀን መልዕክታቸው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተመሠረተ እውነተኛ እና ፍጹም የተስፋ ምስክሮች እንድንሆን በመጋበዝ፥ ስጋትን፣ ጥላቻን እና ተስፋ መቁረጥን በመቀስቀስ ሰብዓዊነትን የሚያጠፋ እና የሚከፋፍል ቃል መቃወም እንደሚገባ አሳስበዋል።
በመልዕክታቸው፥ “ተስፋ ሃላፊነት ሊወሰድ የሚገባው ነው” ያሉት ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ተስፋ የተደበቀ በጎነት፣ ታታሪ እና ታጋሽነት የሚገኝበት እንደሆነ ገልጸው፥ ሆኖም ተስፋ በእውነት፣ በአክብሮት እና በርኅራኄ መነገር የሚገባው መሆኑንም አጥብቀው ተናግረዋል።
ምን ዓይነት የተስፋ ምስክሮች ነን?
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያቀረቡት ጥያቄ፥ የቁጣ ነበልባል በሚቀጣጠልበት ምድር ውስጥ ኃይለኛ ድምፅ ያለው፣ አንድ ቃል ብቻውን የተሰበረ ልብን ሊያጽናና የሚችል በመሆኑ “ምን ዓይነት የሃሳብ ልውውጥ ማድረግ እንችላለን?”
የክርስቲያን መገናኛ ባለሞያዎችን በአሸዋ ውስጥ ያለውን ወርቅ ለማግኘት ከሚጥሩት ጋር ያመሳሰሉት ቅዱስነታቸው፥ “የክርስቲያን መገናኛ ባለሞያዎች አሰቃቂ ታሪኮችን በተሸከመች ምድር ውስጥ ስለ ተስፋ ለመናገር እና እውነታን ለማስዋብ ሳይሆን ነገር ግን በጨለማ ውስጥ ያለውን ውበት ለመግለጥ የተጠሩ ናቸው” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ1ኛ ጴጥ. 3:15-16 ላይ በተጻፈው መልዕክት ላይ በማስተንተን ሦስት አስፈላጊ የክርስቲያናዊ መገናኛ ባህሪያትን አጉልተው ገልጸዋል። ሁሉም የጠፉ በሚመስልበት ጊዜም እንኳ ቢሆን በመንፈስ ቅዱስ ስጦታ አማካይነት መልካምን ለማየት መምረጥ፣ የተስፋችን ምክንያት የሆነውን ራሱን ኢየሱስ ክርስቶስን ለሌሎች ለማስረዳት ዝግጁ መሆን እንዳለብን እና ይህን የምናስረዳው በየዋህነት እና በአክብሮት እንጂ በጠብ ወይም በፍርሃት መሆን እንደሌለበት በማሳሰብ፥ በኤማሁስ መንገድ ላይ ከሙታን የተነሳውን ኢየሱስ ክርስቶስን በማዳመጥ የሚጀምረው እውነተኛ የእርስ በርስ ግንኙነትን አርአያ አድገው አቅርበዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ግራ ተጋብተው በሐዘን ውስጥ ከሚገኙ ደቀ መዛሙርቱ ጋር ተገናኝቶ ተስፋቸውን በእርጋታ ከማደሱ አስቀድሞ በቅድሚያ ሕመማቸውን በትዕግሥት አዳምጧል። እኛም በተመሳሳይ መንገድ ከሌሎች ጋር አብረን ለመጓዝ ተጠርተናል። ይህን አርዓያነት በቃል ሳይሆን እርስ በርስ በአካል በመገኘት እንጀምር። የድፍረትን፣ የምህረት እና የማይበገር እምነት ታሪኮችን ለሌሎች በማካፈል ለዓለም ተስፋን እንመስክር። ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሥቃይን በተሸከመ ዓለም ውስጥ ውበት እና ብርሃን የሚገልጡ ታሪኮችን እና የጋራ ሰብዓዊነታችንን የሚያጎለብቱ ትረካዎችን እንድናቀርብ አሳስበውናል።
ከልብ የሚመነጭ ፈዋሽ የእርስ በርስ ግንኙነት
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ፥ ተስፋን ሰንቀን በፈተና ጊዜ በፍርሃት እና በንዴት ከመረበሽ ይልቅ በምሕረት ላይ የተመሠረተ ተስፋን ለመዝራት አብረን እንድንጓዝ አሳስበዋል።
በተለይም ጦርነት እና መከፋፈል በበዛበት ወቅት እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት ትንቢታዊ ነው። ልብን ይስባል። በመከራ ውስጥም ቢሆን መልካም ነገርን ይገልጣል። ከመለያየት ይልቅ አንድነትን ያጎለብታል። እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት ሰዎችን ወደ ርዕዮተ ዓለማዊነት መቀነስን ይቃወማል። ከሰብዓዊነት ጋር ውበትን እና አብሮነትን ያጎለብታል። በደመ ነፍስ ምላሽ የሚመራ ሳይሆን በፍቅር የሚመራ፣ ቃላትን ወደ የፈውስ መሳሪያነት የሚቀይር ነው።
በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ከተመሠረቱ ልቦች ስለሚመነጩ የእርስ በርስ ግንኙነት ዓይነቶች ተናግረዋል። ይህም ከማግለል ይልቅ የሕብረት ትስስርን ይፈጥራል። ይህ ራዕይ በተለይ የተስፋ ታሪኮች የሕይወት መስመር በሆነባት በቅድስት ምድር አጣዳፊ ነው። እያንዳንዱ ቃል ቁስሎችን እንደገና ሊከፍት ወይም ሊፈውሳቸው ይችላል።
ክርስቲያኖች በመገናኛ ብዙኃን ምሥክሮች መሆን
መላው የቅድስት ሀገር ክርስቲያኖች፥ ቤተ ክኅነት፣ ወጣቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ወላጆች እና ተማሪዎች በሙሉ ድምጻችሁ አስፈላጊ ነው። በእያንዳንዱ የተሰበረ ልብ ውስጥ ፍቅርን ምረጡ። ተስፋ መቁረጥ በሚታይበት ክልል ውስጥ ስለ ተስፋ መናገርን ምረጥ። የቁጣ ስሜት በበዛበት ዓለም ውስጥ የዋሆች ለመሆን አይፍሩ።
በጨለማ ውስጥም ቢሆን ክርስቶስ ከእኛ ጋር እንደሚራመድ እና ቃሎቻችንም የሰላሙ መሣሪያዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ለዓለም በማሳሰብ የተስፋ ተናጋሪዎች እንሁን። ይህንን ተስፋ በታማኝነት፣ በድፍረት እና በርህራሄ፥ ከቅድስት ምድር ልብ ጀምሮ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ እናካፍል።
የቅድስት ሀገር ክርስቲያን በመሆኔ፥ ይህን ጽሑፍ የጻፍኩት፥ “በልባችሁ ውስጥ ያለውን ተስፋ በየዋህነት እርስ በርስ ተከፋፈሉ” (1ኛ ጴጥሮስ 3፡15–16) በሚል ርዕሥ፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለ59ኛው ዓለም አቀፍ የማኅበራዊ መገናኛ ቀን ያስተላለፉትን መልዕክት ለሌሎች እንዳካፍል ከቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ለቀረበልኝ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ነው።