MAP

በቺካጎ በዓሉ የሚከበርበት የዋይት ሶክስ የቤዝ ቦል መጫወቻ ስታዲየም በቺካጎ በዓሉ የሚከበርበት የዋይት ሶክስ የቤዝ ቦል መጫወቻ ስታዲየም  (2025 Getty Images)

የቺካጎ ከተማ የር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ምርጫን ለማክበር ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ተገለጸ

የአዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የትውልድ ሥፍራ የሆነው የቺካጎ ከተማ የቅዱስነታቸውን ምርጫ ምክንያት በማድረግ በዓል እያዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሰሜን አሜሪካ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የትውልድ ከተማ ቺካጎ የቅዱስነታቸውን ምርጫ በጸሎት እና በዝማሬ ለማክበር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።

በቺካጎ ውስጥ ሬት ፊልድ በተባለ አካባቢ የሚከበረው በዓል በእምነት፣ በአንድነት እና በኅብረት መንፈስ እንደሆነ ሀገረ ስብከቱ ገልጿል።

የቺካጎ ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከት በኤክስ ገጹ ላይ ባሠፈረው መልዕክት እንደገለጸው፥ በሕይወት ዘመን አንድ ጊዜ የሚከሰተውን እና ቅዳሜ ሰኔ 7/2017 ዓ. ም. ሊከበር ዝግጅት እየተደረገለት የሚገኘውን የደስታ መግለጫ በዓል ምዕመናን እና የአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲቀላቀሉት ግብዣውን አቅርቧል።

ቺካጎ ውስጥ በዓሉ የሚከበርበት “የሬት ፊልድ” ፓርክ የቺካጎ ዋይት ሶክስ ከፍተኛ የቤዝ ቦል መጫወቻ ስታዲየም የሚገኝበት እንደ ሆነ ታውቋል።

በዓሉን ለማክበር ወደ ሥፍራው ለሚመጡት ታዳሚዎች መግቢያ በር የሚከፈተው ቅዳሜ ሰኔ 7/2017 ዓ. ም. ከቀኑ ስድስት ሰዓት ተኩል ላይ እንደሚሆን የገልጸው የሀገረ ስብከቱ መርሃ ግብር በማከልም፥ በዕለቱ ከሰዓት በኋላ በስምንት ሰዓት ተኩል ላይ የሚጀምረውን መስዋዕተ ቅዳሴ የሚመሩት የከተማው ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፕይች መሆናቸው ታውቋል።

ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች ዝግጅቱን በማስመልከት ባስተላለፉት አጭር የቪዲዮ መልዕክት፥ በዓሉን ሁሉም ሰው እንዲሳተፍ ጋብዘዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች ሥነ-ሥርዓቱን ሁሉም ሰው እንዲካፈል ጋብዘዋል

በቺካጎ በሚዘጋጀው ሥነ-ሥርዓት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ባይገኙም፥ ከሮም በርቀት እንደሚካፈሉት በቪዲዮ መልዕክታቸው ገልጸዋል።

ብፁዕ ካርዲናል ብሌዝ ኩፒች ክስተቱን አስመልክተው የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ እጅግ በርካታ ምዕመናን ምላሻቸውን የሰጡ ሲሆን፥ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች ውስጥ ብቻ ከ9,000 በላይ ትኬቶች መጠየቃቸው ተገልጿል። በመጀመሪያው ቀን ይህ ቁጥር ወደ 20,000 መድረሱ ታውቋል።

በዝግጅቱ ላይ ሁሉም እንዲገኙ በማለት የጋበዘው የሀገረ ስብከቱ የበዓል አዘጋጅ ኮሚቴው፥ ትኬቶች በአምስት ዶላር ($5) እየተሸጡ እንደሚገኙ ገልጾ፥ ለበለጠ መረጃ “archchicago.org/MAPLeoXIV” የተሰኘውን ድረ-ገጽ አንዲጎብኙት አሳስቧል።

 

03 Jun 2025, 16:18