MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “እግዚአብሔር ፍቅሩን ያለ ልክ አብዝቶ ይሰጠናል” ሲሉ አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ተስፋችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” በሚል ርዕሥ የጀመሩትን የኢዩቤልዩ ዓመት ተከታታይ አስተምህሮ በመቀጠል፥ በዘሪው ምሳሌ ላይ የተመሠረተ የመጀመሪያቸውን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ክፍል ረቡዕ ግንቦት 13/2017 ዓ. ም. አቅርበዋል። በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባቀረቡት አስተምህሮ፥ እግዚአብሔር ፍቅሩን ያለ ልክ እጅግ አብዝቶ እንደሚሰጥም አስገንዝበዋል።

በማቴ 13: 1-9 ላይ ስለ ዘሪው ምሳሌ በሚናገረው ክፍል ላይ በማስተንተን ባቀረቡት አስተምህሮ፥ እግዚአብሔር ዘርን እንደሚያበቅል እንደ ለም መሬት መሆን እንዳለብን ባይጠብቀንም ቃሉን ዘወትር በልግስና እንደሚሰጠን እና እርሱን በማመናችንም ‘ዘርን የሚያበቅል አፈር’ የመሆን ፍላጎት በውስጣችን ሊቀጣጠል ይችላል ብለዋል። ክቡራት እና ክቡራን ፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ረቡዕ ግንቦት 13/2017 ዓ. ም. ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው አቀርበንላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! በዚህ የመጀመሪያ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮዬ ታዳሚዎቼን እንኳን ደህና መጣችሁ ለማለት እወዳለሁ። በነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አነሳሽነት፥ ‘ተስፋችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው!’ በሚል መሪ ርዕሥ የሚቀርብ የኢዮቤልዩ ዓመት ተከታታይ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮን እቀጥላለሁ።

እግዚአብሔር በታሪክ መካከል እንዴት እንደሚሠራ የሚያሳይ ስለሆነ ተስፋን ለማግኘት በሚረዱን በኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌዎች ላይ ማሰላሰላችንን እንቀጥላለን። ዛሬ በመጠኑም ቢሆን ለየት ባለ ምሳሌ ላይ ላተኩር እወዳለሁ። ምክንያቱም ይህ ምሳሌ የሌሎች ሁሉ ምሳሌዎች መግቢያ ነው። በማቴ. 13፡1-17 ላይ የተጻፈውን የዘሪውን ምሳሌ እጠቅሳለሁ። ይህም በዛሬው ዘመን ወንጌልን ስለ መስበክ ብዙ የሚያስተምረን በመሆኑ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሃሳቡን ለማጋራት የተጠቀመበትን መንገድ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መገንዘብ እንችላለን።

እያንዳንዱ ምሳሌ ከዕለት ተዕለት የሕይወት ልምድ ጋር የተገኘውን ታሪክ ይነግራል። ታሪኩን የበለጠ በመንገር ወደ ጥልቅ ትርጉም ይመራናል። ምሳሌው በውስጣችን ጥያቄዎች እንዲነሱ ያደርጋል። በዕይታ ላይ ብቻ እንዳንቆም ይጋብዘናል። ‘ከተነገረኝ ታሪክ ወይም ከቀረበልኝ ምሳሌ አስቀድሞ በዚህ ታሪክ ውስጥ የት ነው የምገኘው?’ ብዬ ራሴን መጠየቅ እችላለሁ። ይህ ምሳሌ ለሕይወቴ ምን ያስተምራል? እንደ እውነቱ ከሆነ ‘ምሳሌ’ የሚለው ቃል የመጣው፥ ‘ፓራባሌይን’ ከሚለው ከግሪክ ግስ ሲሆን፥ ትርጉሙም ፊት ለፊት ማውጣት ማለት ነው። ምሳሌው የሚያነሳሳኝን እና ራሴን እንድጠይቅ የሚገፋፋኝን ቃል ከፊት ለፊቴ ያስቀምጣል።

የዘሪው ምሳሌ ስለ እግዚአብሔር ቃል እና ስለሚያስገኘው ውጤት በትክክል ይናገራል። በእርግጥም እያንዳንዱ የወንጌል ቃል በሕይወታችን ውስጥ በእርሻ ላይ እንደተጣለ ዘር ነው። ኢየሱስ የዘሩን ምሳሌ ብዙ ጊዜ ተጠቅሟል። የተለያየ ትርጉም አለው። በማቴ. ምዕ. 13 ላይ የተነገረው የዘሪው ምሳሌ ሌሎች ተከታታይ አጫጭር ምሳሌዎችን ያያዘ ሲሆን፥ አንዳንዶቹም በምድሪቱ ላይ ስለሚሆነው ነገር በትክክል ይናገራሉ። ስለ ስንዴው እና ስለ እንክርዳዱ፣ ስለ ሰናፍጭ ዘር፣ በእርሻ ውስጥ ስለተደበቀ ውድ ሃብት ይናገራል። ታዲያ ይህ አፈር ምንድን ነው? የእኛ ልብ ነው። ነገር ግን ደግሞ የምንኖርበት ዓለም፣ ማኅበረሰብ እና ቤተ ክርስቲያንም ጭምር ነው። በእውነት የእግዚአብሔር ቃል ፍሬያማ ያደርገናል፤ ስለ እያንዳንዱ እውነታ ይገልጻል።

በመጀመሪያ ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤቱ ወጥቶ ብዙ ሰዎችን በዙሪያው ሲሰበስብ እናየዋለን (ማቴ. 13፡1)። ቃሉ የሚማርክ እና ቀልብ የሚስብ ነው። በሰዎች መካከል ብዙ የተለያዩ ሁኔታዎች እንዳሉ ግልጽ ነው። ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል ወይም ትምህርት ለሁሉም ነው። በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ በተለያየ መንገድ ይሠራል። ይህ አውድ የምሳሌውን ትርጉም በደንብ እንድንረዳ ያስችለናል።

አንድ ያልተለመደ ዘሪ ለመዝራት ወጣ። ዘሩ የት እንደሚወድቅ ግድ የለውም። ፍሬ ማፍራት በማይቻልበት ቦታ ዘሩን ይጥላል። በመንገድ ላይ፣ በድንጋያማ ቦታ እና በእሾህ መካከል ሁሉ ዘሩን ይበትናል። ይህ አስተሳሰብ አድማጭን በማስገረም፥ ‘ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?’ ብሎ ራሱን እንዲጠይቅ ይገፋፋል።

ነገሮችን ማስላት ለምደናል። በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ ቢሆንም ነገር ግን ስለ ፍቅር ሲወራ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። ይህ አባካኙ ዘሪ ዘሩን የሚጥልበት መንገድ እግዚአብሔር እኛን የሚወድበት መንገድ ምሳሌ ነው። በእርግጥ የዘሩ ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው መሬቱ ወይም እርሻው በሚቀበልበት መንገድ እና ዘሩ በሚኝበት ሁኔታ ላይ ቢሆንም፥ ከሁሉ አስቀድሞ በዚህ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ የቃሉን ዘር በሁሉም የአፈር ዓይነት ላይ እንደሚጥል ይነግረናል። ያም እኛ በምንገኝበት ሁኔታ ውስጥ፣ አንዳንድ ጊዜ ትኩረታችን የበለጠ በተከፋፈለበት፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሕይወታችን ልንሸከመው በማንችልበት ጊዜ ሲሆን፥ ሌላ ጊዜ ግን ፈቃደኞች የምንሆንበት እና የምንቀበልበት ጊዜም አለ። እግዚአብሔር ይተማመናል፤ ይዋል ይደር አንድ ቀን ዘሩ እንደሚያብብ ተስፋን ያደርጋል። የሚወደንም እንደዚህ ነው። ለም መሬት እንድንሆን ባይጠብቀንም ነገር ግን ሁልጊዜ በልግስና ቃሉን ይሰጠናል። ምናልባትም እርሱ እንደሚያምነን በማየታችን የተሻለ አፈር የመሆን ፍላጎት በውስጣችን ይቀጣጠል ይሆናል። ይህ በእግዚአብሔር የልግስና እና የምሕረት ዓለት ላይ የተመሠረተ ተስፋ ነው።

ኢየሱስ ዘሩ ፍሬ የሚያፈራበትን መንገድ ሲናገር፥ ስለ ሕይወቱም ጭምር እየተናገረ ነው። ኢየሱስ ቃልም ነው፣ ዘርም ነው። ዘር ፍሬን እንዲያፈራ ከተፈለገ መሞት አለበት። ስለዚህ ይህ ምሳሌ እግዚአብሔር ለእኛ ሲል ሊሞት ዝግጁ እንደሆነ እና ኢየሱስ ክርስቶስም ሕይወታችንን ለመለወጥ ሲል መሞቱን ይነግረናል።

የታዋቂው ሰዓሊ የቫን ጎግ፥ ‘ፀሐይ ስትጠልቅ የሚዘራ ገበሬ’ በሚል ርዕሥ የተሳለ ውብ ሥዕል በአዕምሮዬ ውስጥ ይገኛል። ያ በጠራራ ፀሐይ ውስጥ የሚዘራው ዘሪ ሥዕል የገበሬውን ድካም ይነግረኛል። ቫን ጎግ ከዘሪው ጀርባ ለአጨዳ የደረሰ እህል ማሳየቱ ይገርመኛል። ይህ ለእኔ የተስፋ ሥዕል ይመስለኛል። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ዘሩ ፍሬ አፍርቷል። ይህ እንዴት ሊሆን እንደቻለ እርግጠኞች ባንሆንም ነገር ግን ሆኗል። በዚህ ሥዕል ላይ ጎልቶ የሚታየው ዘሪው ሳይሆን ሥዕሉ በሙሉ በፀሐይ አምሳል መሳሉ ነው። ምናልባት አንዳንድ ጊዜ የጠፋ ወይም የራቀ ቢመስለንም ነገር ግን ታሪክን የሚያንቀሳቅሰው እግዚአብሔር መሆኑን ለማስታወስ ነው። የምድርን ደመና የሚያሞቅ እና ዘሩ እንዲደርስ የሚያደርግ የፀሐይ ብርሃን ነው።

ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፥ ዛሬ በምን ዓይነት የሕይወት ሁኔታ ውስጥ ሆነን የእግዚአብሔርን ቃል እንሰማለን? በዘር ምሳሌ የቀረበውን ቃሉን የምንቀበልበትን ጸጋ እንዲሰጠን ዘወትር እግዚአብሔርን እንለምነው። ፍሬ የሚሰጥ መሬት አለመሆናችንን ከተገነዘብን ተስፋ መቁረጥ የለበንም። ነገር ግን እህል የሚያበቅል የተሻለ መሬት እንዲያደርገ እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቀው።”

 

21 May 2025, 16:57