ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ በመነጋገር እና በመወያየት ጦርነትን ማስቀረት እንደሚቻል አስገነዘቡ
ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ለተሰበሰቡት የምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት እንግዶች ያደረጉትን ንግግር ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ብጹዓን ካርዲናሎች፣ ብጹዓን ጳጳሳት ክቡራን ካህናት፣ ገዳማውያን እና ገዳማውያት፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ሆይ! ክርስቶስ ከሞት በእውነት ተነስቷል! በብዙ አገራት የሚኖሩ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናን የእምነታችን እና የተስፋችን ልብ የሆነውን ይህን ዐረፍተ ነገር በብርሃነ ትንሳኤው ሰሞን ለመድገም አይሰለቹም። እኔም እነዚህን ቃላት በመድገም ሰላምታዬን አቀርባለሁ። በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሳኤ ላይ የማይናወጥ ተስፋ በሆነው በተስፋ ኢዮቤልዩ ወቅት እናንተን እዚህ ማየቴ እኔን ያነቃቀኛል። ወደ ሮም እንኳን በደህና መጣችሁ! ዛሬ ከእናንተ ጋር መሆኔ እና የርዕሠ ሊቃነ ጵጵስናዬ የመጀመሪያ የሆነውን ሳምንታዊ የረቡዕ ዕለት ጠቅላላ አስተምህሮዬን ለምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን በማቅረቤ ደስተኛ ነኝ።
በእግዚአብሔር ፊት ውድ ናችሁ። እናንተን ስመለከት የመጣችሁበትን፣ የከበረ ታሪካችሁን እና በርካታ ማኅበረሰቦቻችሁ ያሳለፉትን ወይም እየታገሡት ያለውን ከባድ መከራ አስባለሁ። ‘የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጥብቀው ለሚያቆዩት ልዩ መንፈሳዊ ትውፊቶች እና ክርስቲያናዊ ሕይወት፣ ሲኖዶሳዊነት እና ሥርዓተ አምልኮ የሚነግሩን ሁሉ ሊከበሩ ይገባል’ በማለት የተናገሩትን የነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እምነት በድጋሚ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። (ለምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የዕርዳታ ድርጅቶች [ROACO] የደረጉት ንግግር፤ ሰኔ 27/2024)።
የእናንተ አብያተ ክርስቲያናት ያላቸውን ክብር በማስመልከት የመጀመሪያ ሠነድ ያዘጋጁት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 13ኛ በተመስጦ ቃላት የተናገሩትን መጥቀስ እፈልጋለሁ። ከሁሉ በላይ እንዲህ ብለው ነበር። ‘የሰው ልጆች የማዳን ሥራ የተጀመረው በምሥራቅ ነው’ (ሐዋርያዊ መልዕክት ‘Orientalium Dignitas’ ኅዳር 30/1894 እአአ)። በእውነት እናንተ ‘ቤተ ክርስቲያን የተወለደችበት ቀዳሚ፣ ልዩ እና ተገቢ መብት ያለው ሚና አላችሁ’ (ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፥ ‘Orientale Lumen’ ቁ. 5)። በተለያዩ ባህሎቻችሁ መሠረት አሁን በሮም የምታከብሩት በርካታ ሥርዓተ አምልኮአችሁ እና የኢየሱስ ክርስቶስን ቋንቋ መጠቀማችሁ ጠቃሚ ነው። ‘ሕጋዊው ዓይነት የምሥራቃዊ ሥርዓተ አምልኮ እና ተግሣጽ... ለቤተ ክርስቲያን ታላቅ ክብር እና ጥቅም እንደገና ሊጨምር ይችላል’ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ ሦስተኛ ልባዊ ጥሪ አቅርበው ነበር (Orientaium Dignitas)። ፍላጎታቸውም ዘወትር ወቅታዊ ሆኖ ይቆያል። በእኛ ዘመንም ብዙ የምሥራቅ አገራት ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን፣ አንዳንዶቻችሁን ጨምሮ በጦርነት እና በስደት፣ በመረጋጋት እና በድህነት የተነሳ ከትውልድ አገራቸው እንዲሰደዱ ተደርገዋል። ወደ ምዕራቡ ዓለም ሲደርሱ ትውልድ አገራቸውን ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ ማንነታቸውን ሊያጡ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ትውልድ ሲያልፍ በዋጋ የማይተመን የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ቅርስም ይጠፋል።
ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 13ኛ፥ ‘የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የአምልኮ ሥርዓቶችን መጠበቅ ከማወቅ በላይ አስፈላጊ ነው’ በማለት ተናግረዋል። ‘ማንኛውም የላቲን ሥርዓትን የሚከተሉ ሚስዮናውያን፣ ዓለማዊም ሆኑ መደበኛ ቀሳውስት፣ በምክር ወይም በድጋፍ ማንኛውንም የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን ካቶሊክ ምዕመንን ወደ ላቲን ሥርዓት የሚስብ ከሆነ ከአገልግሎቱ መሰናበት እና መወገድ አለበት’ እስከ ማለት ደርሰው ነበር።
የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመናንን በተለይም ዳያስፖራን መንከባከብ እና ማስተዋወቅ እንደሚገባ ይህን ጥሪ በድጋሚ እናቀርባለን። በተጨማሪም ለምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የተመቻቸ ሁኔታ ለመፍጠር እና ለማቋቋም እንዲቻል በላቲን ሥርዓት ተከታይ ክርስቲያኖች ዘንድ የበለጠ ግንዛቤን መፍጠር ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ የላቲን ሥርዓት ጳጳሳት በዳያስፖራ የሚገኙ የምሥራቅ ካቶሊካዊ ምዕመናን የኑሮ ወጋቸውን ለመጠበቅ በሚያደርጉት ጥረት እና በዚህም ልዩ ምስክርነት የሚሰጡ ማኅበረሰቦችን ለማበልጸግ የሚረዱ መርሆዎችን፣ ደንቦችን እና መመሪያዎችን ለማዘጋጀት እንዲረዱኝ እየጠይቅሁ በቅድስት መንበር የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤትን ለሥራው አመሰግናለሁ።
ቤተ ክርስቲያን እናንተን ትፈልጋችኋለች። ዛሬ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን የምታበረክትልን አስተዋጾ እጅግ ብዙ ነው! በሥርዓተ አምልኮአችሁ ውስጥ ሕያው ሆኖ የሚቀረውን ቅዱሳት ምሥጢራትን፣ ሰውን በሙላት የሚያሳትፍ፣ የመዳንን ውበት የሚዘምር እና የእግዚአብሔር ታላቅነት የሰው ልጅ ድክመቶችን እንደሚያቅፍ የሚገልጽ አስደናቂ የአምልኮ ሥርዓቶችን መልሰን ማግኘት እጅግ ያስፈልገናል! በተመሳሳይ መልኩ በተለይ በምዕራብ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የእግዚአብሔርን ቀዳሚነት፣ የመለኮታዊ ምሥጢር አስፈላጊነት እና የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊነት ዓይነተኛ እሴቶች፣ የማያቋርጥ ምልጃ፣ ንስሐ፣ ጾም እና ለራስ እና ለሰው ልጆች ኃጢአት መለመንን እንደገና መፈለግ አስፈላጊ ነው! እንግዲህ ባህሎቻችሁን ሳትቀንሱ ጠብቃችሁ፣ ምናልባት ለተግባራዊነት ወይም ለምቾት ስትሉ እና በጥቅም ወዳድነት አስተሳሰብ እንዳይበረዙ መከላከል በጣም አስፈላጊ ነው።
የመንፈሳዊነት ወጎቻችሁ ጥንታዊ ቢሆንም ነገር ግን ለሰው ልጅ ዘወትር አዲስ እና መድኃኒት ናቸው። በእነርሱ ውስጥ የሰዉ ልጅ ሰቆቃ አስደናቂ ከሆነው ከእግዚአብሔር ምህረት ጋር ሆኖ ኃጢአታችን ወደ ተስፋ መቁረጥ እንዳይመራን ነገር ግን የተፈወሱትን እና ወደ ሰማይ ከፍ ያሉ ፍጡራን የመሆን የጸጋ ስጦታን እንድንቀበል ያደርገናል። ለዚህም ማለቂያ የሌለውን ውዳሴ እና ምስጋና ለእግዚአብሔር ልንሰጠው ይገባናል። ከሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም ጋር በአንድነት በመጸለይ ጌታን ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲህ እንላለን፡- ‘መስቀልህን የሞት መሻገሪያ ድልድይ ያደረግህ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን! የሟች ሰው ሥጋ ለብሰህ ለሰዎች ሁሉ የሕይወት ምንጭ የሆንክ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ክብር ለአንተ ይሁን!’ (Homily on our Lord, 9)። እንግዲህ ጸጋው በእያንዳንዱ የሕይወት ፈተና ውስጥ የትንሳኤውን እርግጠኝነት ማየት እንድንችል እና ልባችንን እንዳያጠፋው በጸሎት ልንጠይቅ ይገባናል። ሌላው ታላቅ የምሥራቅ ቤተ ክርስቲያን አባት ቅዱስ ይስሐቅ ዘ ነነዌ እንደጻፈው፥ ‘ታላቁ ኃጢአት በትንሳኤው ኃይል አለማመን ነው’ (የቅዱስ ይስሐቅ ዘ ነነዌ ስብከቶች I: 5)።
በግፍ እና በመከራ ውስጥ ሆኖ የተስፋ መዝሙር የሚዘምር ሌላ ማነው? የጦርነትን አስከፊነት በቅርብ የተመለከተ ሌላ ማን ነው? ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እናንተን፥ ‘ሰማዕታት አብያተ ክርስቲያናት’ (አድራሻ የROACO፣ ibid.) በማለት ይጠሯችሁ ነበር።
ከቅድስት ሀገር እስከ ዩክሬን፣ ከሊባኖስ እስከ ሶርያ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ እስከ ትግራይ ድረስ ምን ያህል ግፍ መፈጸሙን እናያለን! በወታደራዊ ወረራ ሕይወት እየተሰዋ ባለበት ወቅት፣ በዚህ ሽብር የተነሳ የብዙ ወጣቶች ሕይወት እየጠፋ ባለበት ወቅት ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን!’ በማለት ደጋግሞ የሚናገረው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሳይሆኑ ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ነው (ዮሐ. 20:19፣ 21፣ 26) ‘ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው ዓይነት አይደለም’ (ዮሐ 14፡27)። በማለት አክሎ ተናግሯል። የኢየሱስ ክርስቶስ ሰላም ከጦርነት በኋላ የሚመጣ የመቃብር ውስጥ ዝምታ አይደለም። የጭቆና ሳይሆን ለሰው ልጅ በሙሉ የተዘጋጀ አዲስ ሕይወት የሚያመጣ ስጦታ ነው። ክፋትን ወደ መልካም ለውጦ በእርቅ፣ በይቅርታ እና በድፍረት አዲስ ሕይወት እንደገና እንድንጀምር ለሚያስችል ሰላም እንጸልይ።
ይህ ሰላም እንዲሰፍን እኔ በበኩሌ ሁሉንም ጥረት አደርጋለሁ። ቅድስት መንበር የተጣሉት እንዲታረቁ፣ ፊት ለፊት እንዲገናኙ እና እርስ በርስ እንዲነጋገሩ ለመርዳት ዘወትር ዝግጁ ነች። ይህም በየትኛውም ቦታ የሚገኙ ሕዝቦች ተስፋቸውን እንደገና እንዲያገኙ እና የሚገባቸውን ክብር መልሰው እንዲያገኙ እና የሰላምን ክብር እንዲያገግሙ ነው። የዓለማችን ሕዝቦች ሰላምን ይፈልጋሉ። መሪዎቻቸውን በሙሉ ልቤ እለምናለሁ። እንገናኝ፣ እንነጋገር፣ እንወያይ! ጦርነትን ማስቀረት ይቻላል። የጦር መሣሪያዎች ችግርን የሚፈቱ ሳይሆን የሚጨምሩ ናቸው። ታሪክ የሚሠሩት ሰላም ፈጣሪ እንጂ መከራን የሚዘሩ አይደሉም። ጎረቤቶቻችን አስቀድሞ ጠላቶቻችን ሳይሆኑ ነገር ግን እንደ እኛ ሰዎች ናቸው። የምንጠላቸው ወንጀለኞች ሳይሆን ነገር ግን አብረን መነጋገር የምንችላቸው ስዎች ናቸው። ዓለምን በጥሩዎቹ እና በክፉዎች የሚከፋፍል የአመጽ አስተሳሰቦችን መቀበል የለብንም።
የጦር መሣሪያዎች ጸጥ ይበሉ ማለትን ቤተ ክርስቲያን አታቋርጥም። በጸጥታ፣ በጸሎት እና በመሥዋዕትነት የሰላም ዘርን ስለሚዘሩ በሙሉ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ለእነዚያ ለምሥራቅ እና ለላቲን ሥርዓት ክርስቲያኖች፥ ከሁሉም በላይ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ የሚገኙት ትውልድ አገራቸውን እንዲተው የሚያደርጋቸውን ፈተና በመቃወም በጽናት መኖር በመቻላቸው እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ። ክርስቲያኖች በቃል ብቻ ሳይሆን ሕልውናቸው አስተማማኝ በሆነበት እና የሚያስፈልጉትን መብቶች ይዘው በአገራቸው መቆየት የሚችሉበት ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ እንትጋ!
የፍትህ ብርሃን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የወጣባቸው መሬቶች ውድ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ወንድሞች እና እህቶች፥ ‘የዓለም ብርሃን’ ስለሆናችሁ እናመሰግናለን (ማቴ. 5፡14)። በሌላ በምንም ሳይሆን በእምነታችሁ፣ በተስፋችሁ እና በበጎ አድራጎታችሁ ጠንካሮች መሆናችሁን ቀጥሉ። አብያተ ክርስቲያኖቻችሁ ለሌሎች አርአያ ይሁኑ። ሐዋርያዊ አባቶቻችሁ በተለይም በጳጳሳት ሲኖዶስ ውስጥ የወንድማማችነት እና ትክክለኛ የጋራ ኃላፊነት ይኖር ዘንድ አንድነትን በቅንነት ያሳድጉ። በንብረት አስተዳደር ውስጥ ያለውን ግልጽነትን በማረጋገጥ፣ ዓለማዊ ሥልጣንን እና ክብርን ሳይፈልጉ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ቅዱስ ሕዝብ ራስን በትህትና በመስጠት ምልክቶች ይሁኑ። አዲሱ የነገረ መለኮት ምሁር ቅዱስ ሲምዖን፥ ‘በሚነድድ የእቶን ነበልባል ላይ አቧራ የሚወረውር ሰው እንደሚያጠፋው ሁሉ፣ ከዚህ ሕይወት እንክብካቤ እና ከማንኛውም ዓይነት ትንሽ እና ከንቱ ከሆኑ ነገሮች ጋር ግንኙነት ያለው አስቀድሞ የተቀጣጠለውን የልብ ሙቀት ያጠፋል’ በማለት ተናግሯል(ተግባራዊ እና የሥነ-መለኮት ምዕራፎች ቁ. 63)። ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ የምሥራቅ ክርስትና ብርሃን ከሁሉም ዓለማዊ ቁርኝት እና ከልዩነት ዝንባሌዎች በሙሉ ነፃ ሆኖ በታዛዥነት እና በወንጌል ምስክርነት ታማኝ ሆኖ መቀጠልን ይፈልጋል።
ለዚህም ምስጋናዬን በማቅረብ እና ቡራኬዬን በመስጠት፣ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሐዋርያዊ አገልግሎቴ በኃይል የተሞላ የምልጃ ጸሎታችሁን እንድታቀርቡ እጠይቃለሁ። አመሰግናለሁ!"