ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ "ድነት የሚገኘው እግዚአብሔር በሚሰጠን የጸጋ፣ የእምነት እና የጽድቅ ስጦታዎች ነው" ሲሉ አስገነዘቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ማክሰኞ ግንቦት 12/2017 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በሮም ውስጥ የሚገኘውን የቅዱስ ጳውሎስ ባዚሊካ የጎበኙ ሲሆን፥ ባዚሊካው በተለምዶ የሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አጽም የሚገኝበት እንደሆነ ይታመናል።
ቅዱስነታቸው በባዚሊካው ውስጥ ጸሎት ካደረሱ በኋላ አጭር የጸሎት ሥነ-ሥርዓት በመሩበት ወቅት፥ ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በላከው መልዕክቱ በምዕ. 1:5 ላይ በማሰላሰል ባሰሙት ስብከት፥ “ጸጋ፣ እምነት እና ጽድቅ የተጠሩበት የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ አገልግሎት ጎልቶ እንዲታይ የሚረዱ ሦስት አበይት መሪ ሃሳቦችን የያዙ ናቸው” ሲሉ አስረድተዋል።
የጸጋ ስጦታ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከእነዚህ ሦስት መሪ ሃሳቦች መካከል የመጀመሪያው በሆነው “ጸጋ” ላይ በማስተንተን እግዚአብሔር በጸጋው ስለምሰጠን ዕርዳታ አብራርተዋል። ቅዱስነታቸው በዚህም ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ሰዎች በጻፈው መልዕክት ላይ እንደገለጸው፥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የተገናኘው መጀመሪያ ኢየሱስ ወደ እርሱ ስለደረሰ ብቻ እንደሆነ መናገሩን አስታውሰው፥ “ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከተገናኘ በኋላ ያከናወነው አገልግሎት፥ ከወንጌል ርቆ ሳለ ወደ አዲስ ሕይወት የጠራው የእግዚአብሔር ፍቅር ውጤት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
“ቅዱስ አጎስጢኖስም ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “መጀመሪያ ካልተመረጥን በቀር እንዴት መምረጥ እንችላለን? አንድ ሰው አስቀድሞ ካልወደደን በቀር መውደድ አንችልም” ማለቱን አስታውሰዋል።
“ያለ እግዚአብሔር ዕርዳታ መልካም ሕይወት መምራት አንችልም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ይህ እውነታ የእያንዳንዱ ጥሪ መሠረት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
የእምነት ስጦታ
ቀጥለውም በቅዱስ ጳውሎስ የጥሪ ምላሽ ውስጥ የእምነትን ሚና የተመለከቱት ቅዱስነታቸው፥ “ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ እግዚአብሔር ለጳውሎስ በተገለጠለት ጊዜ ነጻነቱን አልነጠቀውም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ይልቁንም ውሳኔውን እንዲያሳውቅ ዕድል መስጠቱን ተናግረዋል።
“ድነት የሚገኘው እንዲሁ ሳይሆን ነገር ግን በምስጢራዊ የጸጋ እና የእምነት መስተጋብር፣ በእግዚአብሔር ፍቅር፣ በእምነት እና በነጻ ምርጫ ነው” ሲሉ አብራርተዋል።
የጽደቅ ስጦታ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የሐዋርያው ጳውሎስ ጥሪ የመጨረሻ ገጽታ በሆነው ጽድቅ ወይም በቅድስና የማደግ ሂደት ላይ በማስተንተን ባሰሙት ስብከት፥ “የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ፥ ጳውሎስ ኢየሱስን በራዕይ ካየው በኋላ ክርስቲያኖችን ማሳደዱን እንዳቆመ እና ከእነሱ ጋር አብሮ መሥራት እንዴት እንደጀመረ ይገልጻል” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለተገኙት ባሰሙት ማሳሰቢያ፥ ይህን ዓይነት ፍቅር በማሳየት እንዲወዳደሩ አሳስበው፥ ቅዱስ ጳውሎስ ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለው ፍቅር ራሱን ለሌሎች አሳልፎ እንዲሰጥ እና በመጨረሻም በሰማዕትነት እንዲሞት እንዳደረገው እና ፍቅር የሁሉም ተልዕኮ መሠረት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ በተናገሩት ሐሳብ ላይ በመመርኮዝ ስብከታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ “በሕይወታችን ውስጥ ታላቁ እውነት እግዚአብሔር እንደሚወደን ማወቅ እና ሌላው ሁሉ ትርጉም የሚያገኘው በዚህ ነው” በማለት ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው በማያያዝም፥ “የእኔ ተልዕኮ፥ የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪነት እና የቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያዊ ቅንዓት ወራሽነትን ጨምሮ የእያንዳንዱ ተልዕኮ መሠረት ነው” ብለው፥ ጌታ እግዚአብሔር ለጥሪው በታማኝነት ምላሽ እንድሰጥ ጸጋውን ይስጠኝ” ሲሉ ስብከታቸውን ደምድመዋል።