ቫቲካን የር. ሊ. ጳ. ሌዮ 14ኛ የግንቦት ወር መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶች መርሃ-ግብር ይፋ አደረገ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቫቲካን ዛሬ ባወጣው መግለጫ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በግንቦት ወር ሊፈጽሙ ያቀዷቸው መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶች፥ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪነት መጀመሪያን በማስመልከት ግንቦት 10/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የሚያሳርጉትን የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ያካትታል።
ቅዱስ አባታችን ለእመቤታችን ማርያም በተሰጣት የግንቦት ወር ውስጥ በሮም የሚገኙ ልዩ ልዩ ጳጳሳዊ ባዚሊካዎች ውስጥ የሚቀርቡ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶችን የሚመሩ መሆኑን መግለጫው አስታውቋል።
በመርሃ-ግብሩ እንደተገለጸው፥ የመጀመሪያ ቀጠሮአቸው የሚሆነው በብርሃነ ትንሳኤው አምስተኛ እሑድ ማለትም ግንቦት 10/2017 ዓ. ም. ከጠዋቱ በአራት ሰዓት ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የሚያሳርጉት የሐዋርያዊ መሪነት አገልግሎት መጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴ እንደሚሆን ታውቋል።
ማክሰኞ ግንቦት 12/2017 ዓ. ም. ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ጳጳሳዊ ባዚሊካ ንግደት በማድረግ የሐዋርያውን መካነ መቃብር እንደሚጎበኙ ይጠበቃል።
የብርሃነ ትንሳኤው ስድስተኛ እሑድ በሆነው ግንቦት 17/2017 ዓ. ም. አሥራ አንድ ሰዓት ላይ በቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ ውስጥ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ እንደሚመሩ እና ይህ መስዋዕተ ቅዳሴ የሮም ሀገረ ስብከት ጳጳስ በመሆን የባዚሊካውን ሐዋርያዊ ሃላፊነት በይፋ የሚረከቡበት ይሆናል።
ቅዱስ አባታችን በዚሁ ዕለት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁን ባዚሊካ ጎብኝተው በውስጡ በሚገኝ የሮም ከተማ ነዋሪዎች ጠባቂ በሆነች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መንፈሳዊ ምስል ፊት ጸሎት ያቀርባሉ።
ይህም ከሮም ከተማ በስተደቡብ በሚገኘው እና በቅዱስ አጎስጢኖስ ገዳማውያን ወደሚተዳደር የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ ከሚያደርጉት ጋር ሁለተኛው ማርያማዊ ጉብኝት እንደሚሆን ይጠበቃል።
በመጨረሻም ቅዳሜ ግንቦት 23/2017 ዓ. ም. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ኤልሳቤጥን የጎበኘችበት መታሰቢያ በዓል ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ከጠዋቱ በአራት ሰዓት ላይ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴን በመምራት ለእጩዎች የክኅነት ማዕረግ እንደሚሰጧቸው ይጠበቃል።