MAP

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከብጹእ ካርዲናል ፕሬቮስት ሮበርት ፍራንሲስ (አሁን ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከሆኑት) ጋር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ከብጹእ ካርዲናል ፕሬቮስት ሮበርት ፍራንሲስ (አሁን ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከሆኑት) ጋር   (Vatican Media)

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ፡ ‘ሰላም ከሁላችሁ ጋር ይሁን’

አዲስ የተመረጡት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የምርጫውን ውጤት በጉጉት ሲጠባበቅ ለነበረው ህዝብ እና ለዓለም በሙሉ ሰላምታ ካቀረቡ በኋላ፥ ሰላምን ለማበረታታት፣ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና ለወንጌል ታማኝ ለሆነችው አንዲት ቤተክርስቲያን ለመስራት ቃል ገብተዋል።

  አቅራቢ ዘላለም ኃይሉ ፥ አዲስ አበባ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የጴጥሮስ ተተኪ ሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ በታዩበት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ማዕከላዊ ሰገነት በኩል ብቅ ብለው በአደባባዩ ተሰብስቦ ሲጠብቃቸው ለነበረው በርካታ ህዝብ ክርስቲያን፣ የሮም ከተማ ህዝብ እና ለዓለም በሙሉ “ሰላም ለሁላችሁ ይሁን!” በማለት ሰላምታቸውን አቅርበዋል። ያደረጉት ንግግርም እንደሚቀጥለው ይቀርባል፦

የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰላምታ ለሮም እና ለዓለም በሙሉ
‘ሰላም ለእናንተ ይሁን!’ የተከበራችሁ ወንድሞች እና እህቶች፣ ይህ ለእግዚአብሔር ልጆች ነፍሱን የሰጠ መልካም እረኛ እና ከሙታን የተነሳው የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመጀመሪያ ሰላምታ ነበር። እኔ ደግሞ ይህ ሰላምታ ወደ ልባችሁ እንዲገባ፣ ለቤተሰቦቻችሁ እና ለሁሉም ሰዎች ባሉበት እንዲደርስ እመኛለሁ።

አሕዛብም ሁሉ ምድርም ሁሉ፥ ሰላም ለእናንተ ይሁን።

ይህ ትጥቅ የሚያስፈታ እና ትሁት፣ እንዲሁም ሰላምን የሚጠብቅ የክርስቶስ ሰላም ነው። ይህ ያለ ገደብ እና ቅድመ ሁኔታ ሁላችንንም እኩል ከሚወደን ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ የመጣ ሰላምታ ነው። ሮምን በመጨረሻዎቹ የህይወት ጊዜያቸው በደከመ፥ ነገር ግን ሁልጊዜም ደፋር እና ብርቱ በሆነው ድምፃቸው የባረኩትን፣ በዚያ በትንሳኤው በዓል ቀን ማለዳ ላይ ሮምን እና ዓለምን የባረኩትን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ ድምፅ ሁሌም በጆሮአችን እናስታውሰው።

እኔም ያንኑ በረከት እንድቀጥል ፍቀዱልኝ። እግዚአብሔር ይወደናል፣ ሁላችንንም ክፉ ነገር አያሸንፈንም። ሁላችንም በእግዚአብሔር እጅ ላይ ነን። ያለ ፍርሃት፣ በአንድነት፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን ከእግዚአብሔር ጋር ሆነን እና እርስ በርስ ተደጋግፈን ወደፊት እንጓዛለን። እኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ነን፣ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፊታችን ይራመዳል፥ ዓለም የእርሱን ብርሃን ይፈልጋል። የሰው ልጅ ወደ እግዚአብሔር እና ወደ ፍቅሩ ለመድረስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ድልድይ ያስፈልገዋል። ሁላችንም በሰላም ሁሌም አንድ ህዝቦች መሆን እንድንችል፥ በውይይት እና ከሁሉም ጋር በመገናኘት ድልድዮችን እንድንገነባ ትረዱናላችሁ።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቺስኮስ እናመሰግናለን!

የጴጥሮስ ምትክ እንድሆን የመረጡኝ ብጹአን ካርዲናል ወንድሞቼን አመሰግናለሁ፥ ከእናንተ ጋር ሁላችንም በተባበረች ቤተክርስቲያን ውስጥ በአንድነት ሆነን ሰላም እና ፍትህን እንድፈልግ፣ እንደ ሴት እና ወንድ በአንድነት እንድሰራ፣ ያለ ፍርሃት ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ታማኝ እንድሆን፣ ክርስቶስን እንድሰብክ፣ ሚስዮናውያን እንድሆን፣ ለወንጌል ታማኝ ሆኜ አብሬያችሁ እንድሄድ የመረጣችሁኝ ብጹአን ካርዲናል ወንድሞቼን አመሰግናለሁ።

እኔ የቅዱስ አውግስጢኖስ ልጅ ነኝ፣ የቅዱስ አጎስጢኒዮስ ማህበር አባል ነኝ፥ እርሱም፣ “ከአንተ ጋር ክርስቲያን ነኝ፣ ለእናንተ ደግሞ ጳጳስ ነኝ” ብሏል። ስለዚህም ሁላችንም እግዚአብሔር ወዳዘጋጀልን ሃገር አብረን እንጓዝ።

ለሮም ቤተ ክርስቲያን የቀረበ ልዩ ሰላምታ፡-
እንዴት ሚስዮናዊት ቤተ ክርስቲያን መሆን እንደሚቻል፥ ድልድዮችን መገንባት፣ መነጋገር እንደምንችል፥ በጎ አድራጎታችንን፣ መገኘታችንን፣ ውይይትን፣ ፍቅርን ለሚፈልጉ ሁሉ ሰው ሁል ጊዜ በተዘረጋ እጅ ለመቀበል፣ ልክ እንደዚህ አደባባይ ክፍት እንዴት እንደምንሆን አብረን ማየት አለብን።

[በስፓኒሽኛ] :
ሰላም ለሁላችሁም ይሁን፥ በተለይም ሃገረ ስብከቴ በሆነው የፔሩ ቺክላዮ ሀገረ ስብከት ላሉት ታማኝ ለሆናችሁ፣ ሁሌም ከአቡናቸው ጋር አብረው ለሚሄዱ እና ለሚረዱ ምዕመናን በሙሉ ሰላም ለእናንተ ይሁን።

[ወደ ጣሊያንኛ በመመለስ]፡-
ሮም ከተማ ለምትገኙ፣ በጣሊያን ሃገር እንዲሁም በመላው ዓለም ለምትገኙ ወንድሞች እና እህቶች በሙሉ፥ ሁል ጊዜ ሰላምን፣ ምጽዋትን፣ አብሮነትን በተለይም በስቃይ ውስጥ ላሉ በሙሉ ሲኖዶሳዊ ቤተክርስቲያን መሆን እንፈልጋለን።

ዛሬ የፖምፔዋ እመቤታችን ቅድስት ማሪያም ቀን ነው።

እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሁሌም ከእኛ ጋር መጓዝን ትፈልጋለች፣ ወደ እኛ ትቀርባለች፣ በአማላጅነቷ እና በፍቅሯ ትረዳን ዘንድ ትፈልጋለች። ስለዚህ ለዚህ ተልእኮ እና ለመላው ቤተክርስቲያን፣ ብሎም ለዓለም ሰላም አብረን እንጸልይ።

ይህንን ልዩ ጸጋ እናገኝ ዘንድ የእናታችን ድንግል ማርያም አማላጅነት እንለምናለን።

(በመጨረሻም ከህዝቡ ጋር  'ጸጋ የሞላሽን' በመድገም አጠቃለዋል።)
 

09 May 2025, 16:23