ር. ሊ. ጳ. ሌዮ 14ኛ፥ የክኅነት እና የምንኩስና ሕይወት ጥሪን ለማሳደግ መጸለይ እንደሚገባ አሳሰቡ
ክቡራት እና ክቡራን የዝግጅቶቻችን ተከታታዮች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ በዕለቱ የቅዱስ ወንጌል ምንባብ ያደረጉትን አስተንትኖ ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ መልካም ሰንበት እንዲሆንላችሁ እመኝላችኋለሁ! የሮም ጳጳስ ከሆንኩ በኋላ በሐዋርያዊ አገልግሎቴ የመጀመሪያ እሑድ እና በብርሃነ ትንሳኤው አራተኛ ሳምንት የተከበረውን የመልካም እረኛ በዓልን እንደ እግዚአብሔር ስጦታ አድርጌ እቆጥረዋለሁ።
በዚህ እሑድ በምናሳርገው የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መካከል ዘወትር የሚነበበው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አሥር የተወሰደ ሲሆን፥ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን እንደ እውነተኛ እረኛ የገለጠበት፣ በጎቹን በማወቅ እና በመውደድም ነፍሱን ስለ እነርሱ መስጠቱን የሚገልጽ ነው።
የዛሬው እሑድ በተጨማሪም ላለፉት ስልሳ ሁለት ዓመታት ያከበርነውን ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀንንም ያስታውሰናል። ሮም በዛሬው ዕለት የሙዚቃ ባንዶች እና ታዋቂ የመዝናኛ ኢዮቤልዩ በዓልን እያስተናገደች ትገኛለች። ቤተ ክርስቲያንን በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ እና ሕያው የሚያደርግ የኢየሱስ ክርስቶስን መልካም እረኛ በዓልን በሙዚቃዎቻቸው እና በትርዒቶቻቸው ላደመቁት ምእመናን በሙሉ ልባዊ ሰላምታዬን እና ምስጋናዬን አቀርብላቸዋለሁ።
በቅዱስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎቹን እንደሚያውቅ እና ድምፁን ሰምተው እንደሚከተሉት ተናግሯል (ዮሐ. 10፡27)። በእርግጥም፣ ታላቁ መምህር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጎርጎርዮስ፥ ‘ሰዎች ለሚወዷቸው የፍቅር ምላሽን ይሰጣሉ’ በማለት ያስተምራሉ። (ስብከት 14፡3-6)
ስለዚህ ወንድሞቼ እና እህቶቼ ዛሬ ከእናንተ እና ከመላው የእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር በመሆን በተለይም ለክህነት እና ለምንኩስና ሕይወት ጥሪ ለመጸለይ እፈልጋለሁ። ቤተ ክርስቲያን እነሱን እጅግ ትፈልጋቸዋለች! በጥሪ የሕይወት ጉዞ ላይ የሚገኙ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች በማኅበረሰባቸው ውስጥ ተቀባይነትን፣ መደመጥን እና ብርታትን ማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው። ለእግዚአብሔር፣ ለወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ለጋስ የሆነ ራስን የመሰጠት እና ተአማኒነት ያላቸው ሞዴሎችን መፈለግ አስፈላጊ ነው።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት የተከበረውን የጥሪ ቀን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ወጣቶችን ተቀብለን በጥሪያቸው እናግዛቸው” በማለት ያስተላለፉትን ግብዣ እንቀበል። እርስ በርሳችን በመረዳዳት እንድንኖር፣ እያንዳንዱ እንደየ ሕይወቱ ሁኔታ እርስ በርሳችን በፍቅር እና በእውነት መረዳዳት እንድንችል የሰማዩ አባታችንን እንለምነው። (ኤር. 3፡15) ወጣቶች ሆይ አትፍሩ! የቤተ ክርስቲያንን እና የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግብዣ ተቀበሉ!”
ለእግዚአብሔር ጥሪ መላ ሕይወቷን የሰጠች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ኢየሱስን ስንከተል ዘወትር ከእኛ ጋር ትሁን።”