MAP

የር. ሊ. ጳ. ሌዮ 14ኛ የሐዋርያዊ መሪነት ምልክት የር. ሊ. ጳ. ሌዮ 14ኛ የሐዋርያዊ መሪነት ምልክት  

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳ ሌዮ 14ኛ የሐዋርያዊ መሪነት ምልክት ይፋ መሆኑ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ ሐዋርያዊ መሪነት ምልክት ከቅዱስ አጎስጢኖስ ሕይወት ጋር የተገናኘ እና ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያላቸውን ፍቅር የሚገልጽ መሆኑን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ ለሐዋርያዊ የመሪነት ሥልጣን የመረጡትን ምልክት በማስመልከት ረቡዕ ግንቦት 6/2017 ዓ. ም. ማብራሪያ ሰጥቷል።

በጣሊያን የቤተሰብ ታሪክ እና የዘር ግንድ ጥናት ተቋም ምክትል ፕሬዝዳንት አባ አንቶኒዮ ፖምፒሊ  የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ የሐዋርያዊ መሪነት ምልክት በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያ፥ ምልክቱ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር መንፈሳዊ እሴቶችን የሚገጽል መሆኑን አብራርተዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የመሪነት ምልክት እንደተለመደው የቅዱስ ጴጥሮስ ቁልፎችን እና የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማዕረግ የሚገልጹ ምልክቶችን የያዘ እንደሆነ ተመልክቷል። 

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ ሐዋርያዊ መሪነት ምልክት፥ በጋሻው የላይኛው ግራ ጥግ በኩል በሰማያዊ ቀለም ላይ የተሳለ የአበባ ቅጠል ያለው እና ከታች በቀኝ በኩል የእሳት ነበልባል የሚወጣበት እና በዝሆን ጥርስ በተሠራ መጽሐፍ ላይ የተቀመጠ በቀስት የተወጋ ቀይ ልብ እንደሚታይ ታውቋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ መሪ ቃል “IN ILLO UNO UNUM” ወይም  “በዚህ እኛ አንድ ነን” የሚል ጽሑፍ እንደተቀመጠበት ተመልክቷል።

መሪ ቃሉም፥ ቅዱስ አጎስጢኖስ በስብከቱ ቁ. 127 ላይ “እኛ ክርስቲያኖች ብዙ ብንሆን በክርስቶስ አንድ ነን” በማለት ያቀረበውን ስብከት የሚያስተጋባ እንደሆነ ታውቋል።

በጣሊያን የቤተሰብ ታሪክ እና የዘር ግንድ ጥናት ተቋም ምክትል ፕሬዝዳንት አባ አንቶኒዮ ፖምፒሊ  ሰማያዊው ቀለም የሰማይን ከፍታ የሚያሳይ እና ማርያማዊ ትርጉም እንዳለው ገልጸው፥ የሊሊ አበባ ቅጠል የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥንታዊ ምልክት እንደሆነ አስረድተዋል።

በተቃራኒው በኩል የሚታየው በቀስት የተወጋው እና የሚቃጠል ልብ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለሁለት ዙር ጠቅላይ አለቃ ሆነው ያገለገሉት የቅዱስ አጎስጢኖስ ገዳማውያን ማኅበር ዓርማ እንደሆነ አስረድተዋል።

አባ አንቶኒዮ ፖምፒሊ በማከልም፥ “ይህ ምልክት በምሳሌያዊ ሁኔታ ቅዱስ አጎስጢኖስ በኑዛዜ ቃሎቹ፥ ‘Sagittaveras tu cor meum charitate tua’ ወይም “ልቤን በፍቅርህ ወጋኸው” ያለውን የሚገልጽ እንደሆነ አስረድተዋል።

ይህ ምልክት ከ16 ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በቅዱስ አጎስጢኖስ የገዳማውያን ማኅበር ዓርማ ላይ የሚታይ መሆኑ ተገልጿል።

በተለምዶ የሰውን ልብ ሁሉ የሚለውጥ የእግዚአብሔር ቃል የቅዱስ አጎስጢኖስን ልብ የለወጠ በመሆኑ ከተከፈት መጽሐፍ ጋር አብሮ ይታያል።

“መጽሐፉ የጸጋ ዶክተር የተባለለት ቅዱስ አጎስጢኖስ ለቤተ ክርስቲያን እና ለሰው ልጆች በሙሉ ያበረከታቸውን ብሩህ ሥራዎችን የሚያስታውስ ነው” ያሉት አባ ፖምፒሊ፥

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ መሪ ቃል የተጻፈበት እና በዝሆን ጥርስ የተመሰለው ነጭ ቦታ በብዙ ገዳማዊ ማኅበራት ዘንድ የቅድስና እና የንጽህና ምልክት ሆኖ እንደሚቀርብ አስረድተዋል።

15 May 2025, 17:15