MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ ከሚዲያ ተቋማት ተወካዮች ጋር በተገናኙበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ ከሚዲያ ተቋማት ተወካዮች ጋር በተገናኙበት ወቅት  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሌዮ 14ኛ፥ የዜና ማሰራጫዎች የጥላቻ ቃላትን በመተው ሰላምን እንዲያበረታቱ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ ሐዋርያዊ ምርጫን ለመዘገብ በሮም ከተገኙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር ተገናኝተዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ለባለሙያዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የዜና ማሰራጫዎች እውነትን በማገልገል ሰላም እንዲሰፍን ማበረታታት እንዳለባቸው በማሳሰብ፥ የእርስ በርስ ግንኝነት የሕብረተሰብ ባህልን ለመፍጠር ይረዳል ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያንን በበላይነት የመምራት ከፍተኛ ሐዋርያዊ ሥልጣን በተቀበሉ በአምስተኛው ቀን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን ሕልፈት፣ የብጹዓን ካርዲናሎች ዝግ የምርጫ ጉባኤን እና የአዲሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የመጀመሪያ የአገልግሎት ቀናትን ለመዘገብ በሮም ከነበሩት ወንድ እና ሴት ጋዜጠኞች ጋር ተገኝተዋል።

ሰኞ ግንቦት 4/2017 ዓ. ም. በቫቲካን በሚገኘው ጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር በመገናኘት ጋዜጠኞቹ በእነዚህ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ላደረጉት ያላሰለሰ ጥረት በጣልያንኛ ቋንቋ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

ሰላምን ማበረታታት

አዲስ የተመረጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ ንግግራቸውን የጀመሩት፥ ለሰዎች እና ለብዙሃን መገናኛዎች ሊደረግ የሚገባውን እንክብካቤ እና ሰላምን ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ጥሪ በማቅረብ እንደ ነበር ታውቋል።

ቅዱስነታቸው ለብዙሃን መገናኛ ባለሞያዎች ባስተላለፉት መልዕክት፥ ምንም ዓይነት ዋጋን የማይፈልግ፣ ግልፍተኛ ቃላትን የማይጠቀም፣ የፉክክር ባሕልን የማይከተል እና እውነትን ከፍቅር የማይለይ የመገናኛ መንገድ መከተል እንደሚገባ አደራ ብለዋል።

“እርስ በርስ የምንገናኝበት መንገድ መሠረታዊ ጠቀሜታ አለው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ “የቃላት እና የምስል ጦርነቶችን በጠቅላላው የጦርነት ዘይቤን መቃወም አለብን” ብለዋል።

ስቃይ ከሚደርስባቸው ጋዜጠኞች ጎን መቆም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ እውነትን በመዘገባቸው ለታሰሩ ጋዜጠኞች ቤተ ክርስቲያን ያላትን አጋርነት አረጋግጠው እንዲፈቱም ጠይቀዋል።

ስቃያቸው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ እና የፕሬስ ነፃነት አስፈላጊነትን ዓለምን እንደሚያስታውስ ተናግረው፥ “ነጻ ምርጫን ማካሄድ የሚችሉት እውቀት ያላቸው ግለሰቦች ብቻ ናቸው” ብለዋል።

እውነትን ማገልገል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ ጋዜጠኞች እውነትን ለማገልገል በተለይም በቅርቡ ቤተ ክርስቲያንን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር በመታገዝ በተከሰተው የሐዋርያዊ ሥልጣን ክፍተት ወቅት ላበረከቱት ሥራ፥ የተዛባ አመለካከትን ወደ ጎን አድርገው ማንነታችንን ለዓለም ለማሳወቅ ላደረጉት ጥረት ጋዜጠኞችን አመስግነው፥ ዘመናችን ለመቁጠር እና ለመዳሰስ እጅግ አስቸጋሪ የሆኑ በርካታ ጉዳዮችን ማቅረቡን በመጥቀስ፥ እያንዳንዳችን እነዚህን ጉዳዮች ልናሸንፋቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

የዘመናችንን ፈተናዎች መጋፈጥ

“ቤተ ክርስቲያን የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች መጋፈጥ አለባት” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ በተመሳሳይ መልኩ የመግባቢያ እና የጋዜጠኝነት ሥራ ከጊዜ እና ከታሪክ ውጪ ሊሆኑ እንደማይችሉ ገልጸው፥ይህንንም ቅዱስ አውግስጢኖስ “በመልካም ከኖርን ዘመኑም መልካም ይሆናል፣ ማለቱን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ ዘመናዊው ዓለም “ብዙውን ጊዜ ርዕዮተ ዓለማዊ ወይም ወገንተኛ በሆኑ ፍቅር በሌላቸው ቋንቋዎች ግራ በመጋባት እንድንወድቅ ያደርገናል” ብለዋል።

ሚዲያዎች እኛ በምንጠቀምባቸው ቃላት እና በምንከተለው ዘይቤ ዓለምን ከእንዲህ ዓይነቱ ፈተና ውስጥ ለማውጣት ሃላፊነት ሊወስዱ ይገባል ብለዋል።

“የእርስ በርስ ግንኙነት መረጃን መለዋወጥ ብቻ ሳይሆን ባህልን መፍጠር እንደሆነ እና የሰዎች እና የዲጂታል መሣሪያ አካባቢዎች የውይይት እና የንግግር ቦታዎች ይሆናሉ” ብለዋል።

ሰው ሠራሽ አስተውሎት ሃላፊነትን እና ማስተዋልን ይፈልጋል

“አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ” ወይም ሰው ሰራሽ አስተውሎት መስፋፋትን በተመለከተ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ 14ኛ፥ ትልቅ አቅም እንዳለው በማስገንዘብ፥ “ለሁሉ ሰው ጥቅም እንዲውል ማድረግ ኃላፊነትን እና ማስተዋልን ይጠይቃል” ብለዋል ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ለ2025 ዓ. ም. ለዓለም አቀፍ የማኅበራዊ መገናኛ ቀን ያስተላለፉትን መልዕክት በመድገም፥ “ጭፍን ጥላቻን እና ቂምን፣ አክራሪነትን እና አልፎ ተርፎም የጥላቻ ቃላትን በማስወግድ ዓለም ወደ ሰላም እንዲያመራ እናደርለን” ብለዋል።

 

12 May 2025, 17:10