MAP

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ለእመቤታችን ማርያም የምናቀርበውን ውዳሴ እናሳድግ” ሲሉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ሮም ውስጥ የሚገኘውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁን ባዚሊካ በመሳለም፥ በባዚሊካው ውስጥ በሚገኝ የሮም ከተማ ነዋሪዎች ጥባቂ እመቤታችን ማርያም ቅዱስ ምስል ፊት እና በነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መካነ መቃብር ፊት ቀርበው ጸሎታቸውን ካቀረቡ በኋላ በሥፍራው ለተገኙት ባስተላለፉት መልዕክት፥ “ምዕመናን ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያላቸውን ውዳሴ ሊያሳድጉ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ እሑድ ግንቦት 17/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ጳጳሳዊ ባዚሊካ ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴን ጸሎት ካሳረጉ በኋላ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካን ጎብኝተዋል። በባዚሊካው ውስጥ በሚገኝ የሮም ነዋሪዎች ጠባቂ እመቤታችን ማርያም ቅዱስ ምስል ፊት ቀርበው ጸሎታቸውን አድርሰዋል።

ቅዱስነታቸው በጥንታዊው የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል ፊት አበባ ካስቀመጡ በኋላ ጸሎት ያደረሱ ሲሆን፥ በመቀጠልም በባዚሊካ ውስጥ በሚገኘው የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መካነ መቃብር ፊት ቀርበው ጸሎት አድርሰዋል።

በሥፍራ የተገኙትን አመስግነዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቫቲካን ወደሚገኘው መኖሪያቸው ከመመለሳቸው በፊት፥ በባዚሊካው ዙሪያ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሰላምታቸውን አቅርበው በሥፍራው ለተገኙት ሰላምን በመመኘት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መካነ መቃብር ፊት ቀርበው ጸሎት አድርሰዋል
በነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መካነ መቃብር ፊት ቀርበው ጸሎት አድርሰዋል   (@Vatican Media)

ቅዱስነታቸው ለምዕመናኑ ባሰሙት ንግግርም፥ የሮም ሀገረ ስብከት ምዕመናንበ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ወደ ባዚሊካው መጥተው የአዲሱን ጳጳስ መገኘት ሲያከብሩ በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፥ ልባዊ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።

ለእመቤታችን ያላቸውን ውዳሴ እንዲያድሱ ጥሪ አቅረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመቀጠልም፥ “በዚህ ባዚሊካ ውስጥ የሚያገለግሉትን በሙሉ፣ በዕለቱ አብረዋቸው የነበሩ ሁለቱን ካርዲናሎች እና ሌሎች የጸሎት እና የአምልኮ ሕይወት እንዲኖሩ በታማኝነት የሚያግዙ በርካታ ሰዎችንም አመስግነዋል።

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ አሥራ አራተኛ በባዚሊካው ዙሪያ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሰላምታ ሲያቀርቡ
ር. ሊ. ጳ. ሊዮ አሥራ አራተኛ በባዚሊካው ዙሪያ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሰላምታ ሲያቀርቡ   (ANSA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተጨማሪም፥ ከእግዚአብሔር እናት ጋር ግንኙነት የመፍጠርን አስፈላጊነት አፅንዖት ሰጥተው፥ “የሮም ከተማ ነዋሪ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ በሚገኝበት ወቅት ጠባቂው የሆነችለት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ምስል በመመልከት ለማርያም ያለንን ታማኝነት የምናድስበት አስደናቂ ጊዜ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

እግዚአብሔር በእናቱ በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ሁላችሁን፣ ቤተሰቦቻችሁን እና የምትወዷቸውን በሙሉ እንዲባርክ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደ አንድ የእግዚአብሔር ቤተሰብ በኅብረት እንድንጓዝ እንዲረዳን እግዚአብሔርን እንለምነው” በማለት አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሥነ-ሥርዓቱ ማጠቃለያ፥ ከምእመናን ጋር ሆነው ወደ እመቤታችን ማርያም ዘንድ ያቀረቡትን ጸሎት በመምራት ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ከሰጡ በኋላ መልካም ምሽትን ተመኝተውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካን በጎበኙበት ወቅት

 

 

26 May 2025, 17:50