MAP

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የመንበረ ጴጥሮስ አገልግሎት ጅማሬ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የመንበረ ጴጥሮስ አገልግሎት ጅማሬ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በሰኔ ወር ዘወትር እሁድ የሚመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ መርሃ-ግብር ይፋ ሆነ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጭው ሰኔ ወር ውስጥ በሚውሉ እሁዶች የሚቀርቡ መስዋዕተ ቅዳሴዎችን እንደሚመሩ የተገለጸ ሲሆን፥ እንዲሁም በልዩ ልዩ የቅድስና ጉዳዮች ላይ ድምጽ የሚሰጥ የካርዲናሎች ጉባኤን እንደሚጠሩ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት በሚቀጥለው ሰኔ ወር የሚፈጸሙ የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች መርሃ-ግብር ዋቢ በማድረግ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ጽሕፈት ቤቱ በመግለጫው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ሰኔ 1 (እ.አ.አ) ከረፋዱ በአራት ሰ ዓት ተኩል ላይ የቤተሰብ፣ የሕጻናት፣ የአያቶች እና የአረጋውያን ኢዮቤልዩ በዓል ለማክበር በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የሚቀርብ መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚመሩ አስታውቋል።

የጰራቅሊጦስ በዓል በሚከበርበት እሑድ ሰኔ 8 (እ.አ.አ) ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከረፋዱ አራት ሰዓት ተኩል ላይ ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ማኅበራት፣ እንቅስቃሴዎች እና አዳዲስ ማኅበረሰቦች የኢዮቤልዩ በዓል መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚመሩ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው በማግሥቱ ሰኞ ሰኔ 9 (እ.አ.አ) በቤተ ክርስቲያን እናት ቅድስት ድንግል ማርያም መታሰቢያነት የሚሆን የቅድስት መንበር ኢዮቤልዩ በዓል መስዋዕተ ቅዳሴን በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ ከረፋዱ አምስት ሰዓት ተኩል ላይ የሚያቀርቡ መሆኑን መርሐ ግብሩ ይገልጻል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዚያው ሳምንት ውስጥ ማለትም ዓርብ ሰኔ 13 (እ.አ.አ) ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ በልዩ ልዩ የቅድስና ጉዳዮች ላይ ድምጽ ከሚሰጡ ካርዲናሎች ጋር ጉባኤን እንደሚያካሂዱ ታውቋል።

እሑድ ሰኔ 15 (እ.አ.አ) ከረፋዱ አራት ሰዓት ተኩል ላይ የስፖርተኞች ኢዮቤልዩን በማስመልከት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ይመራሉ።

በሳምንቱ እሑድ ሰኔ 22 (እ.አ.አ) ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ደም (ኮርፐስ ክሪስቲ) ክብረ በዓልን የምታከብር ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዕለቱ በቅዱስ ዮሐንስ ዘላተራን ባዚሊካ ውስጥ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴን ከመሩ በኋላ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ታላቁ ባዚሊካ ውስጥ የሚፈጸም የቁርባን ቡራኬ ሥነ-ሥርዓት ይሳተፋሉ።

ዓርብ ሰኔ 27 (እ.አ.አ)ዓመታዊ የቅዱስ ልበ ኢየሱስ በዓል በማስመልከት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ላይ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ እንደሚመሩ ተገልጿል። 

ከሁለት ቀናት በኋላ ማለትም እሑድ ሰኔ 29 (እ.አ.አ) የቅዱሳን ጴጥሮስ እና ጳውሎስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በማስመልከት ከጠዋቱ በሦስት ሰዓት ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ ውስጥ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴን የሚመሩ መሆኑን፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት የሰኔ ወር የአምልኮ ሥነ-ሥርዓቶች መርሃ-ግብርን መሠረት በማድረግ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

 

 

22 May 2025, 17:31