ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ "ርኅራሄ ሰብዓዊነት እንጂ የሃይማኖት ጉዳይ አይደለም" ሲሉ ገለጹ
ክቡራት ክቡራን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን አስቀድመን፥ ለአስተንትኖ የመረጡትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ቀጥሎ እናነብላችኋለን፥
“ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለ፥ አንድ ሰው ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ወረደ፤ በወንበዴዎችም እጅ ወደቀ፤ እነርሱም ደግሞ ገፈፉት ደበደቡትም በሕይወትና በሞት መካከልም ትተውት ሄዱ።እንደ አጋጣሚ አንድ ካህን በዚያ መንገድ ወረደ፤ አይቶትም ገለል ብሎ አለፈ። እንዲሁም ደግሞ አንድ ሌዋዊ ወደዚያ ስፍራ መጣና አይቶት ገለል ብሎ አለፈ። አንድ ሳምራዊ ግን በጉዞ ላይ ሳለ እርሱ ወደ ነበረበት መጣ አይቶትም አዘነለት” (ሉቃ. 10: 30-33)።
ክቡራት እና ክቡራን አድማጮቻችን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ረቡዕ ግንቦት 20/2017 ዓ. ም. ያቀረቡትን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ፣ አመለካከታችንን ለመለወጥ እና እራሳችንን ለተስፋ በምንከፍትባቸው አንዳንድ የቅዱስ ወንጌል ምሳሌዎች ላይ ማስተንተን እንቀጥል። አንዳንድ ጊዜ ነገሮችን ለመመልከት ያለን ግትር እና ዝግ እይታ ተስፋ ቢስነትን ሲያስከትል፥ በሌላ መንገድ ደግሞ የቅዱስ ወንጌል ምሳሌዎች ነገሮችን በሌላ አቅጣጫ እንድንመለከታቸው ይረዱናል።
ዛሬ ራሱን በሚገባ ስላዘጋጀ አንድ የሕግ አዋቂ፥ ነገር ግን አመለካከቱን መለወጥ ሲገባው በራሱ ላይ ብቻ ስለሚያተኩር ስው ታሪክ ልነግራችሁ እፈልጋለሁ (ሉቃ. 10፡25-37)። ይህ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለም ሕይወት እንዴት መውረስ እንደሚቻል በማያሻማ መንገድ በገለጸው ላይ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። ነገር ግን ከዚህ ጥያቄ ጀርባ ትኩረት የሚያስፈልገው ነገር አለ። ኢየሱስ እንዲያብራራለ የጠየቀው ብቸኛው ቃል “ባልንጀራ” የሚለው ብቻ ሲሆን ትርጉሙም ከሌሎች ይበልጥ የሚቀርብ ሰው ማለት ነው።
በዚህ ምክንያት ኢየሱስ፥ ‘ይበልጥ የሚወደኝ ማን ነው?’ ከሚለው ጥያቄ ወደ ‘ሌሎችን የሚወድ ማነው’ ወደሚለው የተኬደበትን መንገድ የሚገልጽ ምሳሌ ተናገረ። የመጀመሪያው ጥያቄ ገና ያልበሰለ ነበር። ሁለተኛው ደግሞ የሕይወት ትርጉም የተረዳ የአዋቂ ሰው ጥያቄ ነበር። የመጀመሪያው ራሳችንን ወደ ጥግ አድርገን የምንጠይቀው ጥያቄ ሲሆን ሁለተኛው ግን ሌሎችን መውደድ ወደሚለው የሚገፋፋን ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረው ምሳሌ በእርግጥ እንደ ሕይወት አስቸጋሪ እና የማይሸነፍ መንገድ ነው። ከኮረብታማ የኢየሩሳሌም ከተማ ከባሕር ወለል በታች ወዳለችው ወደ ኢያሪኮ ከተማ የወረደ ሰው መንገድ ነው። ይህ ሊሆን እንደሚችል አስቀድሞ የሚያመለክት ምስል ነው። በዚያ ሰው ላይ ጥቃት ሲደርስበት፣ ሲደበደብ፣ ሲዘረፍ እና ግማሽ ሞቶ ሲገኝ ያሳያል። አንዳንድ ጊዜ የምናምናቸው ሰዎች እንኳን ሁሉንም ነገር ከእኛ ነጥቀው የሚወስዱትን ሁኔታ የሚገልጽ ልምድ ነው።
ሕይወት ግን ለዚህ የተፈጥረች ናት። በእነዚህ ገጠመኞች ውስጥ ማንነታችንን እንወጣለን። እኛ እራሳችን በሌላው ፊት በደካማነት እናገኛለን። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ እንዳለብን መወሰን እንችላለን። ራስን እንንከባከባለን ወይም ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ እናስመስላለን። አንድ ካህንና አንድ ሌዋዊ በዚያው መንገድ እየሄዱ ነበር። በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉ እና በተቀደሰው ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ናቸው። ሆኖም ግን በዚህ በተቀደሰ ቦታ ማገልገላቸው ወዲያውኑ ወደ ርኅራኄ አልመራቸውም። እንደውም ርህራሄ የሃይማኖት ጉዳይ ከመሆኑ ይልቅ የሰው ልጅ ጥያቄ ሆነ። አማኞች ከመሆናችን በፊት ሰው እንድንሆን ተጠርተናል።
ካህኑ እና ሌዋዊው ለረጅም ጊዜ በኢየሩሳሌም የቆዩ ቢሆንም ወደ ቤታቸው ለመመለስ ቸኩለው እንደነበር መገመት እንችላለን። ይህን የመሰለ ችኮላ በሕይወታችን ውስጥም አለ። ይህ ችኮላችን ብዙ ጊዜ ርህራሄ እንዳይሰማን ያደርገናል። ስለ ራሱ ብቻ የሚያስብ ሰው ስለ ሌላው ለማሰብ ፈቃደኛ አይደለም።
ነገር ግን እየሄደ ቆም ብሎ ችግር ለደረሰበት የሚጨነቅ አንድ ሰው ደረሰ። እርሱም ከተናቀ ሕዝብ ወገን የሆነ ሳምራዊ ሰው ነው (2ኛ ነገ. 17)። በእርሱ ሁኔታ ላይ ጽሑፉ ይህ ሰው ወደ የት አቅጣጫ እንደሚጓዝ አይገልጽም። ነገር ግን ተጓዥ እንደ ነበረ ብቻ ይናገራል። ሃይማኖታዊነት ከዚህ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ይህ ሳምራዊ ሰው የቆመው ፊት ለፊት ያገኘው ሰው ዕርዳታ እንደሚስፈልገው ስለተረዳ ብቻ ነው።
ርኅራኄ የሚገለጸው በተጨባጭ ምልክቶች ነው። ወንጌላዊው ሉቃስ "መልካም" ብለን በምንጠራው ሳምራዊ ሰው ድርጊት ላይ ያተኩራል። ነገር ግን በጽሑፉ ውስጥ በቀላሉ ሰው የሆነውን ማንንም ይመለከታል። ሳምራዊው ሰው ችግር ውስጥ ወደ ወደቀው ሰው ዘንድ ቀረበ። ምክንያቱም አንድን ሰው መርዳት ከፈለጋችሁ በርቀት ለመቆም ከማሰብ ይልቅ ጣልቃ መግባት፣ ራስን ማቆሸሽ ምናልባትም የችግሩ ተካፋይ መሆን ያስፈልጋል። ቁስሎቹን በዘይት እና በወይን ካጸዳ በኋላ አሰራቸው፤ ተሸክሞትም ወደ ሌላ ቦታ ወሰደው፤ ማለትም ሃላፊነትን ወሰደ። ምክንያቱም የሌላውን ሰው ሕመም ክብደት ለመስማት ፈቃደኛ በመሆን ከልብ ለመርዳት ፈለገ። የተወሰነ ገንዘብ ከፍሎ ወደሚያሳርፍበት ቦታ ወሰደው። ምናልባትም እንደገና ተመልሶ ሊጠይቀው እና ሊከፍልለት ቃል ገባ። ምክንያቱም ያ የተጎዳው ሰው ማስረከብ ያለበት ዕቃ ሳይሆነ ነገር ግን እንክብካቤ የሚያስፈልገው ሰው ነው።
ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ! እኛም መቼ ነው የእኛን ነገር ወደ ጎን አድርገንን ለሌሎች የምንራራው? ያ መንገድ ላይ የወደቀው እና የቆሰለው ሰው እያንዳንዳችንን እንደሚወክል መረዳት አለብን። ኢየሱስ እኛን ሊንከባከብ የቆመበትን ጊዜ ማሰብ የበለጠ ርኅሩሆች እንድንሆን ያስችለናል።
እኛም በሰብዓዊነት መንፈስ እንድናድግ፣ የእርስ በርስ ግንኙነታችን የበለጠ በእውነት እና በርኅራኄ የጎለበት እንዲሆን እንግዲያውስ እንጸልይ። በርኅራሄ የተሞላ የኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ተመሳሳይ ስሜቶች እንዲኖረን ጸጋውን እንጠይቀው።”