ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጋዛ ተኩስ እንዲቆም ጥሪ አቀረቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዱስነታቸው ረቡዕ ግንቦት 20/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የአገር ጎብኝዎች ሳምንታዊ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ባቀረቡበር ወቅት፥ በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ፥ የታገቱትም ነፃ እንዲወጡ እና የሰብዓዊ መብት ሕግ ሙሉ በሙሉ እንዲከበር ተማጽነዋል።
“ከጋዛ ሰርጥ ወደ ሰማይ የሚያቀና የስቃይ ድምጽ እንሰማለን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በሕይወት የሌሉ ልጆቻቸውን የሚጨብጡ እናቶች እና አባቶች ጩኸት፣ ከቦምብ ጥቃት ተርፈው ትንሽ የሚቀመስ ምግብ እና ውሃ ለማግኘት፣ እንዲሁም አስተማማኝ መጠለያ ፍለጋ ሲሉ ያለማቋረጥ ከቦታ ቦታ ለመንከራተት የሚገደዱ ሰዎች መኖራቸውን እንሰማለን” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሰላም ጥሪያቸውን ያቀረቡት፥ በጋዛ በሚገኙ የዕርዳት ማከፋፈያዎች ምግብ ለመቀበል ሲሞክሩ 50 በሚጠጉ ሰዎች ላይ የእስራኤል ጦር ጉዳት ካደረሰባቸው ከአንድ ቀን በኋላ እንደሆነ ታውቋል።
የፍልስጤም ታጣቂዎች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት 2023 ዓ. ም. እስራኤል ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ከሁለት ሳምንት በፊት የእስራኤል ሠራዊት ጦርነት ውስጥ በነበረ አካባቢ አዲስ ጥቃት መፈጸሙ ታውቋል።
ለዩክሬን ሰላም የቀረበ ጥሪ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሰላምታ ባቀረቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ ቀድሞውኑ በጦርነት በተጎሳቆለች ዩክሬን ውስጥ በሲቪሎች እና በመሠረተ ልማት አውታሮቿ ላይ አዳዲስ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ያስታወሱ ሲሆን፥ የሩስያ ድሮኖች እና ሚሳኤሎች በዋነኛነት ሲቪሎችን ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ማድረሳቸው ታውቋል።
ይህ ጥቃት ሩሲያ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2022 ዓ. ም. በዩክሬን ሙሉ ወረራ ማካሄድ ከጀመረች በኋላ ከፈጸመቻቸው የአየር ጥቃቶች ውስጥ ትልቁ እንደሆነ ተነግሯል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ጦርነት ቆሞ ለውይይት እና ለሰላም የሚደረግውን ማንኛውንም ተነሳሽነት መደገፍ ያስፈልጋል” በማለት ጥሪያቸውን አድሰው፥ በጦርነቱ ለተጎዱት በሙሉ በተለይም ለህፃናት እና ወላጆቻቸው ያላቸውን ቅርበት በማረጋገጥ በጸሎትም እንደሚያስታውሷቸው ገልጸዋል።
ዩክሬንን ጨምሮ በጦርነት ምክንያት ሰዎች በሚሰቃዩባቸው ቦታዎች በሙሉ ሰላም እንዲሰፍን ምዕመናን እንዲጸልዩ አደራ ብለዋል።