ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ “ከእንግዲህ ጦርነት ይብቃ!” ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ እሑድ ግንቦት 3/2017 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ወደ አንድ መቶ ሺህ ከሚደርሱ ምዕመናን እና የአገር ጎብኚዎች ጋር ሆነው ወደ እመቤታችን የሰማይ ንግሥት ጸሎት አድርሰው፥ በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ የፊት ለፊት ሰገነት ላይ ሆነው በአደባባዩ ለተሰበሰቡት ምእመናን እና ከዓለም ዙሪያ ለመጡ ሥፍር ቁጥር ለሌላቸው ሰዎች ንግግር አድርገዋል።
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ አልፎ አልፎ የሚከሰቱ እና ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት የሚመስሉ ግጭቶች ከሚሏቸው ጋር ተዛማጅነት ያለውን፥ “ከእንግዲህ ጦርነት ይብቃ!” የሚለውን መልዕክት በመድገም ለዓለም ኃያላን የሰላም ጥሪ አቅርበዋል።
ለዩክሬይን እና ለጋዛ የቀረበ የሰላም ጥሪ
60 ሚሊዮን ለሚሆኑት ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን እና ከ80 ዓመታት በፊት በግንቦት ወር ውስጥ ያበቃው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያስከተለውን ታላቅ አሳዛኝ ክስተት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ ዛሬ ዓለምን እያስጨነቁ የሚገኙ ዘመናዊ ጦርነቶች እና በዚህ ጦርነት በሚሰቃይ የዩክሬይን ሕዝብ ምክንያት ልባቸው ማዘኑን ገልጸው፥ በተቻለ ፍጥነት እውነተኛ፣ ፍትሐዊ እና ዘላቂ ሰላም እንዲገኝ ማንኛውም ጥረት እንዲደረግ፣ የጦር እስረኞች በሙሉ እንዲፈቱ፣ ሕጻናትም ወደ ቤተሰባቸው እንዲመለሱ አሳስበዋል።
በጋዛ ሰርጥ እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ በዚህም ልባቸው እጅግ ማዘኑን ገልጸው፥ በአካባቢው እየተካሄደ ያለው ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ ለደከሙት ሲቪሎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲደርሳቸው እና ሁሉም ታጋቾች ይፈቱ ዘንድ በማለት ተማጽነዋል።
ተስፋ እና ልባዊ ጥሪ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ፥ በቅርቡ በሕንድ እና በፓኪስታን መካከል ተኩስ እንዲቆም መታወጁን በደስታ ተቀብለው በመጪው ድርድር በቅርቡ ዘላቂ ስምምነት ሊደረስ እንደሚችል ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በመቀጠልም “በዓለም ውስጥ ስንት ሌሎች ጦርነቶች አሉ?” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሌዮ አሥራ አራተኛ በመጨረሻም፥ የሰላም ንግሥት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የሰዎችን ስቃይ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በማቅረብ ሰላምን እንድታስገኝልን” በማለት ተማጽነዋል።